ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከግለሰቦች አጭበርብረው የተሰወሩት ሀፍቶም ኃይሌ ያሉበት አልታወቀም

ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከግለሰቦች አጭበርብረው የተሰወሩት ሀፍቶም ኃይሌ ያሉበት አልታወቀም

ኢትዮጵያ ነገ ዜና–  በ84 ማሊዮን ብር በላይ የሚሆን ገንዘብ ከግለሰቦች ላይ ሰብስበው የተሰወሩት ባለሀብት እስካሁን ድረስ ያሉበት ሊገኝ አልቻለም።

ኤች ቱ (H2) የቋንቋ እና የኮምፒተር ትምህርት ቤት ባለቤት የሆኑት አቶ ሀፍቶም ኃይሌ ከ100 በላይ የሚሆኑ ግለሰቦችን ገንዘብ በብድር እና “የድርጅቱ ተጋሪ ትሆናላችሁ” በማለት የተለያየ የገንዘብ መጠን በመቀበል ድንገት አድራሻቸውን አጥፍተው ከተሰወሩ አንድ ወር አልፏቸዋል።
 የገንዘብ ማጭበርበር ወንጀል ተፈጽሞብናል በማለት አስካሁን ቅሬታቸውን ያቀረቡ ሰዎች ቁጥር 120 ደርሷል።  የእነዚህ ሰዎች ብር መጠን ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ቢደርስም ግለሰቡ እስካሁን ድረስ የት እንዳሉ ለማወቅ እንዳልተቻለ ታውቋል።
 ሚሚ ሳህለ የተባለች ተበዳይ ” የኤች ቱ ቋንቋ እና ኮምፒተር ትምህርት ቤት ባለቤት ሀፍቶም ኃይሌ የድርጅቱ ተጋሪ ወይም ባለድርሻ ትሆኛለሽ በሚል አራት ዓመት በውጭ አገር ያፈራሁትን ገንዘብ 180 ሺኅ ብር ከመቀበላቸው ባሻገር ፤ በድርጅቱ ውስጥ ሠራተኛ ሆኘ እንዳገለግል በመስማማት የ180 ሺኅ ብር ደረቅ ቼክ ሰጥቶኝ፣ በእምነት የድርጅቱ ተጋሪ እሆናለሁ ብዬ ስለፋ ገንዘቤን ቀምቶኝ ተሰውሯል” ስትል የገጠማትን ክፉ ነገር አስረድታለች።
 ግለሰቡ በተሰወሩ ሰሞን በሰልክ ደውላ የቤት ኪራይ ብር እንኳን እንዲልኩላት ብትማጸንም” እልክልሻለሁ” ብለዋት በዚያው የቤተሰባቸውን እና የራሳቸውን ስልክ አጥፍተው እንደጠፉባቸው እና እስካሁን ድረስም የት እንደገቡ ለማወቅ እንዳልተቻለ ተናግራለች።
ይህች ግለሰብና ሌሎች ተበዳዮች በሰላሙ ጊዜ አቶ ሀፍቶም የሰጧቸውን ደረቅ ቸክ ይዘው ወደ ባንክ ቢያመሩም ባንኩ በ”ሀፍቶም ኃይሌ” ስም የተመዘገበ የባንክ ሂሳብ ቁጥር ውስጥ ምንም አይነት ገንዘብ እንደሌለው እንዳረጋገጠላቸው ፣ እንዲሁም ሌሎች በውል እና በማስረጃ ለሀፍቶም ገንዘብ ያበደሩ ተበዳዮች ገንዘባቸውን የሚመልሰበት ሁኔታ አስከ አሁን ድረስ እንዳላገኙም ታውቋል።
1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር እንደተጭበረበሩ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሌላ ተበዳይ “የተፈጸመብን አደገኛ የሆነ፣ ተደርጎ የማያውቅ ታሪካዊ ጥፋት ነው።” ሲሉም በደላቸውን ገልጸዋል።
አቶ ሀፎቶም ላይ የቀረበውን ክስ በተመለከተ ፖሊስ የተለያየ አሰሳ እያደረገ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ማግኘት እንዳልቻለ የጠቆሙ የኢትዮጵያ ነገ ታማኝ ምንጮች ግለሰቡ በመቀሌ ተሸሽገዋል የሚል የተለያየ ጥቆማ እየቀረበ መሆኑን ተከትሎ ፖሊስ በቀጣይ ትኩረቱን ወደ እዛ ሊያደርግ እንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

LEAVE A REPLY