ኢትዮጵያ ነገ ዜና፡– የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የኮምዩኒኬሽንና ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ እንዳስታወቁት፣ የኮሚሽነር አበረ አዳሙ ሥርዓተ ቀብር ነገ በባሕር ዳር ይፈጸማል።
የሥርዓተ ቀብሩም በፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት እንደሚፈጸም ተናግረዋል።
በተያያዘ “ቀድሞው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ድንገተኛ ህልፈተ ህይወት የተሰማኝን መሪር ሃዘን እገልፃለሁ” ሲሉ ምክትል ጠ/ሚ/ር እና የውጭ ጉዳይ ሚ/ር አቶ ደመቀ መኮንን መልዕክት አስተላልፈዋል።
“ወንድማችን ለክልሉ ሁለንተናዊ ለውጥ ለዓመታት ከቤተሰቡ ርቆ ለዓላማው ሙሉ ጊዜውን በመስጠት በፅናት ያገለገለ ጠንካራ አመራር ነበር። የወንድማችን የአመራር አበርክቶዎች ታሪክ የማይዘነጋቸው ሲሆኑ፣ ይሄን የመሰለ ታላቅ ሰው በድንገት ማጣት ሃዘናችንን መራራ እና ጥልቅ ያደርገዋል። በአመራር ዘመኑ የደከመለትን በክልሉ የህግ የበላይነት እና ሰላምን የማረጋገጥ ቁልፍ ተልዕኮ በጓዳዊ ቅብብሎሽ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል። በመጨረሻም ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጅ ዘመዶቹ እንዲሁም ለመላው የክልላችን አመራር እና ህዝብ መፅናናትን እመኛለሁ” በማለትም አቶ ደመቀ መኮንን ሀዘናቸውንና ምስክርነታቸውን ገልፀዋል።
የቀድሞው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሚያዚያ 26/2013 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን ትናንት መዘገባችን ይታወሳል።

























