“የለውጥ ሃይሎች” ግልፅና ደፋር ውይይት ለመፍትሔና የጋራ ድል! /ኤርሚያስ ለገሰ – ክፍል...

“የለውጥ ሃይሎች” ግልፅና ደፋር ውይይት ለመፍትሔና የጋራ ድል! /ኤርሚያስ ለገሰ – ክፍል 2/

ጆቤ እንኳን ደህና አልመጣችሁ!! ለህዝብ ውይይት መድረክ የተዘጋጀ (ሂውስተን/ቴክሳስ)

የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንና ራዲዮ(ኢሳት) ጥቅምት/2016

ማስታወሻ        

ይህ ጽሁፍ ከራሴ ውጭ የምሰራበትን የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቭዥንና ሬዲዮ (ኢሳት)ን ጨምሮ የማንንም አቋም አያንፀባርቅም።

መግቢያ

“የለውጥ ሃይሎች ግልፅና ደፋር ውይይት ለመፍትሔና የጋራ ድል” በሚል አቢይ ርዕስ ተከታታይ መጣጥፍ እየቀረበ ነው። ከዚህ ቀደም “በክፍል አንድ” በተሰራጨው ጽሁፍ ሁለት ቁምነገሮችን ለመዳሰስ ተሞክሯል። የመጀመሪያው፦ግልጽና ደፋር ውይይት የምናደርግባቸው መሰረታዊ ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ለመዘርዘር ተሞክሯል። ዛሬ አገራችን ያለችበት ሁኔታ የሚያሳስበው ዜጋ ባለመኖሩና አገር አደጋ ላይ በወደቀችበት ሁኔታ በመተማመን ላይ የተመሰረተና የጋራ ድል (win- win) በሚያረጋግጥ መልኩ ምክክር መካሄድ እንዳለበት የተገለጠበት ነው። መጣጥፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የስርአት ለውጥ መምጣት አለበት በማለት የሚንቀሳቀሱት ሁሉም የለውጥ ሃይሎች የዛሬና የነገን ኢትዮጵያ እጣ ፋንታ በሚወስኑ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ምን እንደሚያስቡ ለህዝቡ ማቅረብ እንዳለባቸው የሚጠይቅ ነው።

ሁለተኛው፦ በተከታታይ ለሚቀርቡት ጽሁፎች መነሻ ከተደረጉ አምስት ታሳቢዎች ውስጥ ሦስተኛው ታሳቢ (“የአዲስ አበባ ነዋሪ የስርአት ለውጥ ይፈልጋል። ህዝባዊ ማዕበሉን ለማቀጣጠል ዝግጁነቱ ከፍተኛ ነው”) የሚለው ሃሳብ የተስተናገደበት ነው። ለማስታወስ ያህል “በክፍል አንድ” በቀረበው ጽሁፍ የቀረቡት አምስት ታሳቢዎች የሚከተለውን ይላሉ

ታሳቢ አንድ፦ የህዉሃት አገዛዝ ይወድቃል። የሚወድቀው ግን በከባድ መስዋዕትነት ነው። ከተከፈለው ያልተከፈለው መስዋዕትነት ይበልጣል።

ታሳቢ ሁለት፦ የኢትዮጵያ አንድነት እንደተጠበቀ ይቆያል። የለውጥ ሃይሉ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ አይደራደርም።

ታሳቢ ሦስት፦ የአዲስ አበባ ነዋሪ የስርአት ለውጥ ይፈልጋል። ህዝባዊ ማዕበሉን ለማቀጣጠል ዝግጅነቱ ከፍተኛ ነው።

ታሳቢ አራት፦የለውጥ ሃይሉ ከህወሃት የቀድሞ የጦር ጄነራሎችም ሆነ አመራሮች ብዙ መጠበቅ የለበትም።

ታሳቢ አምስት፦ ከአጭር ጊዜ አኳያ የተገኘው ድል በብስለትና በፅናት ካልተያዘ ሊዳፈን ይችላል።

በመሆኑም በዚህ ጽሁፍ ላይ ለዋናው ሰነድ መነሻ ከሆኑት ውስጥ በ”ታሳቢ አራትነት” የለውጥ ሃይሉ ከህወሃት የቀድሞ የጦር ጄነራሎችም ሆነ አመራሮች ብዙ መጠበቅ የለበትም”) የሚለው ይቀርባል። በመጣጥፍ ሆድ እቃ ውስጥ የትግራይ ኤሊቶች በተለይም የቀድሞ የህዉሃት የጦር መኮንኖች መደ መድረኩ አሁን ለምን እንደመጡ፤ ይዘው የመጡት እጀንዳ ምን እንደሆነ፤ ወደፊት መምጣታቸው የሚያስገኘው ጥቅምና ጉዳት ለውይይት መነሻ በሚሆን መልኩ የቀረበበት ነው። ከዚህም በተጨማሪ ህሃትን ከመገርሰስ አኳያ ዋነኛ የትግል ማዕከሎችና ፓሎች (ምሰሶዎች) የትኛዎቹ እንደሆነ ለማሳየት ይሞክራል።

(“ክፍል አንድ” አግኝታችሁ ማንበብ ያልቻላችሁ ሰዎች በሳተናው፣ ኢትዮ-ሚዲያ ፎረም፣ ዘሃበሻ፣ ህብር-ሬዲዮድረ-ገጾች ላይ ማግኘት ይቻላል።)

(ታሳቢ አራት)

የለውጥ ሃይሉ ከህወሃት የቀድሞ የጦር ጄነራሎችም ሆነ አመራሮች ብዙ መጠበቅ የለበትም።

ላለፉት ሩብ ክፍለ ዘመናት ህዉሃት በብሔር ብሔረሰቦች ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየማለና እየተገዘተ ህዝቡን ለማታለል ብሎም ለመለያየት ቢሞክርም ያሰበውን አላማ ሊያሳካ አልቻለም። ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው በአገራችን የሰላም እጦት ከጫፍ እስከ ጫፍ እየታየ ነው። የስርአት ለውጥና የነፃነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ የትግል ስልቶች ተቀርፀው ወደ ትግባር ተቀይረዋል። እየተደረጉ ያሉት ትግሎች አስተሳስረን ስንመረምር አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ወደ መቃብር የወረደበት ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ በኋላ ህዉሃት መንግስታዊ የበላይነትን ባገኘበት ሁኔታ የምርጫ ፖለቲካ አጀንዳው ተዘግቷል። የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች እንዳሉት በምርጫ ፖለቲካ መቃብር ላይ ጥቁር አበባ ተቀምጦበታል። መቃብር ፈንቅሎ ትንሳኤ ይፈፀም ይሆን ለወደፊት የምናየው ይሆናል። ተስፋ አለኝ።

ከዚህ ጋ ተያይዞ ህዉሃት መራሹ ድርጅት በየጊዜው የሚሰጠው ድርጅታዊ መግለጫና እሱን ተከትሎ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ተስፋ የሚያስቆርጠው የአገሬው ህዝብና የአለም መንግስታትን ብቻ አይደለም። የስርአቱ መስራችና ባለቤት የነበሩ እንዲሁም በተለያየ ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ ስልጣን ላይ የነበሩትን ጭምር ነው። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚዲያዎችን ያጨናነቁት ጄኔራል አበበ እና ጄኔራል ፃድቃን በስርአቱ ምላሽ ላይ ምን ያህል ተስፋ እንደ ቆረጡ መገመት ይቻላል። “የስርአት ችግር ስላለ፣ ኢህአዴግ የተቀባይነት ችግር ስላጋጠመው የስርአት ለውጥ መምጣት አለብት!” ብሎ የተናገረው አንደበታቸውና የከተበው ብዕራቸው ዞር ብለው ሲመለከቱ ማፈራቸው የሚቀር አይደለም። እነ ፃድቃን “ሀገሪቷ የመበታተን አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል” ቢሉም የቀድሞ የትግል ጓዶቻቸውና የስልጣኑ ባለቤቶች “ህገ-መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ስርአት በጽኑ መሰረት ላይ ተገንብቷል” የሚል ዲስኩር ያሰማሉ።

እነ ጆቤ “ህዝቡ በተስፋ እጦት ውስጥ ገብቷል” ብለው ሲፅፉ በተቃራኒው እነ አባይ ፀሀዬ “የአገራችን ህዝቦች በኢትዮጵያ የፈነጠቀውን የልማትና የዲሞክራሲ ጮራ ተማምነው በለመለመ ተስፋ ወደፊት ይመለከታሉ” የሚል ዘመን ተሻጋሪ ማብራሪያ ይሰጣሉ።  እነ ፃድቃን በቀኝ ሆነው የመቶ ፐርሰንት ምርጫ በህዝብ ማላገጥ ነው” በማለት ብዕራቸውን ሲያነሱ በግራ የተሰለፉት እነ በረከት “ኢህአዴግ ስራ በምርጫ ካርድ የተሰጠውን ሃላፊነት አደራ ለመወጣት ቆርጦ ተነስቷል” ይሉናሉ። አራንባና ቆቦ!!

እዚህ ላይ በሁለቱ የቀድሞ የጦር አዛዦችና የህዉሃት መራሹ መንግስት ሃይሎች መካከል በሁሉም ጉዳይ ተቃርኖ ውስጥ እንደገቡ የሚያስብ ካለ በደንብ ተሸውዷል። ሁለቱም ሃይሎች የህዉሃትን ብሎም የትግራይ ህዝብ ጥቅም ይነካል ብለው በገመቱት ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም አላቸው። ከዚህ አንፃር በቅድሚያ ሊነሳ የሚችለው በቀድሞ በትግራይ አስተዳደር ስር ያልነበሩና ዛሬ የተካለሉት ወልቃይትን የመሳሰሉ ቦታዎች ናቸው። የጦር አዛዦቹም ሆነ የህዉሃት ታጋይ ባለስልጣናት መጀመሪያ ሰሞን የወልቃይትና ተመሳሳይ ቦታዎች ፈጽሞ አንዳይነሱ፤ የሚዲያ ትኩረት እንዳያገኙ አድርገው ነበር። በጽሑፎቻቸውም ሆነ በመግለጫዎቻቸው በየትኛውም ቦታ ከመግለጥ ተቆጥበው ነበር። የቅማንትን ጉዳይ አጉልቶ የገለጠው “ጆቤ” ወልቃይት ላይ ሲደርስ የብዕሩ ቀለም በሚያስፎግር ሁኔታ አልቆበት ነበር። በኦሮሚያ ጥያቄዎች ላይ በምናቡ ከፈጠራቸው የኦሮሞ ልጆች ጋር ማውራቱን ሊነግረን የፈለገው ጄነራል አበበ ጠገዴና ጠለምት ፀለምት(ጨለማ) ሆነውበት ግድግዳ ተስታኮና ተንፏቆ ሲያልፋቸው ተመልክተናል።

ሁኔታዎች እየገፋ ሲመጡና የትግሉ ማዕከሉ “ወልቃይት” መሆኑ ሲረጋገጥ እየተንፏቀቁም ቢሆን የወልቃይትን አጀንዳ ማንሳት ጀመሩ። ለምን ከዚህ በፊት ልታነሡት አልሞከራችሁም ሲባሉ “ይሔ ትልቅ ጉዳይ አይደለም። መደረግም አልነበረበትም” የሚል ምላሽ ሰጡ። ቁምነገሩ እዚህ ጋር ነው። ለእነ ጄነራል ፃድቃን የቅማንት ጉዳይ ትልቅ እንደሆነ አድርገው ሊያገኑት ሲሞክሩ የማያቋርጥ የህዝብ ደም እየፈሰሰበት ያለውን ወልቃይት ንቀው እንደተውት ሊያሳዩ ሞከሩ። እነዚህ ሰዎች ይህን ምላሽ ሲሠጡ ወልቃይት “የትግል ማዕከል” እና “የኢፍትሃዊነት ማሳያ” መሆኑን ጠፍቷቸው አይደለም። ልክ አቶ መለስ በኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ወቅት ካድሬዎች “ለምን ባድመን ለመሰለ ቁራሽ መሬት የ10ሺዎች ደም ይፈሳል?” ብለን ሥንጠይቀው እጁን እየጠበጠበ “ባድመ የትግላችን ማዕከል የሆነችው የኢፍትሐዊነት ማሳያ ስለሆነች ነው” በማለት የንዴት ምላሽ ሰጥቷል። በመሆኑም ባድመ የኤርትራ መንግስት በሃይል ስለወሰዳት መጀመሪያ ወደቀድሞው ቦታዋ ትመለስና ህጋዊ ውሳኔ ይሰጥባት እንደተባለ ሁሉ የወልቃይትም ተመሳሳይ ነው። ወልቃይት “ኢፍትሃዊነት ማሳያ” ስለሆነች መጀመሪያ ወደቀድሞው ታሪካዊ ባለቤቷ ትመለስና ሌሎች የህዝብ ጥያቄዎች ቂም በቀል በማይፈጥሩና የጋራ ድል (Win_Win) በሚያረጋግጡ መልኩ ይፈቱ ማለት የአባት ነው። ይገባልም። ይህ ካልሆነ ግን ምንአልባት ከባድመው ባልተናነሰ በ100ሺዎች የሚጠጋ ህይወት የሚወድቅበትና ደም መቃባቱ የሚያባራ ሊሆን ይችላል።

በመቶ ሺዎች ሊገደሉ ይችላሉ የሚለውም ተራ ማስፈራራት አይደለም። ህዉሃት በተለይም የአማራ ተወላጆች ላይ የቋጠረው የቂም ቋጠሮ ከዚህ በላይ ሊገድል እንደሚችል ፍንጭ የሚሰጥ ነው። የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አሰፋ አቢዩ ከሳምንታት በፊት በሰጠው መግለጫ “99 ፐርሰንት ንፁህ ናቸው። እርምጃ የምንወስደው በተቀሩት ላይ ነው” በማለት ይፋ አድርጓል። አሁን ባለው የአማራ ክልል ንቅናቄ ከ5 ሚሊዮን የአማራ ተወላጆች በቀጥተኛ እየተሳተፉ እንደሆነ ዝቅተኛ ግምት ቢወሰድ እንኳን በኮሚሽነር አሰፋ ስሌት መሠረት ከ50 ሺህ በላይ ሠዎች እርምጃ ይወሰድባቸዋል። ህዝባዊ ማዕበሉ እየሰፋ ሲሄድ በአስቸኳይ የስርአት ለውጥ ካልመጣ እርምጃ የሚወሰድበት የአማራ ተወላጅ ሁለትና ሶስት እጥፍ ይሆናል። ስለዚህም፣ ለህዉሃት “የትግል ማዕከል” (centrifugal force) የሆኑትን ቦታዎች አሳልፎ መስጠት መቃብሩን በጥልቀት የመቆፈር ያህል ስለሚመለከተው በጅምላ ከመግደል የሚመለስ አይሆንም።

በእኔ እምነት ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀጣጠለው ህዝባዊ ማዕበል ከህዉሃት ህልውና አንጻር በርካታ ዋልታዎች (Multi- Polar) ያሉት ቢሆንም፣ የዋልታዎቹ ምሰሶ ወልቃይት (Wolqayit Factor) ተደርጎ የሚወሰድ ነው። የኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ኮንሶ የተነሱት እምቢተኝነቶች ትላልቅ ዋልታዎች ቢሆኑም ህዉሃት ልቦና ገዝቶ በህይወት መቆየት ከፈለገ ወደ ምሶሶነት ሳያድጉ በተራዘመ ሂደት ሊያዳፍናቸው ይችላል። ለምሳሌ ህዉሃት ኤርትራ ላይ የሚያስበው (Eritrian-Factor፡ ኤርትራ በጦርነት ማሸነፍና አስመራ ላይ አሻንጉሊት መንግስት መመስረት) ከተሳካና ህዉሃት ኢትዮጵያን መምራት ከተነሳው የኦሮሚያን ጥያቄ እስከ ጫፍ በመውሰድ ምላሽ ሊሰጥበት ይችላል። ይህም በኦሮሞ ጉዳይ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎችንና አክቲቪስቶችን የመከፋፈል እድሉ ሰፊ መሆኑ አይቀርም። ህዉሃት እስከ ጫፍ የሚወስደውን ፍላጎት ለመቀበል አዳዲስ ሃይሎች (Emerging Powers)የሚፈልቁበት ሁኔታ ይፈጠራል። በመሆኑም ህዉሃት በሚቀደው ሀገር የማፍረስ ቦይ የሚፈሱ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆኑ ሰዎች ይኖራሉ። ከሰሞኑ የድል አጥቢያ አርበኛ ሆነው ብቅ ብቅ ማለታቸው አይቀርም። በጅምር ላይ ያለውን የትብብር መንፈስም ውሃ ሊቸልሱበት ይሞክራሉ።

ወደተነሳንበት ስንመለስ ሁለቱ የህዉሃት የቀድሞ ጦር አዛዦች በተለይም ሌ/ጄነራል ፃድቃን ወልቃይትና ሌሎች “የኢፍትሐዊነት ማሳያ” ቦታዎችና “የትግል ማዕከሎች” በተመለከተ ያስቀመጡት ምላሽ ህዝባዊ እምቢተኝነቱን የበለጠ ነዳጅ የሚጨምር ነው። ጄነራል ፃድቃን መጀመሪያ አካባቢ ባቀረባቸው ጽሁፎች በብልጣብልጥነት ሊያልፈው ቢፈልግም ቦታዎች ይበልጥ “የትግሉ ማዕከሎች” መሆናቸውን በህዝባዊ ማዕበሉ ሲመለከት ከድርቅና በተሻገረ አይን አውጣነት ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ እርስ በራስ የተምታታ ምላሽ ሰጠ። ይህ የጦር መኮንኑ ምላሽ የአማራ ህዝብ ትግልና መነቃቃት ከደረሰበት ደረጃ ጋር ፍፁም የማይመጥን ነው። የአሁኑ የአማራ ትግል የደረሰበት ደረጃ ፍልሚያው ተጧጡፎ አድማሱን በመስፋት ቅኝቱ ሙሉ ለሙሉ ተቀይሯል። ከአስር አመት በፊት ሃሰን ዑመር አብደላ በመጣጥፋቸው እንደገለጡት ቅኝትና ምቱ ከተቀየረ እስክታውም መቀየር አለበት። በመሃመድ አህመድ የትዝታ ቅኝትና ምት ጥላሁን ገሠሠን “አንቺን ነው! ሰማሽ ወይ” የሚለው አይደነስም። በ “እምበር ተጋዳላይ” አጨፋፈር ስልት የይሁኔ “ሰከን በል” አይጨፈርም። እንደዚህ ከሆነ በአራዳ ቋንቋ ሽወዳ ይሆናል። አሁን ትግሉ በደረሰበት ደረጃ ደግሞ ውሽልሽል ምክንያት ሸውዶ ማለፍ የሚችልበት ወቅት ላይ አይደለንም። አለበለዚያም እውነት መድፈር ካልተቻለና የሚያስፈራ ከሆነ (ኮንስቲትወንሲያቸውን እንደሚያጡ ይገባኛል) ምላሽ አለመስጠት ይቻል ነበር። ፃድቃን ሊጠቀምበት የፈለገው “የሽወዳ ፖለቲካ” ህዝባዊ እምቢተኝነቱን አቀጣጥሎ መስዋዕትነቱን ከመጨመሩ ባሻገር በሌሎች ያቀረባቸው የመፍትሄ ሃሳቦችም ላይ በጥርጣሬ እንዲታይ ያደረገ ነው።

ለማንኛውም ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ “የትግሉ ማዕከል” በሆነው ወልቃይት ዙሪያ ለአዲስ አድማሱ ጋዜጣ የሰጠውን መግለጫ በመመልከት ፍርዱን እንስጥ። አዲስ አድማስ ጋዜጣ “በሰሜን ጎንደር አካባቢ ያለው ተቃውሞ በተለይ ከ “ወልቃይት አማራነት” ጋር የተያያዘ ነው። የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ጉዳይ በምን አግባብ ነው መፈታት ያለበት?” ለሚለው ጥያቄ የሚከተለውን ምላሽ ሰጥቷል።

“እኔ የወልቃይት ጉዳይ ለአንዳንድ ፖለቲካዊ አላማዎች ሽፋን ነው ብዬ ነው የማምነው። እንዴት ነው የሚፈታው ላልከው እኔ የሚታየኝ ህገ- መንግስቱን መሠረት አድርጎ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ ይሔ ትልቅ ጉዳይ መደረግ አልነበረበትም። ህዉሃትና ብአኤን ተመካክረው መፍታት የሚችሉበት ደረጃ ላይ መድረስ ነበረባቸው።…. በህጋዊ መንገድ ስንሄድም ህገ-መንግስቱን መሰረት አድርጎ መፍታት ያስፈልጋል ነገር ግን ክልሎች በሚወሰኑበት ወቅት ከፍተኛ የፖለቲካ ውሳኔ ሰጪ አካል ውስጥ ነበርኩ። በወቅቱ ቋንቋና የህዝብ አሰፋፈርን መሰረት አድርገን እንወሰን በሚል ነው የወሰነው። በዚህ መሰረት ደግሞ የተወሰነው ተወስኗል።”

አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቀጥሎ የጠየቀው “በወቅቱ ወልቃይት እንዴት ነው ወደ ትግራይ የተላከው?” በማለት ነበር። ሌ/ጄነራሉ እንዲህ በማለት አስገራሚ፣ አሳዛኝና እርስ በራሱ የሚደባደብ ምላሽ ሰጠ።

“አሁን እየጠየከኝ ያለኸው መረጃ ነው። ይሄን መረጃ አሁን አላስታውሰውም። እንደዚህ  ሆኖ ነበር ብዬ ለማለት አልችልም። የተጠቀምንበት አቅጣጫ ግን የፌደራሊዝሙን መነሻ ነው። የህዝቦች ቋንቋና ባህልን መነሻ አድርገን ነው የከለከልነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ እዚያ አካባቢ ያለው አብዛኛው ህዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ነው። ባህሉ የትግራይ ነው። በትግራይ ውስጥ ሊካተት የሚችል ህዝብ ነው። የሆነውም በዚህ አግባብ ነው።”

በመሆኑም እነዚህ የህዉሃት ጦር ጄነራሎች “ህዉሃት አደጋ ላይ መውደቁን ሲያዩ ሊታደጉት መጡ” የሚለውን አባባል ለጊዜው እንተወውና የጎደላቸውን ነገር በጨዋ ቋንቋ እንንገራቸው። በእኔ በኩል  የጦር ጀነራሎቹ ወደፊት መምጣት ቢያንስ በአራት መሰረታዊ ጉዳዮች እደግፈዋለው።

አንደኛው ያልተገለጠ ማንኛውም አስተሳሰብ ስለማይታወቅ መገለጥ አለበት የሚል የፀና እምነት አለኝ። የሉቃስ ወንጌል (መዕራፍ 6 ቁጥር 45) በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራል።….. ክፉ ሰውም ከልቡ ክፉ መዝገብ ክፉ ውን ያወጣል። መልካም ሰውም ከመልካም መዝገብ መልካም ያወጣል” አንዲል አንደበታቸውና ብዕራቸው የተፋው ቁምነገር ከየትኛው ልብ እንደመነጨ ማወቅ የሚጠቅም እንጂ ጉዳት የሚያደርስ አይደለም።

ሁለተኛው ምክንያት እነዚህ የህዉሃት የጦር ጄኔራሎች የቀድሞ ድርጅታቸው ምን ያህል ኋላቀር፣ ለለውጥ ዝግጁ ያልሆነ ግትረኛ፣ ፈሪ ድንጉጥ እንደሆነ በቀላሉ መረዳት ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። እንደጠበኩት በጥቂት ቀናት ውስጥ በህዉሃት ስፖንሰርነት የሚንቀሳቀሱት የውጭ ድረ-ገጾቻቸው ዘመቻቸውን በተጠናከረ መንገድ ከፈቱ። የአየር ሃይል አዛዥ የነበረውን አበበ ተ/ሃይማኖት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት የአውሮፕላን ግዥ ላይ ፈፀመ ያሉትን ሌብነት እየጠቀሱ  ወረዱበት። “የፈፀምከውን ሌብነት ዝም ስንልህ የረሳነው መሰለህ እንዴ?” በሚል ማስፈራራቱን ቀጠሉ። ጄኔራል ፃድቃንን ደግሞ “የስልጣን ፍላጎት የቀፈቀፈው ሃሳብ” በማለት አብጠለጠሉት። ይባስ ብለው በኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስም ባወጡት ድርጅታዊ መግለጫ የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም የህይወት መለኩ (መንፈሳዊንንም ይጨምራል) ከፍተኛ ለውጥ እንዳመጣ፣ ህገ-መንግስታዊ ስርአቱ ጠንካራ መሠረት ላይ እንደተጣለ፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ (100%) አሽንፈው የመንግስት ስልጣን እንደተቆጣጠሩ፣ ባለሁለት አሀዝ ተከታታይ እድገት አምጥተናል….ወዘተ የሚሉ አስደንጋጭ ቃላትን በመጠቀም የጦር መኮንኖችን ቆሌ ገፈፋ።

ሦስተኛው ምክንያት የህዉሃት የጦር ጄነራሎች የሚያቀነቅኑት ሃሳብ ምን ያህል የአገራችንን ችግሮች በጥልቀት ይዳሳሳል፤ ምን ያህል ተቀባይነት ይኖረዋል፤ ከመንግስትና የለውጥ ሃይሎች ፍላጎት አንፃር የተቃኘ ነወይ፤ የደበቋቸውና ለህዝብ ይፋ ቢደረግ ራሳቸውንም ሆነ የቀድሞ ድርጅታቸውን ተጠያቂ የሚያደርግ ነገር ይገልጡ ይሆን ወይ?….. ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች ምላሽ ያገኛሉ በሚል ነው። በግሌ የጠበኳትን አግኝቻለሁ። መኮንኖች የስርአቱ ችግር አለ መፍትሄው ስርአታዊ (systemic) መሆን አለበት ብለዋል። እርግጥ መፍትሄው አሁን ባለው የህዉሃት/ኢህአዴግ ህገ-መንግስት ማዕቀፍ ስር መሆን እንዳለበት ያስገነዝባሉ። አሁን ባለው ህገ- መንግስት እንዴት አድርጎ ስርአታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደሚቻል እንቆቅልሽ ቢሆንም  እንደ ሃሳብ መነሳቱ የሚያበረታታ ነው። በተለይ ህዉሃት አሁን ከዚያው አቋም ሲነፃፀር ምን ያህል የሰማይና ምድር ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ይቻላል። ሰሞኑን አቶ በረከት የኤፈርት ኩባንያ ንብረት የሆነው ሬዲዮ ፋና በጠራው ኮንፈረንስ ላይ አይኑን በጨው አጥቦ “18 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መክረው የተጻፈ ህገ-መንግስት፣ በአለም ላይ ካሉ ጥቂት ምርጥ ህገ- መንግስቶች አንዱ የሆነ” በማለት ዲስኩር ሲያሰማ እንደነበር ለሁሉም ግልጽ ነው። ህገ-መንግስታዊ ፍርድቤት የሌለው፤ ፍርዱን የሚሰጡት እነ አባዱላ፣ ሙክታር አህመድ፣ አባይ ወልዱ፣ ገዱ አንዳርጋቸው…… ወዘተ የሆኑበት ህገ-መንግስት ምርጥነትን ለመናገር በበረከት የአስተሳሰብ ደረጃ ዝቅ ማለት ይጠይቃል።

አራተኛው ምክንያት፡ የህዉሃት የጦር መኮንኖች በአንዳንድ የለውጥ ሃይሎችና በአለም አቀፍ ተቋማትና ሀገሮች ያለው ግንዛቤ በጣም አደገኛ መሆኑ ላይ ነው፡፤ እነዚህ ግለሰቦችና ተቋማት የጦር መኮንኖች የውስጥ አዋቂ አድርገው ስለሚቆጥሩ እንደ ዋነኛ የመፍትሄ አካል አድርገው የሚወስዱበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ይታያል። ይህ አረዳድ በጣም አደገኛ ከመሆኑም ባሻገር የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ወደኋላ የሚመልስበት እድል ሰፊ ነው።የም ዕራብ ሐገሮች በተለይም ሰሜን አሜሪካ (ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት) በተለያዩ ጊዜያቶች ህዉሃት አደጋ ውስጥ ሲወድቅ እነዚህን የጦር መኮንኖች እንደ አማራጭ የሚያማትሩበት ሁኔታ መኖሩ የሚታወቅ ነው። በምርጫ 97 ማግስት (አቶ በረከት ስምኦን ያጫወተኝ ስለሆነ በከፊል እመኑኝ) የቅንጅት አመራሮች ከአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መ/ቤት ጋር በሚወያዩ ሰዓት ጄኔራል ፃድቃን ገ/ተንሳይ እንዲያካትቱ ጠይቀዋቸው እንደነበረ በንዴት ውስጥ ሆኖ አውግቶኛል። ይሄ የበረከት አገላለጥ እውነት ይሁን ውሸት ታሪክ የሚገልጠው ቢሆንም ዊክሊክስን ያገላበጠና የአሜሪካ ኤምባሲ ከቀድሞ የህዉሃት አመራሮች ጋር ያደረጉትን ሚስጥራዊ ውይይት ለተመለከተ አሜሪካኖቹ የሚይዙት የተሳሳተ አመለካከት እንደሚኖር መገመት ይቻላል።

አንዳንድ የለውጥ ሃይሎች ነን የሚሉና አለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት የጦር መኮንኖቹን እንደዋና መፍትሄ የሚወስዱ ከሆነ በጣም አደገኛ ሁኔታ የሚፈጥርበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የህዉሃት የጦር መኮንኖች ህዉሃት የኢህአዴግ የፖለቲካ አስኳል መሆኑን ሌሎች የኢትዮጵያ ማህበረሰቦችና የውጭ ሃይሎች እንዲያውቁ አይፈልጉም። ጄኔራሎቹ በጠመንጃ፣ በደህንነት፣ በኢኮኖሚና ፖለቲካ የበላይነት የአገሩ ባለቤት የሆነውን የትግራይ ነፃ አውጪ (ህዉሃት) ወደ ጎን ትተው የህይወት እስትንፋስ የሌለውን ኢህአዴግ እንደ መፍትሄ አመንጪና ተጠያቂ አድርገው ያቀርባሉ። ለስሙ ቦታውን የያዙትንና አንዳችም ስልጣን የሌላቸውን ከህዉሃት ውጪ ያሉ ባለስልጣናትን ከፍ ከፍ በማድረግ የተለየ ምስል ለመፍጠር ጥረት ያደርጋሉ። በተለይም የአየር ሃይል አዛዥ የነበረው ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት በሙት መንፈስ የሚመራውን ሃይለማርያም ደሳለኝ ብዕሩን ባነሳ ቁጥር ሲያንቆለጳጵስና ሲያሞካሽ ማየት የተለመደ ሆኗል። “ይድረስ ለክቡር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝየጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ” የሚል ርዕስ በመጠቀም “ለሰራዊቱ ግንባታ የተዘጋጀው መጽሀፍ አግዱልኝ!” በማለት ተማፅኖ ሲያቀርብ ይስተዋላል። ጀቤ ይሄን የሚያደርገው የሃይለማሪያምን “የህዉሃት ትሮይ ፈረስነት” አጥቶት አይደለም። ኢህአዴግ የሚባለው አደረጃጀት ለህዉሃት ጭምብልነት የተፈጠረ መሆኑን ዛሬም የሚመራበት መርሆ በጫካ የተቀረፀና ከዘመኑ ጋር የማይሄድ፤ ሸረሪት የሚሯሯጥበትና ያደረበት መሆኑን ጠንቅቀው ያውቃሉ።

ከጄኔራል ፃድቃን አስተያየት ሳልወጣ አድናቆቴን መግለጽ የምፈልግበት አንድ አረፍተ ነገር አለ። ጄኔራሉ በሌሎች የህዉሃት ታጋዮች ባልተለመደ መልኩ አሁን ያለውን ሁኔታ ሲገመግሙ “የትግራይ ህዝብ በተለይም በከተሞች አካባቢ በሌሎች ማህበረሰቦች የመገለል ሁኔታ አጋጥሞታል። መተማመኛውንም የስልጣን የበላይነት አስጠብቆ ማቆየትና በመከላከያና ሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ተከልሎ መኖር” እንደሆነ ገልጧል። ይሄንን ግምገማ ሙሉ በሙሉ የምቀበለው ነው። ለረጅም ጊዜያቶች ይሄ ችግር እየመጣ እንደሆነ ደጋግመን ስንለፈልፍ በህዉሃት ጎራ ያሉ ሰዎች “ዘረኞች” የሚል ታፔላ ተለጥፎልን ነበር። ዛሬ የጦር መኮንኑ በግላጭ ሲያወጣው በህዉሃት መንደር የተፈጠረ ብዙም መንጫጫት አይታይም። ታዲያ! ጄኔራል ፃድቃን በዚህ ጉዳይ ላይ ይሄን ያህል ርቀት መጓዝ ከቻለ ከጥያቄው ጋር አብረው ለሚነሱት ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ቢሰጥበት እኛንም ከስድብና ውርጅብኝ ያድነናል። ጥያቄው የትግራይ ህዝብ በተለይ በከተሞች ውስጥ በሌላው ማህበረሰብ እየተገለለ መሄዱ እውነት ሆኖ ሲያበቃ፤ የመገለሉ መንስ ኤና መሰረታዊ ምክንያት ምንድነው? መገለሉስ ከመቼ ጀምሮ የተፈጠረ ነው? ተጠያቂው ማነው?…. ወዘተ የሚሉ ናቸው። ይህንን ቁልፍ ጉዳይ መመለስ ከተቻለ ወደ ቁልፍ መፍትሄው የምንሄድበት መንገድ አልጋ በአልግስ ይሆናል።

ከዚህኛው ክፍል ከመውጣቴ በፊት ሁለቱን የህዉሃት የጦር ጄኔራሎችም ሆነ እነሱን ተከትለው ሃሳባቸውን በሰፊው ተቀብለው ያራመዱ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የቀጣይ እጣፈንታ ምን ሊሆን ይችላል የሚለውን የራስ ግምት አስቀምጬ መሄድ እፈልጋለሁ። ከልምድ ማየት እንደሚቻለው ህዉሃት በአንድ መሰረታዊ ጉዳይ ላይ አቋም ወስዶ መግለጫ እስኪያወጣ ድረስ የቀድሞ አባላቱንም ሆነ በግል ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚንቀሳቀሱ (ሸገር 02) ድርጅቶች ትንሽ ለቀቅ ያለ ሃሳብ የሚያራምዱበት በር ገርበብ ይደረግላቸዋል። የዛን ሰሞን አፋችንን ይዘን በመገረም “በሸገር ካፌ” ላይ ወይዘሮ መዓዛ ብሩና ጓድ አብዱ የጄኔራል ፃድቃንን “የስርአት ለውጥ” አስተሳሰብ ተገቢ እንደሆነ በአድናቆት ሲነግሩን ነበር። እርግጥ የደርግ ዘመን ጥያቄና መልስ ላይ “አብዮታዊ” ማብራሪያ ሲሰጥ የምናውቀው ጓድ አብዱ በእያንዳንዱ ንግግሩ ሟቹ መለስ ዜናዊን ሲያንቆለጳጵስ መደመጥ ብዙዎችን አስገርሟል። በጣት ቆጠራ አልፈው ካልሆነ በስተቀር ጓድ አብዱ ከሰባት ጊዜ በላይ ባደርገው የሟች ጥሪ በስላሴ 24 ሰዓት ቁጭ ብለው መቃብር የሚጠብቁ የህዉሃት ዋርድያዎችን ሳያስበረግግ አይቀርም።

ወደ ገደለው ጉዳያችን ስንመለስ የህዉሃት የቀድሞ ጄኔራሎችም ሆነ እንደ ሸገር ያሉት የሚዲያ ተቋማት ህዉሃት/ኢህአዴግ መግለጫ ካወጣ በኋላ ቀስ በቀስ ወደ ኋላ መንሸራተታቸው የግድ ይሆናል። ያለ አንዳች ጥርጥር ጄኔራሎቹ ወደ አፎታቸው ይገባሉ። ሸገርና ተመሳሳይ ሚዲያዎች ደግሞ ወደ ሰገባቸው። ይህን ማድረግ ካልቻሉ “የአበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም” የሚለው ብሂል ወደተግባር ተገልብጦ ለመመልከት ሩቅ አይሆንም። ለነገሩ ጆቤና ጓድ አብዶ በአክሮባት የሚታሙ ስላልሆነ ካናዳው ለማምለጥ እንደ አቦሸማኔ መሮጣቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።

የትግራይ ኤሊቶች፣ የህዉሃት የቀድሞ የጦር ጄኔራሎችም ሆነ የቀድሞ ታጋይ ባላስልጣናት ከህዉሃት በፍጥነት ተፋተው ለአዲስ የስርአት ለውጥ ዝግጁ የማይሆኑባቸው ሌሎች ተጨማሪ መሰረታዊ ምክንያቶች አሏቸው። ከዚህ ውስጥ የቅድሚያ መስመር የምትይዘው ኤርትራ ናት (Eriteria-Factor)። ህዉሃት ከኢርትራ ጋር የገባበት ጦርነት ፍፃሜ የረጅም ጊዜ የመጠባበቂያ ህልሙን ያጨለመ ነው። ለሁሉም ግልጽ እንደሆነው ከጦርነቱ በፊት ከኤርትራ መንግስት ጋር ለአመታት የተካሄደው ድርድርም ሆነ የጦርነት ውሳኔ የተወሰነው በህውሃት ማዕከላዊ ኮሚቴ ነው። ወደ ጦርነት ከተገባም በኋላ የመሪነቱን ሚና የጨበጡት ህዉሃቶች ናቸው። በጦርነቱ ምክንያት የአገሪቱ ካዝና በተራገፈና ሙጥጥ ባለ ሰዓት መንግስት ከሶስት ቢሊዮን ብር ያላነሰ የተበደረው ከህዉሃት የኢኮኖሚ ኢምፓወ ከሆነው ኤፈርት (ትእምት) ነበር። ለጦርነቱ የሚሆነውን የጦር መሳሪያ (ታንክ፣ ሮኬት፣ ሚሳየል፣ የውጊያ አውሮፕላኖች……) በየአህጉራቱ የተሽከረከሩ የሚገዙት የህዉሃት አመራሮችና የጦር አዛዦች ናቸው።

(በነገራችን ላይ በአውሮፕላን ግዢ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ከነበራቸው የጦር አዛዦች ግንባር ቀደሙን የሚይዘው የቀድሞ አየር ሃይል አዛዥ የነበረው ሜ/ጄኔራል አበበ ተ/ሃይማኖት ነው። አበበ የክፍፍሉ መጀመሪያ ወቅት እንቡር እንቡር ቢልም የአንጃዎቹ መጨረሻ ኩምሽሽ አድርጎታል። “አይተነው ጊዜ ወደሚያደላው” አይነት ባህሪ ያለው አበበ ገልብጦ የመለስን ቡድን ይቅርታ ቢጠይቅም የመለስን የቃሪያ ጥፊ ከማግኘት አልታቀበም። ከአዛዥነቱ በንፋስ ፍጥነት ተባረረ። ከዛ በኋላ ጆቦ በሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከኪሱ በማውጣት አሜሪካን ሀገር ተማረ። በትምህርቱም “የአሰብ ኢትዮጵያዊነት” ተገለጠለት። መገለጡ ቀልብ ይስባልና በኢትዮጵያ አየር ሃይል ላይ በተነው። ጆቤ! ዛሬ በወር 150ሺህ ብር የሚከራይ ቪላ አለው። ያውም በአዱገነት እምብርት! ለ100 አመት ይዞ ቢቆይና ከደሞዙ ሰባራ ሳንቲም ባያወጣ አሁን ያለውን ሀብት ሩብ አይኖረውም። እርግጥ ከርቀት እንደሰማነው ባለቤቱ ብቸኛዋ ሴት ጄኔራል ሆናለች።)

እዚህ ላይ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ውጤት ለህዉሃት የበላይነት መምጣትና የትግራይ ተጠቃሚነት ዋስትና የፈጠረው አደጋ ለህዉሃት መሰንጠቅ መሰረታዊ ምክንያት ቢሆንም ሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች አሉት። እነዚህ አደጋዎች ከህዉሃት አፈጣጠር፣ የዘረጋው ስርአት ባህሪና ውስጠ- ድርጅት ሁኔታ ጋር የተያያዘ ነው። ህውሃት የበላይነቱን ያረጋገጠባት ኢትዮጵያ ካልቀጠለችና የአገር መበተን ካጋጠመ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ነፃ ሀገር ፈጥሮ መኖር እንደ መጨረሻ ግብ ያስቀመጠ ቢሆንም ከኤርትራ ጋር የገባበት ቁርሾና ደም መፋሰስ ይህን ፍላጎቱን ከሞላ ጎደል ዝግ አድርጎታል። Eriteria-Factor የተባለው አንዱ ገፅታ ይሄ ነው። የጎንደር፣ አፋር፣ ወሎ ህዝብ ከታች ኤርትራ ከላይ ሆነው ትግራይን ሳንድዊች የሚያደርጉበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ከዚህ በኋላ “የትግራይ ሪፐብሊክ” ከህልም የዘለለ አይሆንም። ትግራይን ገንጥለን በሰላም እንኖራለን የሚባል ህልም ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣……ወዘተ ወደ ትግራይ የተከለሉ ሰአትና የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በተነሳ ሰአት ወደ መቃብር ወርዷል።

የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት አጨራረስ በአንድ በኩል ነፃ ሀገር ለመመስረት ህልም የነበረችውን የህዉሃት አመራሮች ወሽመጥ የቆረጠ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ ለሚፈልገው የትግራይ ህዝብ ትልቅ ብስራት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። በአጭሩ ኢትዮጵያን ወዳድ ለሆነው የትግራይ ህዝብ የጦርነቱ አጨራረስ በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ የሚፈጠር ጥሩ አጋጣሚ ነው። Blessing in disguise!!

የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት አጨራረስ ህዉሃትን ለሁለት ሰንጥቋል የሚባልበት መሰረታዊ ምክንያት ይሄ ነው። የስዬ አብርሃ ቡድን የኢትዮጵያን ህዝብ ሀብትና ደም መከታ አድርጎ ኤርትራ በመደምሰስ አሻንጉሊት መንግስት ለመመስረት ሲያስብ ሌሎች አላማዎችን ለማሳካትም ጭምር ነበር። ህዳጣኑ ህዉሃት ከትግራይ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መግዛት ካቃተውና ህዝባዊ ማዕበሉ ካናወጠው ያለ ኤርትራ ስጋት “ነፃ የትግራይ ሪፐብሊክ” መመስረት ይችላል። የስዬ ቡድን ኤርትራ ላይ ለራሱ ተጠሪ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት መመስረት አለመቻሉ በክፉ ጊዜ መጠጊያ የምትሆነውን “ሪፐብሊክ ትግራይ” የመመስረት ራዕይ ተጨናገፈበት። በተለይ በአሁን ሰዓት የኢትዮጵያ ህዝብ ልጆቹን በመገብሩ ቁጭት ላይ የወደቀ መሆኑና ከዚህ በኋላ ጋሻነቱ ባከተመበት ሁኔታ ከኤርትራ ጋር ጦርነት መግጠም ማለት የህዉሃት ፍፃሜ መሆኑ አይቀርም። በሌላ በኩል ጓድ መለስ በስልጣን ለመቆየት ካለው ጥማት በመነሳት ጦርነቱ ሊገፋበት አለመቻሉ እዛው ሳለ የትግራይን ነፃ መንግስት ህልም ባጭሩ የቀጨ ሆኗል። ይህ በመሆኑ ምክንያት በህዉሃት/ኤህአዴግ ህገ-መንግስት ውስጥ የሰፈረው አንቀጽ 39 ከህዉሃትና ትግራይ ህዝብ አኳያ ከወረቀት አንበሳነት የዘለለ አይሆንም። የህዉሃት አፈጣጠር መነሻ የሆነው “የትግራይ ነፃ ሪፐብሊክ” መመስረት እውን ሊሆን የሚችለው ሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ሲሟሉ ብቻ ነው። አንደኛው ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት….. የመሳሰሉ መሬቶችን ለባለቤታቸው ሲመልሱ ይሆናል። ሁለተኛው ኤርትራ ላይ (Eriteria-Factor) ዳግም ጦርነት በመክፈትና ኤርትራን ወደ ዳግም ሱማሊያ መውሰድ፤ ከተቻለም ለህዉሃት ተጠሪ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት በመመስረት በተራዘመ ጊዜ በኮንፌደሬሽን መዋሃድ። የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ሌሎች ቀድሞ በትግራይ ክልል ያልነበሩ ቦታዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ይመለሳል የሚለው ጥያቄ “በህዉሃት መቃብር” ላይ ብቻ የሚፈፀም ነው። ለዚህም ነው ከየትኛውም የኢትዮጵያ ቦታዎች በበለጠ ሁኔታ እነዚህ አካባቢዎች “የትግሉ  ማዕከል” ናቸው የተባለበት ምክንያት። ኤርትራን በጦር ገጥሞ ለህዉሃት ተገዢ የሆነ አሻንጉሊት መንግስት በአስመራ እናቋቁማለን የሚለውም ፍላጎት ያስቀና የደቀቀ ተደርጎ ባይወሰድም ወደ ዜሮ የቀረበ እድል (Probability) ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው።

እርግጥ ሌሎች ህዉሃትን ለሁለት የሰነጠቁ እንጭፍጫፊ ምክንያቶች እዚህ ላይ ሊጨመሩ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ እሙን ነው። የህዉሃት የፍጥረቱ የመጨረሻ ግብ ከመኮላሸቱ ጎ ለጎን የዘረጋው ስርአት ባህሪና የውስጠ- ድርጅቱ ሁኔታ ለመሰነጣጠቁ ምክንያት ነው። ህውሃት የዘረጋው ስርአት የፓርቲውን የበላይነትና የትግራይን የተለየ ተጠቃሚነት ዝርፊያ (ሙስና) አንዱ መለያ ባህሪው ነው። መንግስት እንደመሆኑ መጠን ወረራና ዝርፊያው “መንግስታዊ” መሆኑ አይቀርም። “መንግስታዊ ሌብነት”…. “መንግስታዊ ዝርፊያ”…. “መንግስታዊ ሙስና”…. “መንግስታዊ ውንብድና!”…. በመሆኑም የህዉሃት አንዱ መሰረታዊ መለያ ባህሪ በአዋጅ፣ በህግ፣ በመመሪያ የሚፈፅም የቡድን ዝርፊያ (“መንግስታዊ ሙስና”) ነው። ህዉሃት ገና ከጠዋቱ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ የመንግስትና ድርጅታዊ የስልጣን ቦታዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለው በዚህ ምክንያት ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ውጭ ጉዳይ፣ መከላከያ፣ ደህንነት፣ ፖሊስ፣ ሚዲያ፣ የድርጅት ቢሮ፣ የክልሎች ሞግዚት በመሆን አይናቸውን በጨው ያጠቡት ለዚህ ነው።

ይህም ሆኖ የህዉሃት ስርአት በትግራይ ህዝብና ልሂቃን ዘንድ ያለው አረዳድ ከሌላው አካባቢ ጋር ተመሳሳይ አይደለም። አሁን ባለው ነባራዊ እውነታ ከትግራይ ህዝብ የወጡት ህዉሓቶች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት፤ ገዳዩ አሳሪው ገራፊውና መርማሪው እነሱ በሆኑበት፤ የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም በገነቡበት፤ በትግራይ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅና ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እልፍ አእላፍ ፋብሪካና የኢኮኖሚ አውታሮች በተገነቡበት፤ በጠብታ ኢኮኖሚ መልኩ በትግራይ ክልል የተገነቡት፤ መሰረተ ልማቶችና ማህበራዊ ፍትህ ማምጫ ተቋማት….. ወዘተ በፍጥነት ወደ ህዝባዊ እምቢተኝነቱ ሊቀላቀላቸው አይችልም። ራሳችንን ማምሸት ካልፈለግን በስተቀር የትግራይ ህዝብ በህዉሃት አገዛዝና አፈና ተማሮ ሊሆን ይችላል እንጂ “አዲስ ስርአት” ለመቀበል ዝግጁነቱ አይታይም። የህዉሃት አገዛዝ በፓርቲ መዋቅሩ አማካኝነት የሚፈጥረው ጭቆና፣ የዘመድ አዝማድ አድሎአዊ አሰራር፣ ኋላቀርነት፣ “አህያ ቢራገጥ” የሚመስል አይነት ቂም በቀል፣… አሰልቺ ስብሰባዎች እና መዋጮ….. ወዘተ የትግራይን ህዝብ ሊያስመረምረው ይዝል ይሆናል እንጂ ለስር-ነቀል ለውጥ የተዘጋጀ አይደለም። ግፋ ቢል ከአጭር ጊዜ አኳያ “ላም እሳት ወለደች” ከሚለው ብሂል የሚርቅ አይደለም። ይህ የብዙሃኑ የትግራይ ተወላጅ ፍላጎት አድርገን ልንወስደው የምንችል ነው።

LEAVE A REPLY