ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቀድሞ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንት ለዶክተር አምባቸው መኮንን መታሰቢያ ህንጻ ማሰሪያ የመሬት ካርታ መስጠቱ ተሰማ።
ባህር ዳር ከተማ ተደርጎ በነበረው በሰኔ 15ቱ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ የተሰውት ዶክተር አምባቸው መኮንን መታሰቢያ ሕንጻ ማሰሪያ የሚሆን ቦታ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 2 ሺኅ 250 ካሬ ሜትር የተመረጠ ሲሆን፣ የዚህን የመሬት ካርታ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ለሰማዕቱ ቤተሰቦች ማስረከባቸው ታውቋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከአሁን ቀደም ለዶክተር አምባቸው መኮንን ፣ አቶ ምግባሩ ከበደ እና አቶ እዘዝ ዋሴ ቤተሰቦችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት የሰጠ ሲሆን፣ ለኢታማጆር ሹም የነበሩት ሰዓረ መኮንን 1 ሺኅ ካሬ ሜት የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ መስጠቱ አይዘነጋም።
በርክክቡ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ ጀግኖቻችንን ለማሠብ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል ያሉት ም/ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ወደፊትም ለቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ከጎናቸው መቆሙን ይቀጥላል ሲሉም ተደምጠዋል።

























