ወዳጆቼ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሪፖርት ከሞላ ጎደል አድምጠናል! /ግርማ ሰይፉ ማሩ/

ወዳጆቼ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሪፖርት ከሞላ ጎደል አድምጠናል! /ግርማ ሰይፉ ማሩ/

ወዳጆቼ የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሪፖርት ከሞላ ጎደል አድምጠናል፡፡ እንደተለመደው አሁንም በእድገት ጎዳና ላይ እንገኛለን፡፡ በሚገርም ሁኔታ የበጀት ጉድለት መሻሻል አሳይቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ አገሪቱ የምታገኘው የውጭ ምንዛሪ በተከታታይ እየቀነሰ ባለበት ሁኔታ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሬ ለምን ቀነሰ ብዙ ምክንያቶች መደርደር ቢቻልም አሁን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡን መረጃ የበጀት ጉድለት የተሻሻለው ከውጭ የሚገባው ዕቃ በመቀነሱ ነው፡፡ ልብ በሉ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ቀንሶ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ዕቃ ቀንሶ አገራችን ግን በእድገት ጎዳና ላይ እየገሰገሰች ነው፡፡ በረሃብ ሰውነታችሁ ሲከሳ ጎሽ ሰውነቴ ቀንሶ ሸንቃጣ ሆንኩ እንደማለት ነው፡፡ ይህች አልባኒያ ኤኮኖሚ አሁንም አለች እንዴ?

የአገራችን የኤኮኖሚ እድገት ከተነሳ፤ እርዳታ የሚያስለምን ድርቅ የማይበግረው ኤኮኖሚ ገንብተናል፡፡ እርዳታ ከተነሳ አይቀር ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አንድ ነገር ደረታችንን ነፍተን አንገታችንን ቀና አድርገን መናገር ያለብን ነገር ነግረውናል፡፡

ድርቁ እኛ እንደሰማነው ብዙ ሺ እንሰሳት ቢቀጥፍም አንድም የሰው ህይወት ሊነካ አልቻለም፡፡ ይህ አስማት ይገባችኋል? እኔ አልገባኝም፡፡ መቼም የሰው ህይወት ከእንስሳቶቹ የተሻላ ድርቅ መቋቋም መቻሉ አስገራሚ ነው፡፡ ይህ የእኔ የእውቀት ችግር ይሆናል፡፡ ሰው መሞት ያቆመበት የዚህ ችጋር ሚስጥር፣ የሚስጥረኛነታችን፤ የድብቅ ገበና አባዚያችን ብቻ ነው፡፡ በጎረቤት አገር በድርቁ ምክንያት ሰው እየሞተ በእኛ ሞት የራቀበት ሚስጥር፡፡ በከተማ ውስጥ ልጆች በጠኔ በሚወድቁበት አገር፣ ደርቅ ባለባቸው ቦታዎች ጠኔ መግደል ትቶ ሌላ አገር ሄዶዋል፡፡

ሌላው ሪፖርቱ ሲቀርብ የታዘብኩት ነገር አቶ ሶፊያን አህመድ (የቀድሞ ሲኒየር ሚኒስትር) ግርጅፍ ብለው መታየታቸው ብቻ ሳይሆን የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ሁኔታ የሚያዩበት ሁኔታ ኢቢሲ እንዴት እንዳቀረበው ገርሞኛል፡፡ እናንተስ፡፡ በቅርቡ ከስልጣን የተሰናበቱት የት እንዳሉ ለጊዜው የማናውቃቸው ወ/ሮ አስቴር ማሞንም ስመለከት አንድ ነገር ትዝ አለኝ፡፡ እንደምታውቁት የምርጫ ወረዳቸው በቅርቡ አደጋ የደረሰበት የቆሼ አካባቢ ነው፡፡

ለምርጫው ሰሞን አለርት አካባቢ በሬ አስጥለው ሲጋብዙ ነበር፡፡ ዛሬ ምን ነው ለቅሶ ሳይደርሱ ቀሩ? በሚቀጥለው ምርጫ ባይገቡ እንኳን የቀድሞ ውለታ እንዴት ይረሳል፡፡ በኒዎርክ በአሸባሪዎች በንግድ ማዕከል ላይ አደጋ የደረሰ ጊዜ ሂላሪ ክሊኒተን የኒዎርክ ተመራጭ ነበሩ፡፡ በወቅቱ የሰሩትን ስራ ለፕሬዝዳንትነት ሲወዳደሩ ለምርጫ ቅስቀሳ ሲጠቀሙበት ነበር፡፡ ወጉ እንዳይቀር ምሳሌ ላቅርብ ብዬ ነው፡፡ የእኛ ምክር ቤት ሰዎች በሰፈራቸው ዜጎች በጥይት ሲቆሉ፣ በአመፅ ሲታመሱ፣ ምን ነው? እኔ እያለሁ ብለው በአደባባይ አይታዩም፡፡ የምክር ቤት ሰዎቻችን ሰራቸው የፓርቲያቸውን የአዋጅ ምርት ማምረት ነው፡፡

በዚሁ አጋጣሚ በቆሼ ለደረሰው አደጋ ጥናት ይጠናል፡፡ ለዚሁም ከቴክሳስ የሚመጡ ባለሞያዎች ይኖራሉ መባሉን የሰማ ጓደኛዬ አሁን የሼክ አላሙዲን ድርጅቶች የሰጡትን ጠቀም ያለ እርዳት (ፈጣሪ አብዝቶ ይስጥልኝ ብያላሁ በዚሁ አጋጣሚ) ሌሎችም እንዳቅማቸው የወረወሩት በጥናት ሰበብ ሊጨርሱት ነው፡፡ ብሎ ጥርጣሬውን አጋርቶኛል፡፡ እኔም ይህ ጥርጣሪ አለኝ፡፡ መፍትሔው አሁኑኑ ከተጎጂዎች፣ ድጋፍ ካደረጉ ድርጅቶች፣ ከሌለች ከሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣ አካል ተቋቁሙ ገንዘቡ ለእለት ደራሽ እርዳታ ሳይሆን ለዘላቂ መልሶ ማቋቋም እንዲውል ማድረግ የግድ ይላል፡፡ መንግሰትም “አስፈላጊውን ድጋፍ አደርጋለሁ” ከሚል መያዣ መጨበጫ ከሌለው ፉከራ፣ በአስቸኳይ የሚሰጠውን ቦታ፣ ገንዘብ መጠን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

LEAVE A REPLY