የአስቸኳይ ጊዜ አወጁ እስከመቼ? /ከ ሀ. ህሩይ ቶሮንቶ-ካናዳ/

የአስቸኳይ ጊዜ አወጁ እስከመቼ? /ከ ሀ. ህሩይ ቶሮንቶ-ካናዳ/

እ.አ.አ. ከጥቅምት 2015 ጀምሮ በሀገሪቷ ውስጥ በሰላማዊ መንገድ የተጀመረውን ተቃውሞ እና የመብት ጥያቄ በአግባቡ ከመመለስ ይልቅ፤ መንግስት የሀይል እርምጃ መውሰዱን በመምረጥ የገደላቸው እና ያሰራቸው ዜጎች በርካቶች ናቸው፡፡ ከህግ ውጭ እየወሰደ ያለውን የሀይል እርምጃ እና የመብት ጥሰት ሀጋዊ ለማድረግ፤ ከኦክቶበር 2016 ጀምሮ ለ6 ወራት የሚቆይ ያስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በማወጅ እና ኮማንድ ፖስት በማቋቋም በሕግ እውቅና የተሰጣቸውን እና የተረጋገጡትን የዜጎች ሰብአዊና ዴሞክራሲየዊ መብቶች አግዷል፡፡

ትክክለኛው ቁጥር መንግስት ከገለፀው በላይ ቢሆንም መንግስት ራሱ 24,000 ሰዎችን ማሰሩን እና ከነዚህም ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ተሀድሶ ተሰጥቷቸው ወደ 21,000 የሚሆኑት ከእስር መልቀቁን፤ ቀሪዎቹ ደግሞ እንደፈፀሙት ጥፋት ጉዳያቸው በፍ/ቤት እንደሚታይ የኮማንድ ፖስቱ ሲክሬታሪያት ገልፀዋል፡፡ በሌላም በኩል ጠ/ሚኒስትሩ አደጋ ላይ ወድቆ የነበረው የሀገሪቱ እና የህዝቡ ሰላም የተመለሰ መሆኑን ገልፀዎል፡፡ እየገለፁም ነው፡፡ ባለስልጣናቱም ሰላምና መረጋጋት የሰፈነ መሆኑን ለማብሰር በየክልሉ ሽር ጉድ ሲሉ ይታያሉ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ የዜጎችን መብት አግዶ፤ በሽዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በእስር ቤት አጉሮና፤ የሚፈልገውን ገድሎ ህዝቡን በፍርሀት ካሸማቀቀ በኋላ፤ ለይስሙላ የካቢኔ ለውጥ አድርጓል፡፡ በየክልሉ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ብዙ ባለስልጣናትን ከስራ አሰናብቷል፡፡ በረቀቀ መንገድ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በመከፋፈል ከሚፈልጋቸው ጋር የይስሙላ ድርድር ጀምሯል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ እኩይ እርምጃ የህዝቡን ተቃውሞ አላቆመም፡፡ ጥያቄውንም አልመለሰም፡፡ ምክንያቱም የሚያስፈልገው እውነተኛ የሆነ የሰርዓት ለውጥ ስለሆነ ነው፡፡ እንግዲህ መንግስት ይህንን ሁሉ የሚያደርገው የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስና፤ በፀረ ሰላም የውጭ ሀይሎች ተቀስቅሷል ያለውን የሀገሪቷን እና የህዝቡን ሰላም ለመመለስና ለማረጋገጥ ከሆነ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አወጁ ዓላማ ግቡን መትቷል ማለት ስለሆነ፤ በስራ ላይ መቆየቱ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሁኔታዎች እየታዩ የቆይታው ጊዜ እንደሚራዘም ሁሉ፤ ሁኔታዎች እየታዩ ከጊዜ ገደቡ ወዲህ ሊነሳ እንሚችል ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ የኢሕአዴግ መንግስት ትልቅ ራስ ምታት የሆነበት፤ የህዝቡ ተቃውሞና አመፅ አሁንም የቀጠለ እና፤ እንዲያውም ወደ መሳሪያ ትግል እየተለወጠ መሆኑ ነው፡፡ ለፕሮፓጋንዳ ያህል የህዝቡ ጥያቄ ተመልሷል፣ ሰላም ሰፍኗል ይበል እንጂ፤ የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄ አልተመለሰም፡፡ ጥያቄው ሀገሪቷን እና ዜጎቿን በእኩልነት እና በነፃነት የሚያስተዳድር፣ በህግ የበላይነት የሚያምን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንዲመሰረት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንደሌለ እና የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱ ለመሆኑ ዓለም ያወቀው ሀቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዜጋም የሚያውቀው ነው፡፡

ለህዝቡ መብት የሚታገሉና፤ መብቱ እንዲከበር በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ያቀረቡ ፓርቲዎችን በማፍረስ፣ በማዳከም፤ ብሎም መሪዎቻቸውን እና አባሎቻቸውን ያለፍትህ በማሰርና በተንዛዛ የፍርድ ሂደት በማንገላታት፤ መንግስት መልሻለሁ የሚለው የህዝብ ጥያቄ አስቂኝ ስለሆነ፤ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ተነሳም አልተነሳም ህዝቡ ለመብቱ የሚያደርገው ትግል ይቀጥላል፡፡

በቸር ይግጠመን

LEAVE A REPLY