መጨረሻው ወንበር ላይ ‹‹ ሰይጣን ተቀምጧል ›› ! /አሌክስ አብርሃም/

መጨረሻው ወንበር ላይ ‹‹ ሰይጣን ተቀምጧል ›› ! /አሌክስ አብርሃም/

ቆየት ብሏል ….መቐሌ ዩኒቨርስቲ ለአንድ ወርክ ሾፕ ጠርቶን ወደዛው ጎራ ብየ ነበር ….ከተለያዩ ዩኒቨርስቲወች የተሰባሰብን በእድሜም በትምህርትም ወጣት የነበርን ፣ ጎልማሶች እንዲሁም በእድሜም በትምህርትም የገፉ ሙህራን አዳራሹ ውስጥ ነበሩ ! ፈረንጆችም ነበሩ ! አንዳንድ ወረቀቶች በተሰበሰብንበት ጉዳይ ላይ በተለያዩ ምሁራን ቀረቡና በጉዳዩ ላይ ክፍት ውይይት እንዲደረግበት ለተሳታፊው እድል ስለተሰጠ ከተለያዩ አቅጣጨወች ተሳታፊወች የቀረቡትን ወረቀቶች በማድነቅ አስተያየት ተሰጠ! የወረቀት አቅራቢወቹም እውቀት ትጋት እና ጉብዝና ተደነቀ !

አዳራሹ በአንድ አይነት የመደናነቅና የመሞጋገስ ድባብ ተሞልቶ እያለ ድንገት ከኋላ አካባቢ የአንድ ተሳታፊ እጅ ወጣ ! የመድረክ መሪው ፊት ባንዴ ጨፍግጎ እድሉን ከኋላ አካባቢ እጁን ላወጣው ሰው ሰጠ …. ብዙሃኑ ታዳሚ ወደኋላው እየዞረ ተመለከተ አጠገቤ የነበረ አንድ የመቐሌ ዩኒቨርስቲ መምህር ‹ይሄ ሰይጣን ሊበጠብጠው ነው› አለ ! ‹ሰይጣኑ› መናገር ጀመረ ! ከጎኔ የነበረው ሰው እንደፈራው ተናጋሪው አዳራሹ ውስጥ የነበረውን የመደናነቅና የመሞከሻሸት ድባብ አፈር ድቤ አስበላው !

የቀረበውን ወረቀት ሃሳብ አንድ በአንድ እያነሳ ተቸ ይሻላል የሚለውን ሃሳብም አቀረበ ! በከንቱ ደግፈው ሃሳቡን ሲያሞካሹ የነበሩ ምሁራንንም በሃፍረት እስኪሸማቀቁ ልክ ልካቸውን ነገራቸው ! በየንግግሩ መሃል በድፍረቱና ሃሳቦቹን በሚገልፅበት መንገድ አዳራሹ በታፈነ ሳቅ ይሞላ ነበር ! ከዚህ ሰው ንግግር በኋላ እንደአዲስ የጦፈ ክርክር ተነሳ ! ከጎኔ የተቀመጠውን መምህር ‹‹ይሄ ሰው ማነው ›› ስል ጠየኩት …በብስጭት ፊቱ ጨፍግጎ ስሙን እየተፀየፈ ጠራው ‹‹ አብርሃ ደስታ ይባላል በቃ ዋና ስራው ማራበሽ ሰላም ማደፍረስ ነው ›› ሲል አጭር ማብራሪያ ሰጠኝ ፊቱ ላይ ጥላቻና ብስጭት ይንቀለቀል ነበር !

ለሻይ እረፍት እንደወጣን አብርሃ ብቻውን ቁሞ ከሩቁ አየሁት …. በኋላ አንድ መቀሌ ዩኒቨርስቲ የተመደበ ጓደኛየ ሲነግረኝ አብርሃ ደስታ በአካባቢው መሃበረሰብ በተለይ ‹‹በተማረው ›› ክፍል የተገፋ ሰው ነበር ! ጓደኞቹ እሱ ጋር መታየት የሚያመጣባቸውን ጣጣ በመፍራት ሸሽተውታል ….በጣም የተወሰኑ ሰወች ብቻ ናቸው የሚቀርቡት …እንዲህ ወገቡን አስሮ ስለነፃነታቸው የሚከራከርላቸው የአካባቢው ነዋሪወች ሳይቀሩ እንደከሃዲ ነው የሚመለከቱት ! እንደውም በመንገድ ላይ ሲያልፍ ምራቃቸውን ሁሉ የሚተፉበት ግልፍተኛ የህወሃት አድናቂወች ነበሩ ! አንገታቸውን በፍርሃት ደፍተው ምራቃቸውን ሲተፉበት ደረቱን በነፃነት ነፍቶ ያመነበትን ከመናገር ወደኋላ የማይል አብረሃም ደስታ የትግራዩ ጉዱ ካሳ ነው !

ምክንያቱም በአካባቢው ህወሃት ሰወች ተሰብስበው እንደመሰረቱት የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን መላእክት ተሰባስበው እንዳቋቋሙት የፃድቃን መሃበር ነው የሚታየው ! የህወሃት ስብከት ፖሊሲና ህግ ለአካባቢው ህዝብ (ለብዙሃኑ) እንደ ሃይማኖት ቀኖና ነው አይሻርም አይቃወሙትም የማይከሰስ ንጉስ የማይታረስ ሰማይ ነው ! በእርግጥ በጣም አልፎ አልፎ ስህተቱን የሚቃወሙ ይኖራሉ ግን ያን ያህል ቦታ የሚሰጣቸው አይደሉም ! ከዛም በኋላ የታዘብኩት ነገር ህወሃት በጀግንነት ተዋግቶ ፍርሃትን ህዝብ ላይ የዘራ የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን ነው! ያኔ የተማሩና ትልቅ ደረጃ የደረሱ አንዳንድ የህወሃት ደጋፊና አባላት ሳይቀሩ አብረሃ ደስታ ሲናገር ሲስቁ እንዳይታዩ አቀርቅረው ሳቃቸውን ሲያፍኑ ታዝቢያለሁ ! የሚስቁበት እንኳን ነፃነት የሌላቸው እነዛ ሙህራን በተለያዩ ጊዚያት እዚሁ ፌስ ቡክ ላይ ስለነፃነት ሲሰብኩ እየተመለከትኩ ‹በነፃነት› እስቃለሁ !
…..

ከልጅነት እስከእውቀት የህወሃት ታጋዮችን ጀግንነት ታላቅነት ቆራጥነት ሃቀኝነት በተለያየ መንገድ እየተነገረው ያደገ ወጣት …የሌሎች አገዛዞች ጭራቅነት እየተሰበከለት ከሶስት አስርተ አመታት በላይ የኖረ ህዝብ ህወሃትን መቃወምን እንደመናፍቅነት ነው የሚቆጥረው ! አብርሃም ደስታ ደግሞ ቀኖናውን ጥሶ ህወሃትን በመቃወም ‹‹ሃፂያት›› ሰርቷል !! ያውም ህወሃት ተወልዶ የጎረመሰበት ብሎም ለአቅመ መንግስት እስኪደርስ የተደላደለበት ግንባር ላይ ህወሃትን ‹‹ተሳስተሃል›› የሚል ‹‹መናፍቅ ›› ነው !

ያን ቀን እዛ አዳራሽ ውስጥ የሆነውን ነገር ከተመለከትኩ እና ብዙወች እንዴት በጥላቻ ይመለከቱት እንደነበር ከታዘብኩ በኋላ አብርሃም ደስታ የማንንም ጥላቻና ኩርፊያ ሳይፈራ ዘና ብሎ ሃሳባቸውን ውድቅ ሲያደርግበት የነበረበት መንገድ ትዝ ሲለኝ ሰብሳቢወቻችን በብስጭት ሲወራጩና ንግግሩን ሊያስቆሙት አስር ጊዜ ማይክ ሲወግሩ የነበረበትን ጊዜ ሳስታውስ የፖለቲካ አቋሙ ምንም ይሁን ምን ሃሰቡ ልክም ይሁን ስህተት አብረሃም ደስታ የማይናወጥ አቋም ያለው ሰው እንደሆነ አስባለሁ ! እናም ባለፈው በድንጋይ ተወገረ ሲባል እስካሁን አለመወገሩ ነበር የገረመኝ !

እኔ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ተስፋ አለው ብየ የማምን ሰው አይደለሁም ! ቢሆንም ግን አብርሃ ደስታ በተስፋ ቢሱ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ተስፋ ያለው ሰው ይመስለኛል ! ካልታሰረ አልያም በሂወት ከቆየ !
በግሌ የአብርሃን የፖለቲካ አመለካከት ሳይሆን ፅናቱን አደንቃለሁ !! በዛች ቅፅበት ‹‹ፃድቃን ነን›› የሚሉ ምሁራንና የድርጅት አባላት ‹‹መጨረሻ ወንበር በተቀመጠው ሰይጣን ›› ሲደነባበሩ ማየቴ ትዝ የሚለኝ ዛሬም አብርሃ ደስታ ፌስ ቡክ ላይ አንድ ቃል ሲናገር የሚንጫጩትን ውል አልባ ጩኸት እና ስድብ የሚያዘንቡትን ሰወች ስመለከት ነው !
ለማንኛውም የአብርሃ ደስታ አይነት ፅናት ለአንድ የፖለቲካ ሰው ወሳኝ መሳሪያ ነው ….የሚያራምደው የፖለቲካ አቋም ሌላ ነገር ሁኖ !

                             *** ***

እዚሁ ፌስቡክ ላይ ከማውቃቸው ፀሃፍት መካከል ፍፁም ጨዋነትና ፅናት ባልተለያቸው ፍፁም ሰላማዊ ፅሁፎቹ አውቀው ለነበረው አብርሃ ደስታ ዛሬም ከፍ ያለ አክብሮት አለኝ !! አብርሃምን ያከበርኩት ለምንድነው ? አብርሃም ብዙቆች የሚመኙት ስራ የነበረው ሰው ነበር … ግን ስራ ስላጡ የአገሩ ልጆች በየቀኑ ሲጮህ ሰምቻለሁ … አብርሃም ጥይት አልተኮሰም …ግን ከተኳሾች በላይ አስፈሪ ድፍረት ነበረው …አብርሃም ፀያፍ ነገርን ፅፎ አይቸው አላውቅም ..ግን ሁልጊዜም ፀያፍ ስድቦችና ዛቻዎች እዚሁ ፌስቡክ ላይ እንደተሰነዘሩበት ነበር …አብርሃም የሚጮህላቸው ሳይቀሩ አግልለውት ነበር ላገለሉት ሚስኪኖች ግን ‹‹ተገለሉ›› ብሎ ሲከራከር ነበር ….አብርሃም ዛሬ ታስሯል ግን አልቆመም !!

ዛሬ የዚህ ፅኑ ሰው የልደት ቀን ነው …የመልካም ልደት ምኞቴን የማቀርበውም ለዚሁ ትንታግ ፀሃፊና ፖለቲከኛ ነው ! እንዲሁም በወቅቱ የታዘብኩትን ለትውስታ ያህል በድጋሜ ታነቡት ዘንድ ለጠፍኩ ! መልካም ልደት አብርሃም ደስታ !

LEAVE A REPLY