በገዛ ዳቦዬ… /አስፋ ጫቦ/

በገዛ ዳቦዬ… /አስፋ ጫቦ/

ዛሬ በሌላ ሰበብ በጨረፍታም ቢሆን ለማየትና ለማሳየት የምሞክረው አሜሪካ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በንግዱ ዘረፍ ተሳታፊነት ነው።ዲያስፖራ አላልኩም!ቃሉን ስለማልወደው ነው! ሌላ ቀን እንወያይበታለን!

ገና አሜሪካ እንደመጣሁ 1984(1992) ፣በፊት የሚያውቁኝና አዲስ ያወቁኝም አሜሪካኖች ዋሺንግቶን ዲ ሲ ፤ጆርጅ ታዎን(Goergetown) በሚባለው የሀብታሞች መንደር፤ አበሻ ምግብ ቤት ምሳ ጋበዙኝ።በጫወታችን መካከል በእንግድነቴ በዞርኩበት ስለኢትዮጵያውያን የታዘብኩትንና ያለኝን አስተያየት ሰጠህ። ወረዱብኝ! በተለይም ዲን ጀምስ ፖል(James Paul) ወረዱብኝ።”አንደኛ እንደህግ ባለሙያ አልተናገርክም! በቂ መስረጃ ሳትይዝ ወደድምዳሜ ተሸጋገርክ! ሁለተኛምና እዚህ ያሉትን ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያውያን ባህርይ ልብ አላልክም።ኢትዮጵያዊው በተፈጥሮ ልታይ ልታይ የማይል (Low Profile)ሕዝብ ነው። እንጅ ለመሆኑ ከአፍሪቃ የትኛው አገር ነው ቤተክርስቲያናት፤ መስጊዶች፤ የባህል ማእከሎች(Community Centers) ፤የምግብና ሌሎች አገራቸውን ነክ የሆነ ነገር ያዘጋጄና ያደራጀ በከፍተኛ ሥልጣንና በየዪኒቨርስቲዎቹ …”ይቅርታ ብጤ ጠይቄ ተለያየን። ከዚያ ወዲህ የበለጠ ልብ እንድል ረድቶኛል

***

የዛሬ ወር ገደማ ይመስለኛል የትራምፕን የአሜሪካንን ፕሬዚደንት ምርጫ ማሸነፍ ሰበብ ሆኖ “በማግስቱ!” የሚል ጽፌ ነበር። ማሕበራዊ ገጽ (Facebook)ና ድህረገጻት (Online) ሁሉ ለጥፌው ነበር። አዲሳባ አዲስ አድማስም ላይ ወቷል።እንዳሉኝ ከሆነ ቁጥር ስፍር ያሌለው ሰው ማንበበ፣ አስተያየት መስጠት ብቻ ሳይሆን አዳርስውታልም (Share)።ደስ አለኝ!” የውለዱትን ሲስሙለት የደገሱትን ሲበሉለት!” እንደሚባለው መሆኑ ነው።፣”በማግስቱ!” መዝጊያው ላይ አንዳንድ ስለ አሜሪካን የምታዘባቸውን አልፎ አልፎ ማቅረብ እሞክራለህ ብዬ ነበር። ይኸ ያ መሆኑ ነው! የትራምፕን መመረጥ ጥቁር አሜሪካውያን Afirican Americans) እንዴት እንዳዩት በጨረፍታ ለማየትና ለማሳየት ሙከራ መሆኑ ነው ።

የዛሬ አመት ይሁን እንዲያ ሌላ የጻፍኩትም ነበረኝ። ሙሉ ለሙሉ አላስታውሰውም። የማስታውሰውን ያክል ካለሁበት ከዳላስ ወደዋሽንግቶን ዲ.ስ ለመብረር ዳላስ Love Field Airport አውሮላን ማረፊያ ሄደኩ። ፈታሹ የያዝኩትን ቡና “ድፋው!” አለኝና ደፋሁት። የሚጠጣ ነገር የታሸገም ቢሆን አውሮፕላን ይዞ መውጣት ከተከለከለ ቆይቷል። ለወዳጆቼ ይሆናል ብዬ የገዛሁትን ዊስኪና የወይን ጠጅ “ወይ ጠጣው ወይድፋው!”አለኝ።ሰጠሁት እንጅ አልደፋትም! የጸጥታው ጉዳይ ነው። በዛሬው ዘመን ፈንጂ ምን ማን መስሎ እንደሚመጣ አይታውቅምና! “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ!” የሚሉት አይነት መሆኑ ነው።

እኔ አውሮላን መብረርረ ይስለቸኛል! ረዥም ሰአታት ቁጭ የሚያሰኝም በረራ አውቃለሁ። ከዳላስ ዋሽንግቶን ዲ.ሲ 3 ሰአት ከሩብ ነው። ቢሆንም የሰለቸኛልና ጋዜጦች፤መጽሐፍት ቡና ይዤ ተሳፍሬ አባብለዋለሁ። አውሮላንኑ ላይ የሚሰጠውን ነጻ ቡናና ቁራሳ- ቁርስ(Snack) አለወደውም።የለበጣና የይስሙላ ይመስለኛልና!የአሁኑን አላውቅም እንጅ ለአለም አቀፍ በረራ የኢትዮጵያ አየር መንገድና የጀርመን አየር መንገድ የመስለ የለም።የአገር ውስጥ በረራ ሁሌም፤የትም የማስተናገዱ ደረጃው ዝቅ ይላል።

ስለዚህም ቡናና ቁርሳ- ቁርስ(Snack) ለመግዛት አውሮፕላን ማረፈፊያ አዳርሽ(Terminal) ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስል ብዙ ኢትዮጵያዊያንን አየሁ።አሁን አቡነ ባርናባስ የሆኑት አባ ወለደትናሳኤ አንዴ ሎስ አንጀለስ (Los Angeles) ጫዋታ ላይ “አቶ አስፋ እባክዎ ይተውኝ! አበሻን እንኳንስ ፊቱን አይቼ ከማጅራቱም ቢሆን እለየላሁ!” ያሉኝ አስታወሰኝ። አንዳንድ ኢትዮጵያውያ እንግሊዚኛውን በቅጡ የማይችሉ በአማርኛ ሲያናግሯቸው በእንግሊዚኛ የሚመልሱትን አንስተን ስንጫወት ነበር። አሁን ይህንን የነሳሁት ኢትዮጵያዊውንና ብዛቱን ለመለየት ችግር አልነበረብኝም ለማለት ነው።

ቡና ፍለጋ የገባሁበት አንዲት ወደወጣትነት የምታደላ ልጅ አገኘሁና “አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ!” አልኳት። ይህንን እዚህ አሜሪካኖቹ “ትንሽ ጫዋታ”(Small Talk) ብለው የሚጠሩት አይነት መሆኑ ነው። በአብዛኛው ፈርንጆቹ ዘው ብለው ወደፍሬ ሐሳብና ወደሚያከራክርና ወደሚያወያይ ጉዳይ አይገቡም። ገራ ገሩንና የማያሻማው ላይ ያተኩራሉ። ብዙ ጊዜ የ አየር ጠባይ ተዘውትሮ የዚህ ደንበኛና መደበኛ ርእስ ወይም ስፖርት ነው። አየሩ ባለቤት የሌለው የሁሉም ንብረት ነውና!

ኢትዮጵያዊው፤በአብዛኛው፤ከሰላምታ በኋላ፣” ምን የአገራችን ነገርኮ…!” ብሎ ይጀመራል። ቢያውቅህም! በቅጡ ባያውቅህም!ዛሬ ጥዋት ተገናኝታችህ ከሆነም! “የአገር ፍቅር!” መሆኑ መስለኝ። ቢሆንም ይህን የመሰለ ጉዳይ ቦታ ቦታና ወቅትም የሚፈልግ ይመስለኛል። “ከምንና ስለምን፣ ከማንስ ጋር!” የሚለው አስቀድሞ የሚታወቅና ካደረው ከሰነበተው ቢጀመር የሚሻል ይመስለኛል። ያለበለዚያ የሚገባውን ክብደት ያጣና የለበጣ ያሰመለዋል ብዬ እፈራለህ።የሚያወሩትን ማጣትም ሳይሆን ይቀራል? “ዝም አይነቅዝም !”ጥሩ አማራጭ ይመሰለኛል።መስመር የለቀቅህ መሰለኝ!የኔነገር!

ታዲያ“አንቺ ይህንን አየር ማረፊያ ተቆጣጠርነው አይደለም እንዴ፦” ያልኳት ልጅ “አይ! ገና ነው! ገና ነው!” አለችኝ። ኮስተርና ፍርጥም ብላ!ጥያቄየን እንደዋዛና ለስላምታ በር መከፍቻ እንዳቀርብኩት አልቆጠርችውም። የምታየውንና የሚታያትን እውነት የተናገረች መስለኝ። ከዚህ ተነሰቼ አንድ ለማስረጃነት የሚሆን አቀርባለሁ።

***

7–Eleven የሚባል በአሜሪካ ሁሉ የተዳረስ፤ዛሬ በሌላውም አለም ያለ፤ከብዙ አመታት በፊት ቴክሳስ የተጀመረ ኩባንያ ነው። ሰሙ 7-Eleven መሆኑ በወቅቱ ያ ሱቅ ክፍት የሚሆንበትን ሰአት ማመልከቱ ነው። ከጥዋቱ 1 ሰአት ይከፍትና ማታ በ5 ሰ አት ይዘጋል ለማለት ነው። አሁን ሰአቱ ቀርቶ ሰሙ ብቻ ነው የተረፈው!24 ሰአት ክፍት ነው። እንዲህ አይነት ሱቆችን Convenience Store የሏቸዋል። ትርጉሙ::

Convenience store – Wikipedia – A convenience store is a small retail business that stocks a range of everyday items such as groceries, snack foods, confectionery, soft drinks, tobacco products, over-the-counter drugs, toiletries, newspapers, and magazines.

ዳላስ Dawntown መርካቶ ማለት ነው፤ያለው 7-Eleven አንድ ሲቀር በሙሉ በኢትዮጵያዊያን የሚካሔድ ነው። የሚካሔድ ያልኩትን በኋላ አስረዳለህ።
የዛሬ 3 አመት ገደማ ይመስለኛል የመጀመሪያውን 7-Eleven ያየሁት Gaston and Peak መንገድ ነበር። ቡናና ሲጋር ልገዛ ገብቼ ኢትዮጵያውን ብቻ ሳይ አንዱን ጠየቅኩትን” የኛው ነው!” አለኝ። የቻልኩትን ያክል አመስገንኩ፤አበረታተሁና ወጣሁ። ከዚያ በኋላ ባለፈው ሁለት አመት ነው አራት አዳዲስ 7-Eleven መርካቶ ያየሁት።

የመርካቶው ሲገርመኝ የዛሬ አመት ገደማ የመስለኛል አዲስ የተከፈተውን ቢጫ(Yellow Line) የባቡር መስመር መጨረሻ መቆሚያ ለማየት ተሳፈርኩና Buckner የሚባል መንገድ ደርስኩ። ከመቆሚያው ማዶ አንድ 7-Elevem አየሁና የሆነ ነገር ለማግዛት ሲሔድ ሻጩ ኢትዮጵያዊ ነው። እኔ ለየሁት!እሱ አለየኝም! በአማርኛ ስላምታ ስሰጠው ደነገጠ! ጥቁር አሜርሪካዊ ብለው የሚገመቱኝ አይጠፉም! ብዙ ጊዜ ኢትዮጵያዊ መሆኔ ወዲያውን የማይረዱ ያጋጥሙኛል። ይኸኛው ከዚያ አንዱ ነው። ደስ አለው! ፈነደቀ! እዚያ አካባቢ ብዙ ኢትዮጵያዊ አያዘውትርም መስለኝ። ደጋግሜ እንድመጣም ጋበዘኝ። እቃ ለመግዛት ሳይሆን አገሩን እንዳስታውሰው አይነት መስለኝ። ከወደጎንደር የመጣ መስለኝም።አማርኛውም አስተነጋገዱም ሞቅና ለየት ያለ ነበር።

ዳላስ የተለያዩ ከተሞች አቀፍ (Metropolitan)ከተማ ነው። በአብዛኛዎቹ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶችና ሱቁች አለቡት። በተለይም Park Lane በሚባለው መንገድ ሞቅና ደመቅ ያሉ የኢትዮጵያውያን ምግብ ቤቶችና ሱቆች እንደልብ ናቸው። ይህ በአብዛኛው ኢትዮጵያዎያን በሚሞኖሩበት ከተማ የተለመደ ነው። ተመጋቢው፣ሸማቹ ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳይሆን ፈረንጁንም ይጨምራል። ሎስ አንጀሊስ የነበርኩ ጊዜ፤ መርካቶ፣ የዳዊት ምግብ ቤት፣ፈርንጁ ከአበሻው ጋር መሳ ለመሳ ሲሆንም አይቻለሁ። ሽሮውን፤ጎመኑና የክክ ወጡን ጤናማ ምግብ(Health Food) ሲሉም ሰምቻለሁ። የበለጠጠ ደምቆ ያየሁት በዋሽንግቶን ዲሲ፤ በሜሪላንድ (አገር ማርያም)ና በቨርጂኒያ ነበር። አንድ ቀን ሲለኝ እመለስበታለሁ። አሁን ወደተነሳሁበት ልመለስ።

ይህንን 7-Elevenአይነቱን የንግድ ሥራ ፍራንቻይ (Franchise)ይሉታል። ትርጉሙ ይኸውና።

franchise;an authorization granted by a government or company to an individual or group enabling them to carry out specified commercial activities, e.g., providing a broadcasting service or acting as an agent for a company’s products

ገባ ብለን ብናየው ዘመናዊ ገባርነት መሆኑ መስለኝ። ባለሀበቱ ፣ ኩባኒያው፣ ምን መሸጠ እንዳለበት ዋጋውን ጨምሮ ይነግረውና ይህንንኑ በሱ ፈቃድ ስም እንዲሸጥ ይፈቅድልታል። ፈቃዱን አከራየው ማለት ነው። ለዚያ በስምምነቱ መሠረት ለባለሀብቱ ይገብራል።እሱ(ሷ)ም ድርሻ አላቸው!

ይኸ ነገር ኢትዮጵያም አለ። ይህ ሁሉ ነዳጅ ማደያ፤ የግል የራዲዮና ተሌቪዥን ጣቢያ ፍራንቻይዝ መሆኑ ነው።

ይኸ ሁሉ ሲሆን በአብዛኛው የአሜርሪካ ከተሞች ሱቆቹና ንግዱ የሚካኸደው በፈረንጅ ካልሆነ እነደኢትዮጵያዊው በመጤው ነው። የሚበዙት ላቲኖ የሚባሉ አሜሪካኖች ፤ማለትም የእስፕየን ዝርያ ነን በሚሉት፤ በቻናውያን ፤በፓክስታና ህንድ… ምኑ ተቆጥሮ ነው። “ጥቁሩአሜሪካዊ የለበትም!” ለማለት ነው።

“ለምን፣ስለምን ጥቁር አሜሪካዊ ንግድ ሥራውውስጥ የለበትም?” ጥሩ ጥያቄ ነው! መልሱ የአሜረካን ታሪክ አካል ነው! አብርሐም ሊንክን ተብሎ በሚዘመርለት ፕሬዚዳንታቸው ዘመን “ነጻ ወጡ!”(Emancipation Declaration) ተባለ። ከዚያ በፊት በተለይ ደቡብ ክፍል በጌቶቻቸው መሬት ላይ የሚይርሱ፤የሚኖሩ ነበሩ። “ነጻ ወጣ!” ሲባል ባሪያ አሳዳሪው ከመሬቱ አባረራቸው! ወደከተማ ገቡ! ትምህርት፤ዕውቀት፤የሥራ ልምድ፣ ገንዘብ ሳይኖራቸው መለመላቸውን ነው የተነቀሉት።በዚህም በየከተማው የተረገጠ የተረሳ ጥጋ ጥግ ታጎሩ!ተጠራቀሙ!ጌ ቶ (Ghetto) የሚባለውይህ ነው! አሜሪካ ጥቁሩ አብዛኛው የሚኖረው ጌ ቶ ነው። “ኑሮ ካሉ መቃብር ይሞቃል!”ም የሚባለውንም የሚያሟላ አይመስልም።
የንግድ ስራ አሁን ትምህርት ቤት ተግብቶ የሚማሩት ሙያ ቢሆንም ከትውልድ ትውልድ ለዘመናት የሚተላለፍ ነው። ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያ የነጋዴ ልጅ ቢሆን ባይሆንም ስለንግድ እውቀት አለው። ገቢያ ሲሐድ፤ሲገዛ፤ሲሸጥ ሲለዋወጥ እያየ ነው ያደገው። ስለዚህም ንግድ ሲጀምር የሚጀምረው ከሀ አይደለም። ያ ለዘመናት የተወራረደው አለው።እርሾ ማለትነው! ይህ ለኢትዮጵያ ያልኩት ለቻይናዎቹ፤ ሕንዶቹ፤ ፓክሲታኖቹ ለሌሎች ሁሉ ይስራል። ጥቁር አሜሪካኑ ይህ የትውልድ ወርስና ቅርስ የለውም! ሊጀምር እንኳን ቢል ንግድ የውድድር ጉዳይ ነውና አብረው መወዳደሪያው ሜዳ የተሰለፉት በዘመናት ይቀድሙታልና ከስሮ ይወጣል ማለት ነው።

አሜሪካን ጥቁሮቹ በትግላቸው ያስገኙት (Civil Rights Movement)ብዙ መብቶች አሉ። ይህ እነማርቲን ሉተር ኪንግ የታገሉለትና የሞቱለት! የዚህ ትግል ወጤት ለቁጥረ- አናሳ(Minority) ለሆኑ ዜጌች ለትምህርትም ሆነ ለንግድ የተሻለ እድል በሕግ መድቧል። እነዚህ ከሌላ የመጡት፤ ኢትዮጵያውያኑን ጨመሮ የዚህ የጥቁሩ አሜሪካዊ የትግል ወጤት የሆነውን መብት ተጠቃሚ ናቸው። ቁጥረ-አናሳ (Minority) ናቸውና!! ጥቁር አብዛኛው አልተጠቀበትም!ሊጠቅምበትም አይችልም! ከላይ በገለጽኩት ምክንያት! እርሾው የለውምና!

***

አሁን ወደተሳሁበት ከፊልዋንኛው ነጥብ ልግባ።ይህም የጥቁር አሜሪካኖችና የዶናልድ ትራምፕ ምርጫ መሆኑ ነው። በተለምዶ ጥቁር አሜሪካውያን ዴሞክርቶች ናቸው። ይህም ማለት ሂለሪ ክሊንተንን የደግፋሉና ይመርጣሉእንደማለትነው። በ ው ድ ድ ሩ ወቅት “ጥቆሮቹ በዚህ ምርጫ ትራምፕን ነው የሚደግፉት!”የሚል ዜና አልፎ አልፎ ቢናኝም ለማመን የሚያስቸግር ነበር።

ለማመን የሚያስቸግረው ክሊተን ለጥቁር አድማጮችዋ ያ የተለመደውን ዴሞክራርት ተወዳዳሪ የሚለውን አለች። የተጠናውን! ትራምፕ ግን ግልጽ ነበር። “እኔን ምርጡኝ !ሁሌ ደሞክራት መርጣችህ ያለፈላችህ ነገር የለም! እኔንን ብትመርጡ የምታጡት ነገር የለም! What have You Got to Loose ! ማንም ሆነ ማን ሊያደርግላችህ የሚችለው ነገር የለም! እንደማለት ነው። “ያውበገሌ!: ናችህ !” ማለት ነው:: እውነትም ነው! ስድብም ነው!

ትራምፕ ሌላ ያለው ነገር አለ።” እዚህ የተጠራቀመውን የውጭ ዜጋ በተለይም ሚክሲካኖችን አስወጣና ፤እንዳይገቡም አጥር አጥራለሁ!” አለ። ለጥቁር አሜሪካኖች ያቃጨለው ይህ ነው። ጠራርጎ ሲያሰወጣለን ሥራ እናገኛናለን ነው።

እኔ ብዙ ጥቁር አሜሪካውያን ወዳጆች አሉኝ።አሜሪካዊ ወዳጅ የሚባል ነገር ካለ! ስለዚህም በምርጫውም ውስጥ ከምርጫውም በኋላ እናወራለን።”ለመሆኑ መቼ ነው የምትሔደው?” ይላሉ። “አይ አልሕሔድም ተክሳስ ተሰማምቶኛል” እላለሁ:: “ የለም ወደ አገርህ ማለታችን ነው!” ይላሉ። ከዚያም አጠገባችን ያሉ ሜክስካኖችን ያሙልኛል።” ቆይ ታዘበኝ አሁን ትራምፕ ተመርጧልና በሚመጣው ሳምንት አታገኛቸውም!” ይላሉ። ይኸው ነው። ይህ ለኢትዮያውንም የሚሆን ነው።የደረሱበት አዘቅት ሥረአቱ መሆኑን ትተው “መጤው ነው እንጅ!” ማለታቸው ነው። እውነቱን ከፍተው ለማየት አለማቻል ፤ወይም አለመፈለግ፤ወይም ምርጫ እንደማጣት ነው። “የጨነቀው እርጉዝ ያገባል…!” አይነት መሆኑ ነው።
የሚገርመው ወይም የሚያስቀው ይህ እናስወጣለን የሚሉት መክስኮዊ ይህ ያለበት አገር ፤አሜረካ አገሩ፤ትላንት Spanish American War ,Mexican American War በሚሉት ጦርነት የተወሰደ ነው። ለምሳሌ ተክሳሳን ተክሳስ ብለን የምንጠራው በእንግሊዚኛ ሲሆን ነው። ያለበለዚያ ቴሐስ ነው ::X በስፓኒኛ ሀ ተብሎ ነው የሚነበበው።ከዚህምሌላ የግዛቶቹ ስም፣ካሊፎርኒያ ፤ኔቫዳ፤ ነው መክሲኮ፤ ኮሎራዶ ፤አሪዞና እንዳለ በእስፐይን ቋንቋ ነው።በተለየ ካሊፎርኒያ ከሳን ፍራንሲስኮ እስከ ሳን ዲያጎ ሎስ አንጀለስንጨምሮ ጨምሮ የካቶሊክ ቅዱሳን ስም ነው ፤የካሊፎርኒያ ዋና ከተማ ስም ሳክራሜንቶ(Sacramento) “ቅዱስ ቅርባን” ማለት ነው።

ይህን መነሻ በማድርግ ሰፋ ተደርጎ ከታየ ትልቁ ምስል የሚታይ ይመስለኛል።

“ከኋላ የመጣ ቀንድ አወጣም!”ንም የሚያጣ አይመስለኝም። “በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት!” ማለትም ይኸው ይመስለኛል!

አንድ ቀን ሲመቸኝ ወይም ሲለኝ ስለ “ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ!” እመለስበታለህ

LEAVE A REPLY