“የኢትዮጵያ ሳምንት” እና “ኢትዮጵያን እናልብሳት” የተሰኙ መርኃ ግብሮች መካሄድ ጀመሩ!

“የኢትዮጵያ ሳምንት” እና “ኢትዮጵያን እናልብሳት” የተሰኙ መርኃ ግብሮች መካሄድ ጀመሩ!

ኢትዮጵያ ነገ ዜናከግንቦት 10 እስከ ግንቦት 16/2013 ዓ.ም ድረስ፣ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት “የኢትዮጵያ ሳምንት” የተሰኘ መርኃ ግብር ትናንት ተከፍቷል።

በአዲስ አበባ የወዳጅነት ፓርክ በተከፈተው በዚህ የኢትዮጵያ ሳምንት ዝግጅት ላይ፣ ሁሉም ክልሎች ባህላቸውንና ማንነታቸውን የሚያሳዩ አውደ ርዕዮችንና ያላቸውን ሀብት ይዘው የቀረቡ ናቸው።

በመርኃ ግብሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የክልል ርእሰ መሥተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ ከዝግጅቱ የሚገኘው ገቢም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢ ለተፈናቀሉ ዜጎች ማቋቋሚያ እንደሚውል ተገልጿል።

በሌላ በኩል፣ ሦስተኛው ዙር የአረንጓዴ ዐሻራ የችግኝ ተከላ መርኃ ግብርም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከፍተኛ የፌደራል እና የክልል የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት ትናንት በይፋ ተጀምሯል።

“ኢትዮጵያን እናልብሳት” በሚል በተጀመረው የዘንድሮ
ዓመት የችግኝ ተከላ መርኅ ግብር፣ 6 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል መታቀዱና ከአገራችን አልፎ አፍሪካን ለማለምለም የሚደረግ አሕጉራዊ ጥረት ጅማሬ እንዲሆን ለማስቻልም ወደ ጎረቤት ሀገራት 1 ቢሊዮን ችግኞች እንደሚላኩ ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመርኃ ግብሩን መጀመር አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት “የኢትዮጵያውያን ሕይወት ከዛፎች እና ከጫካ ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ነው፡፡ ዛሬ የ2013ን የአረንጓዴ ዐሻራን የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር አስጀምረናል። በ2011 የአካባቢን ብክለትና የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመቅረፍ አስበን የአራት ዓመት ዕቅድ በማውጣት ያቀረብነው ሀገራዊ ጥሪ አንድ አካል ነው፡፡ በጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የምግብ ዋስትናን ያለማረጋገጥ፣ አካባቢ ተኮር ግጭቶች እና የመሳሰሉ አሉታዊ ሁኔታዎችን የመከላከያ መንገዱ በእጃችን ነው፡፡ ሲሉ ተናገረዋል።

አክለውም ለመላው ኢትዮጵያውያን ‘ኢትዮጵያን እናልብሳት’ ብዬ ጥሪ አቀርባለሁ። ጥሪው ሀገራችንን አረንጓዴ እናልብስ፣ በክልል፣ በጎሳ፣ በሃይማኖት፣ በጾታ ከመከፋፈል አልፈን፣ ለዚህ ታላቅ ሕዝብ በሚመጥን መልኩ፣ ኢትዮጵያችንን በብልጽግና እና በክብር በአንድነት የተፈጥሮ ልብሷን እናልብሳት ማለቴ ነው” ብለዋል።

LEAVE A REPLY