የዶ/ር መራራ ከእስር በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየተጠየቀ ነው /ኢትዮጵያ ነገ/

የዶ/ር መራራ ከእስር በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየተጠየቀ ነው /ኢትዮጵያ ነገ/

/Ethiopia Nege/:- ባሳለፍነው ሳምንት ማገባደጃ ከአውሮፓ ህብረት ስብሰባ በኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ማበራሪያ ከሰጡ በኋላ ወደ ሀገራቸው የተመለሱት ኢትዮጵያዊው አንጋፋ የፖለቲካ ሰው ረዳት ፕሮፌስር መረራ ጉዲና ለእስር መዳረግ ውግዘትን በማስከተል ላይ ይገኛል።

በርካታ የአለማቀፍ ተቋማትና ታላላቅ መንግስታትን ጨምሮ መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ በህዝብና በሀገራቸው ጉዳይ ላይ በንቃት የሚሳተፉ ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን እስርና ወከባ በጽኑ እንደሚያወግዙ ይፋ አድርገዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ የዶ/ር መረራ መታሰር በሀገሪቱ እየተደረገ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ የጠቆሙት የህግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑት ሴናተር ክሪስ ኩምስ አሁን ያለውን መንግስት አምባገነን እየሆነ መምጣቱን አስምረውበታል።

በሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ትግል የሚያካሂዱ የተቃዋሚ ድርጅቶችም የፕሮፌሰሩን እስር ከማውገዛቸውም በተጨማሪ ዶ/ር መራራ በሰላማዊ መንገድ መንግስትን ለመለወጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስዋጽኦ ያደረጉና በሽብር ሊከሰሱ ያማይገባ መሆኑን በመመስከር ቃላቸውን ሰጥተውላቸዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር መረራ የታሰሩት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል በሚል እንደታሰሩ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ ዶ/ር ነገሬ ሌንጫ መክሰሳቸው የሚታወስ ሲሆን የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትን ጨምሮ የተለያዩ መንግስታት የዶ/ር መረራን እስር ከማውገዛቸውም በተጨማሪ በአስቸኳይ እንዲፈቱ እየጠየቁ ሲሆን የአሜሪካ መንግስት ረዳት ቃል አቀባይ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን መግለጻቸው አይዘነጋም።

/Ethiopia Nege December 7, 2016/

LEAVE A REPLY