ዝክረ አድዋ /ከጽሀፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ፅሁፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ/

ዝክረ አድዋ /ከጽሀፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ፅሁፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ/

(የአድዋው ጦርነት በወቅቱ የንጉሱ ጸሀፊ ከነበሩት ከጽሀፌ ትዕዛዝ ገብረ ሥላሴ ፅሁፍ ተቀንጭቦ የተወሰደ።)

ንጉሠ ነገስቱ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያን መሳፍንት እና መኳንንት ሹማምንቱንም ባላባቱንም ባጠቃላይ ተዋጊ ጦር በክተት አዋጅ ቀስቅሰው ከአዲስ አበባ ከተነሱ ጀምሮ ከአምባላጌ እስከ መቀሌ ከድል ወደ ድል እየተራመዱ እንደልቡ ፈንጭቶ እስከ አምባላጌ ድረስ ሰፍሮ የነበረውን የጣልያን ጦር እየጠረጉ ወደ አድዋ አካባቢ ነድተውታል። ከዚያም በኋላ ባለው ጊዜ ለዋናው ጦርነት አድዋ ላይ በመሰባሰብ የተለያዩ የውጊያ ዘዴዎችን በመቀየስ እና በመመካከር እንዲሁም ሠራዊቱ ለውጊያ ዝግጁ ሆኖ በተጠንቀቅ ጦርነቱን እንዲጠባበቅ ተደረገ።

. . . ቅዳሜ ማታ የካቲት 22 ቀን አፄ ምኒልክ ቀኝ አዝማች ታፈሰን አስጠርተው እንደዚህ አሉት “ስንቅ ፍለጋ የሄዱት ተዋጊወች ተመልሰው የገቡ እንደሆነ ሰኞ ወደ ሐማሴን እንሄዳለን ሥለዚህ አንተ በሌሊት ተነስተህ ከግምጃ ቤት ጓዝ ወስደህ መተላለፊያችንን እንዳያውኩ በየሰፈሩ የሞቱትን የበቅሎና የፈረስ ሬሳ እያቃጠልክ አጥፋ።” ቀኝ አዝማች ታፈሰም እሺ ብሎ እንደታዘዘው አደረገ። የዚህም ቀን ቃፊር ሆኖ የማስጠበቁ ተራ የራሥ መንገሻ ዮሐንስ ነበር። ሲነጋ ደግሞ የካቲት 23 ቀን የጊዮርጊስ በዓል ነበር. . . .።

. . . . ከሌሊቱ 11 ሰዓት ግድም የጣልያን ጦር በድንገት ደረሰ እና 500 ከሚሆኑት በር ጠባቂ የራስ መንገሻ ዮሐንስ ወታደሮች ጋር ገጠመ። የራስ መንገሻ ወታደሮች ተዋግተው የጠላትን ወታደሮች እንዲሁም ሁለት ባሻ ባዙቃ ማረኩ እና የተማረኩትን ቢጠይቋቸው “ግማሹ የአፄ ምኒልክ ጦር ሥንቅ ፍለጋ መሄዱን ስለ ሰሙ ጣልያኖች በድንገት አደጋ ጥለው ለመዋጋት አራት ጀኔራሎች በአባ ገሪማ በኩል አንደኛው ጀኔራል በማርያም ሸዊቶ በኩል ተሰልፈው ይጓዛሉ” ብለው ተናገሩ። ይኸን ሲሰሙ ከቃፊር ጠባቂዎች አንዱ ወደ ንጉሰ ነገስቱ ሰፈር እየሮጠ ሲሄድ በመንገድ ቀኝ አዝማች ታፈሰን አገኘ እና የያዘውን ወሬ ነገረው። ቀኝ አዝማች ታፈሰም ከበቅሎ ወርዶ እፈረሱ ላይ ተጋባ እና በግልቢያ ወደ ንጉሱ ድንኳን ደረሰ እና ለእልፍኝ ዘበኞቹ ንገሩልኝ አለ . . . አፄ ምኒልክም ከድንኳኑ ወጣ ብለው ምነው ብለው ቢጠይቁት ጣልያኖች አደጋ ለመጣል መምጣታቸውን ተናገረ. . . .።

አፄ ምኒልክ ጣልያኖች ተሰልፈው በጣም ተጠግተው ጦርነቱን ካልጀመሩ በቀር ጦሬን አሰልፌ ሁለተኛ አልወጣም ብለው ስለ ነበረ “በከንቱ አሰልፎ ሊያስወጣኝ ሳይሆን ሊዋጋ የመጣ መሆኑን ታምናለህን?” ብለው ታፈሰን ቢጠይቁት “ዛሬሥ እርግጥ ነው” ብሎ መለሠ። አፄ ምኒልክም ወታደሩ ሁሉ መሳሪያውን ይዞ እንዲነሳ ካዘዙ በኋላ ራሳቸውም የጦር ልብሳቸውን ለበሱ። በዚህ ጊዜ ፀሀይ ወጣች የትግሬ ጦርም ከሌሊቱ 11 ሰዐት ጀምሮ ሳያቋርጥ ይታኮስ ነበር እና ሲነጋ የጠመንጃው ጢስ ይታይ ነበር። የራስ ሚካኤልም ሰዎች ወዲያው ሄደው ወደ ጦርነቱ ተጨመሩ. . . ።

. . . . በዚህም ቀን አገልጋይ ከጌታው ወታደር ካለቃው ተለያዩ እና ሁሉም ነዶ እንዳየ ዝንጀሮ ወደፊቱ ጦርነት እና መድፍ ወዳለበት ለአገሩ ለመሞት ገሠገሠ። ማንም ሰው መድፍ ይመታኛል የጠብ መንጃውም ጥይት ይመታኛል ብሎ በልቡ ፍርሐት ያደረበት የለም። . . . አለቃው ሲወድቅ ወታደር፤ ወንድሙ ሲወድቅም ወንድሙ አያነሳውም። ቁስለኞች ራሳቸው “አገር ይርጋ እንጂ እኔን ስትመለስ ታነሳኛለህ፤ ሥለዚህ እንዳታነሳኝ በመሃይም አንደበቴ ገዝቸሀለሁ” ይሉ ነበር። ጥይቱ ያለቀበት ወታደር ከቆሰለው እና ከሞተው ወገብ ላይ ወስዶ ተኩሱን ይቀጥላል። አንዳንዱም ብዙ እየሮጠ ተዋግቶ ድካም ሲሰማው አረፍ ማለት ይጀምር እና ወዲያው ተነስቶ “ጮማ ላበላኝ ጠጅ ላጠጣኝ ጌታዬ ምኒልክ ብድሩን እንዴት ነው የምመልሰው” እያለ ይደነፋ እና እንደገና ወደ ጦርነቱ ይገባል. . . . ።

. . . . ንጉሱ የሚሸሹ የጣልያን ወታደሮችን እየተከተሉ የሚወጉ ወታደሮቻቸውን እየመሩ ሲሄዱ መጀመሪያ ካገኟቸው የሚበረክቱ በዛ ያሉ ጣልያኖችን አግኝተው ሲዋጉ የተኩሱም መጠን ከፊተኛው የበለጠ ሆነ። በዚያ ላይ የጣልያን ብዙ ወታደሮች ወደቁ የቀሩትም ሸሹ። . . . የኢትዮጵያም ጦር የሚሸሸውን የጣልያን ጦር እየተከተለ የራቀውን በጥይት የቀረበውን በጦርእና በጎራዴ እየመታ ፈጀው። የመጀመሪያው ጦር በተሸነፈ ጊዜ አፄ ምኒልክ ወደፊት እየገፉ ጦር ያነሰበትን ግንባር እየመረመሩ በፍጥነት ጦር እየላኩ ሲያዋጉ ጊዜው 5 ሰዐት ሆነ. . . ።

. . . የንጉሱ አሽከር ሊቀ መኳሥ አባተ ተምሳስ ዣንጥላውን አስይዞ “ውጋ በርታ” የሚለውን ነጋሪቱን ያለማቋረጥ እያስጎሸመ ሲያዋጋ ዋለ። የመጀመሪያው ድል ወደተፈፀመበት ሥፍራ እቴጌይቱ መጥተው ቆመው በእርኮት እና በገንቦ ያለውን ውሀ እና መጠጥ በገረዶች እያስቀዱ ቁስለኞቹ ኢትዮጵያውያን እና ጣልያኖችም እንዲጠጡ እና እንዲረኩ አደረጉ።በዚሁ ቀን ብዙ መነኮሳት የሰሌን ቆባቸውን ደፍተው፣ ካባቸውን ደርበው የቆዳ ቀሚስ ለብሰው ግማሹ ከንጉሱ ነገስቱ ዙሪያ ግማሹ ከእቴጌይቱ ዘንድ የቀሩትም በተዋጊው መኳንንት እና ወታደር ዘንድ ሆነው ወዲያ እና ወዲህ እየተላለፉ ሊዋጋ ወደ ጦርነቱ የሚገባውን እያናዘዙ፤ አንዳንድ ከጦርነቱ ሲሸሽ ያገኙትን ወታደር እየገዘቱ ሲያበረታቱ እና ሲያዋጉ ዋሉ።

. . . በዚህ ታላቅ ጦርነት ሽማግሌው ራስ ወልደ ሚካዔል ሰለሞን የራስ ኃይለ መለኮት አባት ምንም በእድሜ ገፍተው ቢያረጁ የአሽከራቸውን እጅ እንደጨበጡ ይዋጉ ነበር። እንደ እርሳቸውም በእድሜ የገፉት በጀግንነት የሚታወቁት ራስ ደርሶ ምንም እንኳን የጦርነት አዛዥነቱ ወደ ራስ ወርቁ ቢዛወር ከንጉስ ተክለ ሃይማኖት አልለይም ብለው መጥተው ጦርነቱን ተካፍለዋል. . . . . .።

ይቀጥላል…

LEAVE A REPLY