በምርጫው ጉዳይ የአውሮፓ ሕብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት መስማማት አለመቻላቸው ተገለጸ!

በምርጫው ጉዳይ የአውሮፓ ሕብረትና የኢትዮጵያ መንግሥት መስማማት አለመቻላቸው ተገለጸ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናየአውሮፓ ሕብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ከስምምነት መድረስ ባለመቻለሁ ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ አስቦ የነበረውን የምርጫ ታዛቢ እንዲቀር መወሰኑን ከቀናት በፊት ይፋ አድርጓል።

የአውሮፓ ህብረት 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ያቀረበውን ቅድመ ሁኔታ ኢትዮጵያ እንደማትቀበለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡

ሰኞ ዕለት፣ የሕብረቱ የውጪ ጉዳዮች እና የደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል የአውሮፓ ሕብረት ለቀጣዩ ምርጫ ታዛቢዎችን ለመላክ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን በገለፁበት መግለጫቸው “ህብረቱ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ለመላክ ከፍተኛ ጥረት ቢያደረግም ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለስልጣናት ጋር የአውሮፓ ሕብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን የሚሰማራበት ቁልፍ መለኪያዎች (ፓራሜትርስ) ላይ ከስምምነት መድረስ አልተቻለም” ብለዋል።

በዚህም ሕብረቱ ግንቦት 28 በሚደረገው ምርጫ ላይ ታዛቢ ልዑክ ላለመላክ መወሰኑን ይፋ ያደረጉት ጆሴፍ ቦሬል “የአውሮፓ ሕብረት የዲሞክራሲ ግንባታ ድጋፍ ዋናው ምሰሶ የምርጫ ታዛቢ ልዑክ ትክክለኛነት ነው። ሕብረቱ የምርጫ ታዛቢ ልዑኩን ለመላክ ያቀረባቸው መስፈርቶች እንዳይሟሉ መከልከሉ አሳዝኖኛል” ሲሉም ተናግረዋል።

ይሁንና “የአውሮፓ ህብረት ምርጫን ለመታዘብ ያቀረበውን ጥያቄ ኢትዮጵያ አትቀበለውም” በማለት የኢትዮጵያን አቋም ያንፀባረቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “ህብረቱ 6ኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ያቀረበው ጥያቄ የሀገርን ሉአላዊነት የሚጋፋና የኢትዮጵያን ህጎች የማያከብር ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጡ ጥያቄው ተቀባይነት አላገኘም” ብለዋል፡፡

ህብረቱ በቅድመ ሁኔታነት ካስቀመጧቸው ጉዳዮች በህግ ያልተፈቀደ ከቴሌኮሚዩኒኬሽን ቁጥጥር ውጪ የሆነ ቪሳት የሳተላይት መሳሪያ ይዘው ለመግባትና ከምርጫ ቦርድ አስቀድሞ መግለጫ ለማውጣት መፈለጋቸው ስለመሆኑም አምባሳደር ዲና ተናግረዋል፡፡

LEAVE A REPLY