የሲራጅ ፈጌሳ መግለጫና የሃይለምርያም ደሳለኝ 84% “ድጋፍ” ቀልድ ዋነኛ መልዕክት ምንድነው?

የሲራጅ ፈጌሳ መግለጫና የሃይለምርያም ደሳለኝ 84% “ድጋፍ” ቀልድ ዋነኛ መልዕክት ምንድነው?

የሲራጅ ፈጌሳ መግለጫና የሃይለምርያም ደሳለኝ 84% “ድጋፍ” ቀልድ ዋነኛ መልዕክት ምንድነው? ኢትዮጵያን የሚያስተዳድረው የወታደራዊና ደህንነት ጁንታ ቃል አቀባይ ሲራጅ ፈጌሣ የተባለው ሰው (መከላከያ ሚኒስቴር! የሚለውን ማአረጉን አሱም ሆነ ጌቶቹ አያምኑም!) ከትናንት ወዲያ ወደ መገናኛ ብዙሃን ብቅ ብሎ፣ የዛሬ አምስት ወር በሀገሪቱ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ፣ ሃገሪቱ ላይ የሰፈነውን ሰላምና መረጋጋት ታሳቢ በማድረግ፣ የአዋጁ አንዳንድ አንቀጾች መነሳታቸውን ወይንም ላላ መደረጋችውን ይፋ አድርጓል።

የህዝብን አንቅስቃሴ ከመገደብና ከማፈን ውጭ፣ ምንም አይነት የሀገር ህልውናን የሚፈታተን ሁኔታ በሌለበት ወቅት(ለስልጣናቸው ስሱ በመሆናቸው ብቻ!) በፍጹም መታወጅ ያልነበረበትን አዋጅ ደንግገው ሲያበቁ፣ ቀነ ገደቡ ሊያልቅ አንድ ወር ሲቀረው፣ በተገኘው” አንጻራዊ ሰላም” (ጥብቅ አፈና ቢል ይቀል ነበር ) አንዳንድ አንቀጾች ተነስተዋል የሚለው ገለጻ የሚያመለክተው ነገር ቢኖር፣ በመሰረቱ ጁንታው ላልተወሰነ ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማራዘም መወሰኑን ነው። በዚህ አዋጅ መሰረት መንግስት ያመናቸው ከ 40000 በላይ ታሳሪዎች አንደነበሩና ከነዚህም ውስጥ አስከ 20000 የሚሆኑት ‘ትምህርት’ አግኝተው መፈታታቸውን ብንሰማም(ባሳፋሪና ከደርግ በተዋሰው አሰራር አሸማቃቂ ጽሁፍ ያዘለ ካናቴራ አስለብሶ)፣ ሌሎች አካላት ግን በፌዴራልና በክልል አስር ቤቶች መቶ ሺዎች ታስረው አንደነበረና፣ የተወሰኑ የተፈቱ ቢኖሩም ጅምላ አስሩና አንግልቱ ግን አሁንም አንደቀጠለ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አንዳሉ ይገልጻሉ። የወታደሩ፣ የደህነንትና የፖሊስ ወከባ፣ አስርና አንግልት የየቀኑ የዜጎች አጣ በሆነበት ሀገር፣ መረጋጋት የሚሉት ፌዝ ፣ሀገር አቀፍ ሊባል በሚችል ሁኔታ ሞቅና ደመቅ ብሎ የነበረው ሕዝባዊ ትግል አስበርግጎት የነበረው የገዢ ቡድንን አስመልክቶ የሚነገር ካልሆነ በቀር፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ገላጭ አንዳልሆነ ሁሉም የሚገነዘበው ነው። የኢህአዴግ መንግስት ራሱን ሲያንቆለጳጵስበት የነበረውን ‘ህገ መንግስት ‘ አሽቀንጥሮ ጥሎ በገሃድ በወታደራዊና ደህንነት ጁንታ መመራት የጀመረበትን አምስተኛ ወር አስቆጥሯል።

በሀገር ቤት ያለው ተጨባጭ ሁኔታ የሚያመላክተው፣ የሀገሪቱ አጠቃላይ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ መረጋጋት ሳይሆን ውጥረቱ ከቀን ቀን፣ ከወር ወር አየጨመረ መሄዱን አንጂ መረጋጋትን አይደለም። ይሄንንም በመገንዘቡ ይመስለኛል የገዥው ቡድን በቃል አቀባዩ አማካኝነት አንዳንድ አንቀጾች አነሳሁ በሚል ሰበብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘሙን በተዘዋዋሪ ያበሰረን። የመንግስት አፈናና አስር የህዝብን ትግል ሙሉ ለሙሉ የመግታት አቅሙ ሁልጊዜም ግዜያዊ በመሆኑ፣ የህዝቡ ትግል ስፋትና ጥልቀት አየጨመረ መሄዱና የኢህአዴግ መንግስትም ሊቋቋም የሚችልበት አቅሙ አየላላ አንደሚሄድ በመገንዘብ የገዢው ቡድን በውስጡ የቀረ ትንሽ የኃላፊነት ስሜት ካለው፣ አሁኑኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ከማንሳት ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም።

በእስካሁን አብሪቱ ቀጥሎ ከሄደ ግን የጊዜ ጉዳይ ነው አንጅ ከስሩ ተመንግሎ አንደሚወድቅ ጥርጥር አይኖርም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁኑኑ ይነሳ! በአዋጁ ሰበብ የታሰሩ አስረኞች በሙሉ አሁኑኑ ይፈቱ! በሀገሪቱ ያሉት የፖለቲካ አስረኞች በሙሉ አሁኑኑ ይፈቱ!

አበጋዝ ወንድሙ

LEAVE A REPLY