ኢትዮጵያ ነገ ዜና || የትራፊክ ቅጣትን በቴሌ ብር መክፈል የሚያስችል ስምምነት በኢትዮ ቴሌኮም እና በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ መካከል ተፈረመ።
ትራፊክ ፖሊሶች አጭር ቁጥርን 6050 በመጠቀም በአጭር የጽሁፍ መልእክት ቅጣቱን በመመዝገብ ለተቀጪዉ አሽከርካሪ በእጅ ስልክ አማካይነት በሚደርሰው የቅጣት ደረሰኝ የትራፊክ ደንብ ቅጣት ክፍያን በቴሌ ብር በኩል መፈጸም ይቻላል ተብሏል።
የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ብርሃኑ ኩማ እንደገለፁት “6050 የአጭር ፅሁፍ መልዕክት ለትራፊክ ፖሊሶች እንደመዝገብ የሚያገለግል በመሆኑ የሚይዙትን መዝገብ (ፓድ) ያስቀራል ብሏል። በተጨማሪም አሽከርካሪዎች መንጃ ፈቃዳቸው ሳይያዝና ቢሮ ለቢሮ ሳይንቀሳቀሱ ቅጣታቸውን ከፍለው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።
ይህ አሰራር የቅጣት ክፍያ አገልግሎቱ ሙሉ ለሙሉ የወረቀት አሰራርን የሚተካ፣ ቅጣቱን ወዲያው በመክፈል የመንጃ ፈቃድ እንዳይያዝ የሚያደርግ ቀላል እና ጊዜ ቆጣቢ መሆኑንም የኮምኒኬሽን ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።
የቴሌ ብር ቴክኖሎጂ 15 ነጥብ 6 ሚሊየን የቴሌ ብር ደንበኞች አገልግሎቱን እየተጠቀሙ ሲሆን በ42 ሚሊየን የገንዘብ ዝውውሮች 7.9 ቢሊየን ብር መንቀሳቀሱን ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል።
ይህ አገልግሎት ወይም አሰራር ለዘመናት አድካሚ የነበረውን በወረቀት ላይ ያተኮረ የቅጣት ክፍያ አፈጻጸምን ያስቀራል የተባለለት ሲሆን፤ በተለይ አሽከርካሪዎች የቅጣት ክፍያውን ለመፈፀም የሚወስድባቸውን ጊዜ በመቆጠብ እና ድካምን የሚያስቀር ዘመናዊ አገልግሎት ከመሆኑም ባሻገር መንግስት ለመቅጫ ፓድ ህትመት የሚያወጣውን ወጪንም እንደሚያስቀር መገለፁን ከኤጀንሲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

























