ወያኔ እንዲህ እያሰበ መሆኑ ጭምጭምታ ተሰማ፤ ዕውነት ከሆነ ጥቅምና ጉዳቱ ምን ይሆን?...

ወያኔ እንዲህ እያሰበ መሆኑ ጭምጭምታ ተሰማ፤ ዕውነት ከሆነ ጥቅምና ጉዳቱ ምን ይሆን? /ሞረሽ ወገኔ/

ዛሬ ላለንበት ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትንና ዐማራ የተሰኘውን ነገድ ከመኖር ወደ አለመኖር ያደረሳቸውን ምክንያት መገንዘብ፣ ለምንፈልገው መፍትሔ ጥርጊያ መንገድ ይከፍትልናል። ከትግራይ ነፃ አውጭ ግንባር (የትግሬ-ወያኔ) የትግል ጉዞ እንደምንረዳው፣ ችግር በገጠመው ቁጥር፣ ዓላማውንና ቆሜለታለሁ የሚለውን ሥርዓት እንደ እባብ ገላ በሌላ በመተካት ጊዜ ይገዛል። ከማኦ ዜ ዱንግ እስከ ኤንቨር ሆጃ፣ ከካርል ማርክስ እስከ ሌኒን፣ ከሂትለር እስከ ደቡብ አፍሪቃ የአፓርታይድ አገዛዝ ያሉትን ርዕዮተ-ዓለሞች ካንዱ ወደ ሌላው ከብርሃን ፍጥነት በፈጠነ ሁኔታ በመቀያየር ኅልውናውን ለማራዘም ይሞክራል። የትግሬ-ወያኔ ላለፉት 25 ዓመታት ያራመደው በዘር ጥላቻ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካና አገሪቱንና ሕዝቡን በነገድ ሸንሽኖ ያደረሰው ጥፋት፣ በተለይ ከ2007 እስከ 2009 ዓም ያሉት ዓመታት ሕዝቡ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ስለሆነበት፣ የአገዛዙን የአፈናና የእመቃ መዋቅር በመበጣጠስ በየአቅጣጫው ያስነሳው ተቃውሞ የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ ከሥሩ እያናጋው በመምጣቱ ምክንያት «አልሸሹም ዘወር አሉ» ዓይነት እና፣ «የጥልቅ ተሐድሶው» መገለጫ እንዲሆን የታሰበ የመንግሥት የአደረጃጀት ለውጥ ለማድረግ የታሰበና ወደዚህም ግብ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ በመሰማት ላይ ነው።

በግልጽ እንደሚታወቀው፣ የትግሬ-ወያኔ ዘረኛ አገዛዝ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማፍረስ ሰንቆት ለተጓዘበት ዓላማ ማስፈጸሚያ አድርጎ የተጠቀመው  የመንግሥቱን አደረጃጀት በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሠረተ አፋዊ ፌደራላዊ  አደረጃጀት መከተሉ ነው። በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሠረቱት እነዚህ «የፌደራል መንግሥት አካላት ናችሁ» የተባሉትም በፈለጉትና ባሻቸው ወቅት «መገንጠል እንፈልጋለን» ብለው ባሰቡ ጊዜ መገንጠል እንዲችሉ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39(1) የመገንጠል መብታቸው የተከበረ እንዲሆን ተደንግጓል። በዚህ ሕገ-መንግሥት የፌደራል መንግሥቱ መቀመጫ የሆነ በራሱ የፌደራል መንግሥቱ  ቁጥጥር ሥር የሆነ መዲና የሌለው መሆኑም ይታወቃል። ይህም በመሆኑ በአዲስ አበባ ከተማ የመስፋፋትና የልዩ ልዩ የግንባታ ሥራዎች «በኦሮሚያ መንግሥት ሙሉ ፈቃድ» ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረጉ፣ ለከተማዋ ዕድገት እንቅፋት ከመሆን አልፎ፣ በኦሮሞ ብሔርተኞችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ደም ያፋሰሰ ክስተት መስተናገዱ ይታወሳል። ችግሩም  ዛሬም እልባት ያላገኘ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የትግሬ-ወያኔ «ኦሮሚያ» ብሎ በከለለው አካባቢ የተቀሰቀሰው የሕዝብ እንቢተኝነት ለበርካታ ሰው ሕይዎት ማለፍና በብዙ ሚሊዮን ብር ለሚገመት ንብረት ውድመት መንስዔ መሆኑ አይዘነጋም። በደብረዘይት ከተማ «የእሬቻ» በዓል አከባበር ላይ በግፍ ሆን ተብሎ በተዘጋጀ ሤራ ያለቀውን ሕዝብ ማስታወሱ ብቻ ለዚህ አባባል ከበቂ በላይ ማሳያ ነው።

በኦሮሞ ብሔርተኞች የተቀነቀነውና ለአንድ ዓመት ያህል የዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ፣ የትግሬ-ወያኔን የስለላና የአፈና መዋቅር በመበጣጠስ በአገዛዙ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ በማየሉ፣ አገዛዙ አቅዶት የነበረውን የአዲስ አበባን የማስፋፋት ዕቅድ ለጊዜውም ቢሆን እንዲያቆም ከመገደዱም በላይ፣ በኦሕዴድ የዘመናት አገልጋዮቹ ላይ የመረረ እርምጃ እንዲወስድ አድርጎታል። በሌላ በኩል ለ42 ዓመታት ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው የወልቃይት ጠገዴ የማንነት ጥያቄ የቀሰቀሰው ሕዝባዊ ማዕበል፣ የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ ከምንጊዜውም በላይ ጥያቄ ውስጥ ያስገባው በመሆኑ፣ አገዛዙ ሕገመንግሥቱን አግዶ የአስቸኳይ ወታደራዊ አዋጅ አውጆ፣ አገሪቱን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር አድርጎ፣ «ጠላቴ ነው» ያለውን ሁሉ እንደፈለገ በጠራራ ፀሐይ በማሰርና በመግደል በሕዝቡ ላይ የመከራና የስቃይ ናዳ እያወረደበት ይገኛል። ይኽም ሆኖ፣ ሕዝባዊ እንቢተኝነቱ እየበረታ እንጂ፣ እየላላ ባለመሄዱ፣ የትግሬ-ወያኔ ለጊዜውም ቢሆን ጊዜ መግዣ ይሆነኛል ብሎ ያሰበውና ለ25 ዓመታት አጥልቆት የነበረውን «የማንነቴ መገለጫ ነው» ያለውን የቋንቋ ፌደራሊዝም አውልቆ በክፍለ-ሀገራት ማንነት ላይ የተመሠረት ፌደራላዊ አስተዳደር ለመመሥረት በመዘጋጀት ላይ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ።

እንደመረጃዎቹ አባባል ከሆነ፣ ወያኔ ከገጠመው አጣብቂኝ መውጫ ይሆነኛል ብሎ ያሰበው፣ በዘጠኝ ክልላዊ መንግሥታትና በሁለት የከተሞች አስተዳደር ያዋቀረውን የቋንቋ ፌደራሊዝም ሽሮ፣ በ39 ክፍለ-ሀገሮች የተዋቀረ ፌደራዊ መንግሥት የመተካት ዕቅድ እንዳለው ያመለክታል። በመረጃዎቹ መሠረት ወያኔ ለ26 ዓመታት የድሉ ቁንጮ አድርጎ ይመለከተው የነበረውን የቋንቋ ፌደራሊዝም አፍርሶ፣ «ከእሾህ ወደ ጋሬጣ» ዓይነት የሆነ፣ መነሻውን ቋንቋ ያደረገ፣ ነገር ግን፣ ትግራይ ሲቀር በስተቀር ቀደም ሲል በክልላዊ መንግሥትነት አካቷቸው የነበሩትን ወረዳዎችና አውራጃዎች በሠፈሩባቸው ነገዶች ስም የክፍለ-ሀገር ደረጃ በመስጠት፣ ለበለጠ የርስ በርስ ግጭትና ብጥብጥ፣ አገሪቱንና ሕዝቡን ሊያቋርጥ ወደማይችል ትርምስ ሊከት የሚችል ሁኔታን የሚፈጥር አደረጃጀት የተከተለ እንደሆነ «ክፍለ-ሀገራት» ብሎ የሰየማቸው አካባቢዎች ሁኔታ ያሳያሉ። የትግሬ-ወያኔ ለተነሳበት ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንቅስቃሴ ማብረጃና ለሥልጣን ዕድሜዬ መራዘሚያ ይሆነኛል ብሎ የፈጠራቸው አዲሶች ጠቅላይ ግዛቶች የሚከተሉት ናቸው።

 

ተራ ቁጥር

ከፍለ-ሀገራት

ተራ ቁጥር

ክፍለ-ሀገራት

1

ትግራይ ክፍለ-ሀገር

21

ኢሉባቡር ክፍለ-ሀገር

2

አፋር ክፍለ-ሀገር

22

ሶማሊ ክፍለ-ሀገር

3

ወልቃይት-ጠገዴ-ሑመራ ክፍለ-ሀገር

23

ጋምቤላ ክፍለ-ሀገር

4

ቤጌምድር ክፍለ-ሀገር

24

ቤንሻጉል-ጉምዝ ክፍለ-ሀገር

5

ጭልጋ-መተማ ክፍለ-ሀገር

25

ቤንቺ ማጂ ክፍለ-ሀገር

6

አገው-አዊ ክፍለ-ሀገር

26

ሸካ ክፍለ-ሀገር

7

ጎጃም ክፍለ-ሀገር

27

ከፋ ክፍለ-ሀገር

8

ባሕርዳር ዙሪያ ክፍለ-ሀገር

28

ደዋሮ ክፍለ-ሀገር

9

ባቲ-ሰንበት ክፍለ-ሀገር

29

ኦሞቲክ ክፍለ-ሀገር

10

ወሎ ክፍለ-ሀገር

30

ጋሞጎፋ ክፍለ-ሀገር

11

ሸዋ ዐማራ ክፍለ-ሀገር

31

ኮንሶ ክፍለ-ሀገር

12

ቦረና ክፍለ-ሀገር

32

ሲዳማ ክፍለ-ሀገር

13

አርሲ ክፍለ-ሀገር

33

ጌድዎ ክፍለ-ሀገር

14

ባሌ ክፍለ-ሀገር

34

ጉራጌ ክፍለ-ሀገር

15

ሐረርጌ ክፍለ-ሀገር

35

ስልጢ ክፍለ-ሀገር

16

አዲስ አበባ ዙሪያ ክፍለ-ሀገር

36

ሐዲያ ክፍለ-ሀገር

17

ጉጂ ክፍለ-ሀገር

37

አላባ-ከምባታ-ጠምባሮ ክፍለ-ሀገር

18

ወለጋ ክፍለ-ሀገር

38

ወላይታ ክፍለ-ሀገር

19

ሸዋ ክፍለ-ሀገር

39

ቡርጂ-ዲራሸ-አማሮ ክፍለ-ሀገር

20

ጅማ ክፍለ-ሀገር

 

 

 

ከሰንጠረዡ መገንዘብ እንደምንችለው ክፍለ-ሀገራዊ ክፍፍሉ የተሠመረው ሦስት ነገሮችን መሠረት በማድረግ ነው። እነዚህም ቋንቋ፣ የጥንቱ ክፍለ-ሀገሮች፣ አውራጃና ወረዳዎችን መሠረት ያደረጉ ሆነው እናገኛቸዋለን። አሥራ ስምንቱ(18) ቋንቋን መሠረት አድርገዋል። አሥራ አንዱ(11) የቆዳ ስፋታቸው የጥንቱን ክፍለ-ሀገሮች አያካት እንጂ፣ በስም ደረጃ የጥንቱን ስማቸውን እንዲይዙ ተደርጓል። አሥሩ(10) የጥንቶቹን አውራጃና ወረዳ ስሞች እንዲይዙ ሆነዋል። ይህ አስተዳደራዊ መዋቅር እና አደረጃጀት በዚህ መልክ እንዲሆን አስፈላጊ ያደረጉት ከትግሬ-ወያኔ ዓላማ አኳያ የሚከተሉት እንደሆኑ መገመት ይቻላል።

 

 

  1. የአደረጃጀት ለውጡን አስፈላጊ ያደረገው መሠረታዊ ምክንያት በመላ አገሪቱ ከሁሉም በላይ በጎንደርና በጎጃም ክፍለ-ሀገሮች፣ እንዲሁም የትግሬ-ወያኔ «ኦሮሚያ» ብሎ በከለላቸው ክፍለ-ሀገሮችና አውራጃዎች በተከታታይ የዘለቀው ሕዝባዊ እንቢተኝነት የትግሬ-ወያኔን መንግሥታዊ መዋቅር ሽባ በማድረጉና በትግሬ-ወያኔ ኅልውና ላይ ከፍተኛ አደጋ የጋረጠ ስለሆነ፣ የሕዝባዊ እንቅስቃሴውን አቅጣጫ ለማሳት፣ የተቃዋሚ ቡድኖችን የትኩረት አቅጣጫ ለማዛባት፣ በዚህም ወያኔ እንደ እባብ አፈር ልሶ ራሱን መልሶ የሚያጠናክርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ነው።
  2. በቋንቋ መነሻነት የተካለሉት አሁን የሚታወቁት ክልሎች በሕዝብ ብዛት እና በተለያዩ በተፈጥሮ ሀብቶች ከትግራይ ስለሚበልጡ፣ በሕዝብ ተወካዮች እና በ«ብሔር/ብሔረሰቦች» ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ወያኔ እንደ እስከ ዛሬው የፈለገውን የማስወሰንና ያሻውን ሁሉ የራሱ የማድረግ አቅሙ ጥያቄ ውስጥ የከተተው በመሆኑ፣ ያን ለማዛባትና በሁለመናቸው ከትግራይ ያነሱና የኮሰመኑ አዳዲስ ማንነቶችን ለሌሎች አላብሶ፣ የትግራይ የበላይነት በሁለመናው መልኩ እንዲቀጥል ለማስቻል ነው። ከዚህ ላይ ሊስተዋል የሚገባው ባለፉት 26 ዓመታት «ትግራይ» ተብሎ ከተከለለው ክልል የተቀነሱት ከጎንደር ክፍለ-ሀገር የነጠቃቸው አራት ወረዳዎች ብቻ ናቸው። ይህም በአዲስ መልክ ከተደራጁት 39 ክፍለሀገሮች ጋር ሲነፃጸር ትግራይ በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ብዛት ከሁሉም የበላይነቱን እንድትይዝ ያደርጋል። በየትኛውም መልኩ፣ በዚህ የክፍለ-ሀገሮች ፌደሬሽን ውስጥ 5 ሚሊዮን የሚሆን ሕዝብ ከትግራይ ሌላ ሊኖር አይችልም። ይህም በሕዝብ ተወካዮችና በ«ብሔር/ብሔረሰቦች» ምክር ቤቶች ውክልና ከፍተኛ ቁጥር የሚኖረው የትግሬ ሕዝብ ነው። በዚያው መጠን የአገሪቱ በጄት ከፍተኛ መጠን ያለው የሚመደበው ለትግራይ  ይሆናል። ይህም በሁለተናዊ መልኩ የትግሬ-ወያኔ ትውልድ በኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሕይዎት ውስጥ እንደ እስካሁኑ የበላይነቱን ይዞ እንዲቀጥል ያደርገዋል።
  3. ሌላውና ለዚህ ዓይነቱ ጥቃቅን መንግሥታት መፍጠርና በክፍለ-ሀገራት ላይ ለተመሠረተ ፌደሬሽን መመሥረት የትግሬ-ወያኔን ያስገደደው ምክንያት፣ «ኦሮሚያ» ብሎ የከለለው አካባቢ ተወላጅ የሆኑ ብሔርተኞች፣ «እንደ ቁጥራችንና ብዛታችን የመንግሥትና የሕዝብ የሥራ ቋንቋ ኦሮሚኛ ይሁን፤ ወሣኝ የሆኑት የመንግሥት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሥልጣን በኦሮሞዎች ይያዙ፤ ይህ ካልሆነ ግን፣ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 39 በተሰጠው የመገንጠል መብት መሠረት እንገነጠላለን» በማለት የጀመሩት የመገንጠል እንቅስቃሴ እያየለ በመምጣቱ፣ ይህን «የሕዝብ ቁጥርና የተፈጥሮ ሀብት የበላይነት ያለን እኛ ነን» በማለት፣ በኦሮሞ ብሔርተኞች የተፈጠረውን የትምክህተኝነትና የጠባብነት እብጠት ለማስተንፈስ የታቀደ ይመስላል።ከአዲሱ የክፍለ-ሀገሮች ክፍፍል ለመገንዘብ እንደሚቻለው፣ በትግሬ-ወያኔ ላይ የጠነከረ ተቃውሞ በማሰማት ላይ ያሉትን «የኦሮሚያና የዐማራ ክልሎችን» አፍርሶ፣ በፍጥነት እየጎለበተ የመጣውን ኦሮሟዊ እና ዐማራዊ ማንነትን ለማጥፋት አልሞ የተነሳ እንደሆነ ያስረዳል። ክፍፍሉ ከመሠረቱ ሦስቱን ክልላዊ መንግሥታትን፣ ማለትም፦ «ኦሮሚያን፣ ዐማራንና ደቡብን» እንዳልነበሩ አድርጎ ያጠፋል። በአንድ ክልላዊ መንግሥት ተዋቅረው የነበሩት ዐማራ፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ በተከታታይ ለዘጠኝ፣ ለአሥርና ለአሥራ ሦስት ተሸንሽነዋል። የቆዳ ስፋታቸውና ያካተቱት የሕዝብ ብዛት በነበረ መልኩ ሊሆን እንደሚችል ቢታሰብም፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ሶማሊ እና ቤንሻንጉል-ጉምዝ የነበራቸውን ስም ይዘው እንዲቀጥሉ ተደርጓል። ሐረሪ እንደ ጥንት ጧቱ በሐረር ክፍለ-ሀገር የተካተተ ይመስላል፤ በአዲሱ የክፍለ-ሀገር አደረጃጀት ራሱን ችሎ አልተጠቀሰምና።

    ማንም ሊገነዘበው እንደሚችል፣ የትግሬ-ወያኔም ሆነ፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች፣ በተለይም ኦነግ፣ ሳያስቡት የማዕከላዊ መንግሥትና የአንድነት ኃይሉ ባልጠበቁት ወቅትና ፍጥነት ከሥልጣን መወገድ በፈጠረላቸው ድንገተኛ የሲቃና ደስታ ስሜት ተውጠው፣ ሁለቱም ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ዐማራ ቡድኖች፣ የኋላውን ወይም መጭው ምን ሊሆን እንደሚችል ሳያንሰላስሉ፣ አገሪቱን ከነባር የአደረጃጀትና የግንኙነት ባህል አውጥተው፣ በቋንቋ ልዩነት ላይ የተመሠረተ የፌደራል አደረጃጀት እንድትከተል አደረጉ። ለዚህም የኦሮሞ ብሔርተኞች ዮሐን ክራፍ የተባለው የጀርመን ሚሽነሪና ሰላይ፣ መካከለኛውን አፍሪካ የጀርመን ቅኝ ግዛት ለማደረግ በተሰጠው ተልዕኮው መሠረት፣ ተልዕኮው መሳካት የሚችለው «በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩትን ጋሎች (ኦሮሞች) አንድ የጋራ መታወቂያ ክልል ሰጥቶ፣ መግባቢያ ቋንቋቸውም አንድ ዓይነት እንዲሆን ማደርግ ነው» ሲል ድምዳሜ ላይ ደረሰ።

    ለዚህ ድምዳሜውም፣ ኦሮሞዎች ሊኖሩበት የሚገባውን ክልል «ኦርማኒያ» ሲል፣ ቋንቋቸውን «አፈ ኦሮማ» እንዲባል ለጀርመን መንግሥት ሀሳብ ማቅረቡ ይታወሳል። ይህን እንግዲህ በ18ኛው ክፍለ-ዘመን አጋማሽ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኦሮሞ ብሔርተኞች  የዐማራውን ነገድ እንደ ቅኝ ገዥ፣ ምኒልክን እንደ ጥቁር ናዚ በመሳል የራሳቸው የሆነና «ኦሮሚያ» የሚባል ግዛት ከኢትዮጵያ በመገንጠል ለመመሥረት ሲንቀሳቀሱ መኖራቸው ይታወቃል።

    በመሆኑም ሁለቱ ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ትናንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ጋር አጣጥመው ሳያዩ፣ በድንገተኛ ድል ተሳክረው፣ ኦሮሞዎቹ በየትኛውም ጊዜ ዕውን ይሆናል ብለው ያላሰቡትና ከሰማይ እንደወረደ መና የሚቆጥሩት መልካም አጋጣሚ ተፈጠረላቸው።

    የትግሬ-ወያኔም ትግራይን ለመገንጠል መሬት ነክሶና ቆንጥጦ የተዋጋ ቢሆንም፤ እንዲዚያ ባለ ፍጥነት የመላው ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሥልጣን ባለቤት እሆናለሁ ብሎ ባልጠረጠረው መንገድ ሥልጣን ከመሀል መዳፉ ገባለት። ለሥልጣኑ መደላደልና ባጭር ጊዜ ውስጥ ዕውቅና ለማግኘት ሲል፣ ኦነግ የጠየቀውን፣ በራሱ ሰው በሌንጮ ለታ በተረቀቀ የሽግግር መንግሥት ቻርተር፣ የራሱ «ኦሮሚያ» የተባለ ክልል የአገሪቱ ሁለንተናዊ ሀብት ጎተራ የሆኑትን ክፍለ-ሀገሮች ጠቅሎ በመስጠት፣ ኦሮሚኛን የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ፈቀደለት። ይህንንም ድላቸውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ለተያያዙት የዘመናት ትግል የዓላማቸው መዳረሻ አድርገው ቆጠሩት። ሁለቱ ፀረ-ኢትዮጵያ ቡድኖች ኢትዮጵያን የማጥፋት የዓላማቸው ብቸኛ ማረጋገጫ መስፈሪያቸው የዐማራው መጥፋት እንደሆነ በማመን፣ በዐማራው ላይ ሰብአዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቹና ጥቅሞቹን ከመንጠቅና ከመግፈፍ አልፈው የእርዳ ተራዳ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ሰላባ አደረጉት። በዚህም ከ5 ሚሊዮን በላይ ዐማሮች ከምድረ-ገጽ እንዲጠፋ አደረጉ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ደግሞ ሀብት ንበረታቸውን ተነጥቀው ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ እንዲባረሩ ተደረጉ።

    ሆኖም ሌባ ሲካፈል እንጂ ሲሰርቅ ስለማይጣላ፣ ኢትዮጵያን፣ ኢትዮጵያዊነትንና ዐማራን ለማጥፋት ይበጀናል ባሉት መንገድ ሽርክና የፈጠሩት ቡድኖች፣ የኢትዮጵያን ሀብት በመካፈሉና ወሣኝ የሥልጣን ቦታዎችን በመያዝ ረገድ የአንበሣውን ድርሻ ለእኔ፣ ለእኔ በማለት ወደ ጦርነት ገቡ። ኦነግም ሳያስበው ጨብጦት ከነበረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕምብርት ውስጥ በወያኔ ተግፍትሮ እንዲለቅ ተገደደ። ይህም መላው የኦሮሞ ብሔርተኞች «የያዝነውን አጣን»፣ በሚል ስሜት በዮሐን ክራፍ የተነደፈላቸውን «ኦሮሚያ» የሚባል አገርና «ኦሮሚኛ» የሚል የጋራ ቋንቋቸውን የትግሬ-ወያኔ የፈቀደላቸው በመሆኑ፣ የትግሬ-ወያኔን የኦሮሞ ሕዝብ ባለውለታ እንደሆነ በመቁጠር በጠላትነት የሚመለከቱት አልሆኑም። በመሆኑም በሺህዎች የሚቆጠሩትን የኦሮሞ ልጆች ገድሎና አስሮ ሲያሰቃይ፣ የሚያወግዙት ዐማራውን እንጂ፣ የትግሬ-ወያኔን አይደለም። ይኸም ሆኖ፣ «ብልጥ ልጅ የሰጡትን ይዞ ያለቅሳል» እነደሚሉት፣ የኦሮሞ ብሔርተኞች የያዙትን ይዘው ከማልቀስ ወጥተው፣ «ኦሮሚያን» ለመገንጠል በመንቀሳቀሳቸውና ይህም የትግሬ-ወያኔን አገዛዝ ሁለንተናዊ አቅም እያዳከመው በመምጣቱ፣ ይህን በሕዝብ ቁጥር እና በተፈጥሮ ሀብት የበላይነት ስሜት «የሰከረውን» የኦሮሞ አክራሪ ብሔርተኛ ቡድን ፍላጎት ለማስተንፈስ ትናንት ያለዕውቀት፣ ያለማስተዋል፣ «የናንተ ነው» ብለው የሰጧቸውን «ኦሮሚያ» የተባለውን ክልል መንጠቅና «ኦሮሚያ» የተባለ አገር እንመሠርታለን የሚለውን የኦሮሞ ብሔርተኞች ፍላጎት ወደ ቀን ቅዠትነት ለመለወጥና ለትግሬ-ወያኔ ዕድሜውን ለማራዘም የሚያስችል የኃይል አሰላለፍ ለውጥ ለማድረግና የተወሰነውን አንድነት ኃይል በመክፈል ድጋፍ ሊያስገኝልን ይችላል ብሎ የትግሬ-ወያኔ ያዘጋጀው የሌላ ዙር ማታለያ ይመስላል።

    በሌላ በኩል እየተጠናከረ የመጣውን የዐማራ የኅልውና ሕዝባዊ እንቢተኝነት እንቅስቃሴ በአውራጃ፣ በወረዳና በክፍለ-ሀገር ዐማራውን ከፋፍሎ ለማዳከምና የትግሬ-ወያኔን የአገዛዝ ዘመን ለማራዘም እንደሆነ መጠራጠር አይቻልም። ምክንያቱም ዐማራው ለክፍለ ሀገር፣ አውራጃና ወረዳ ማንነቱ የጎላ ቦታ ስለሚሰጥ፣ በዚህ ስስ ስሜቱ በመግባት፣ ከዐማራዊ የኅልውና ጥያቄው ለማፋታት እንደሆነ ይታመናል። በዚህም የተነሳ «የዐማራ ክልል» ብሎ ከልሎት የነበረውን አካባቢ በዘጠኝ ክፍለ-ሀገሮች ሸንሽኖታል።

     

     

     

    ይህ በ39 ክፍለ-ሀገሮች ላይ የተመሠረተ ፌደደራላዊ የመንግሥት አደረጃጀት እንደታሰበው በሥራ ላይ ከዋለ የሚከተሉት ጥቅሞችና ጉዳቶች ይኖረዋል።

    ጥቅሞች፦

     1)    በተፈጥሮ ሀብትና ሆን ተብሎ በተዛባ የሕዝብ ቆጠራ «በሕዝብ ቁጥር የበላይ ነን» በማለት፣ «ሁሉም ለእኛ ይሁን»፣ «ምኒልክ ጥቁር ናዚ ነው» በማለት ዐማራን ለማጥፋት ከትግሬ-ወያኔ ጋር የተባበሩትን የኦሮሞ ብሔርተኞች እብጠት በእጅጉ ያስተነፍሳል። «ኦሮሚያ» የሚለው ዮሓን ክራፍ ወለድ የግዛት ስም ያከትማል። የተስፋየ ገብረአብ «የቡርቃ ዝምታ» የወለደው የአኖሌ ሀውልት እንዲፈርስ በር ይከፍታል።

    2)     አማርኛ ቋንቋን ከመንግሥትና ከሕዝብ የሥራ ቋንቋነት ለማስጥፋት የሚደረገውን ሤራ ያከሽፋል። አማርኛ ከሞላ ጎደል የሁሉም ክፍለ-ሀገራዊ መንግሥታት የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ተጽዕኖ ያሳድራል።

    3)     የየነገድና የጎሣቸው አለቃ/መሪ ለመሆን ለሚጓጉ የወያኔ ጀሌዎች ወደፊት ወንበር እንዲመጡ ሠፊ በር ይከፍታል። የመንግሥት መሪዎች ነን የሚሉት ከ9 ወደ 39 ያሳድጋልና!

     

    ጉዳቶች፦

     1)    በሁሉም ዘርፍ የትግሬ-ወያኔን የበላይነት ያጠናክራል። ይህም የትግሬ-ወያኔ «ለመቶ ዓመታት በተከታታይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቁንጮ ላይ እኖራለሁ» ሲል ያቀደውን ሤራ ተግባራዊ ለማድረግ ይጠቅመዋል። ውጤቱም የኢትዮጵያዊነት የጋራ ዕሴቶች ተሟጠው እንዲጠፉ ሠፊ ዕድል ይሰጣል።

    2)     እስካሁን በሥልጣን ሽኩቻው ያልገቡ የሕዳጣን ነገዶች ልሂቃንን ወደ ሽኩቻው እንዲገቡ በር ይከፍታል። ይህም የእርስ በርስ ጦርነቱና ንትርኩ የበለጠ ነዳጅ እንዲያገኝ የሚረዳ በመሆኑ፣ አዲሶቹ ክፍለ-ሀገራዊ ክፍፍሎች በድንበር፣ በነገድ፣ በበጄት ድልድል፣ በልማት ቅደም ተከተል ወዘተርፈ በመሳሰሉት እርስ በራሳቸው በመናቆር የትግሬ-ወያኔ ገላጋይ መስሎ በመግባት ንትርኩን በማባባስ በሕዝቡ ኑሮ ላይ ጫና በማብዛት «የትግሬ-ወያኔ የተሻለ ነው» እንዲባልና አገዛዙን አጠናክሮ እንዲቀጥል ዕድል ይሰጠዋል።

    3)     የኢትዮጵያዊነት መገለጫና መታወቂያ የሆኑትን አስተዳደራዊ ክፍፍሎች በማዛባት የሕዝቡን የነበረ ማንነቱን ያሳጣል።

    4)     ክፍፍሉ «የኦሮሚያ» የተሰኘ አገር እንመሠርታለን ብለው ሌት ተቀን የሚጥሩትን የኦሮሞ ብሔርተኞች የዘመናት ሕልም የሚያጨልም በመሆኑ ተቃውሞአቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ያደርጋል። ይህም የሰላምና መረጋጋት ጠንቅ ይሆናል።

    5)     «በደቡብ ብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል» ተካተው የነበሩትንና አንድ ዓይነት ማንነት ለመፍጠር ይጥሩ የነበሩትን ነገዶችና ጎሣዎች ሁኔታ በመቀየር፣ በትናንሽ ማንነቶች ስለሚተካ፣ የወደፊት እጣ ፋንታቸው ወደማያቋርጥ ክፍፍልና ብጥብጥ የሚመራቸው በመሆኑ፣ ኑሮአቸው የጎሰቆለ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ ክልል ተጠቃለው የነበሩት እንደ ወላይታ፣ ሃዲያ፣ ከምባታ፣ ጉራጌ፣ ወዘተርፈ ዓይነት ነገዶችና ጎሳዎች ከፍተኛ የመሬት ጥበት ያለባቸው በመሆኑ፣ የእነርሱን ተዘዋውሮ የመሥራት መብት በእጅጉ በማጥበብ ለከፋ ድህነት ይዳርጋቸዋል።

    6)     አዲሶቹ ክፍለ-ሀገሮች አዲስ ማንነት ያጠለቁ ስለሆኑ፣ የየአካባቢዎቹ ልሂቃን ማንነታቸውን ለማስረገጥና በሕዝቡ ዘንድ ለማስረጽ የሚደረገው ሠፊ ጥረት የሕዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ከትግሬ-ወያኔ ላይ እንዲነሳ በማድረግ፣ የትግሬ-ወያኔ አገርና ትውልድ የማጥፋት ዓላማው ያላንዳች ሀግ ባይ እንዲቀጥል ሠፊ በር ይከፍትለታል።

    በጥቅሉ የታሰበው የ39 ክፍለሀገራዊ ፌደሬሽን በሥራ ላይ ከዋለ እነዚህና መሰል ሁኔታዎች ሊከተሉ እንደሚችል መገንዘብ ይቻላል። ይህ ያንድ በኩል ዕይታ ነው። ሁሉም በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚል ወገን ሁሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚታየውንና የሚሰማውን ለሕዝብ ዓይንና ጀሮ ቢያደርስ አንድ የተጨበጠ ቁምነገር ላይ መድረስ ስለሚቻል ሕዝቡን በአንድ አቅጣጫ ለማሰለፍ ይረዳልና ያለንን አስተያየት እንወርውር

    ኢትዮጵያ በጀግኖች እና ቆራጥ ልጆቿ መስዋዕትነት ለዘለዓለም ፀንታ ትኖራለች! 

    ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

    ፈለገ አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!

    ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት!

LEAVE A REPLY