“የእንስሳ ኮቴ!” የምን የእንስሳ ኮቴ? /በፍቃዱ ዘ ኃይሉ/

“የእንስሳ ኮቴ!” የምን የእንስሳ ኮቴ? /በፍቃዱ ዘ ኃይሉ/

የተቀመጣችሁበት ካፌ/ሬስቶራንት ውስጥ የሆኑ ወጣቶች መጥተው፣ የሆነ በራሪ ወረቀት ቢሰጧችሁ ምን ትገምታላችሁ? ያው የኮምፒዩተር ወይም የቋንቋ ሥልጠና ማስታወቂያ ነገር – አይደል? እኔን ግን በቀደም‘ለት አራት ኪሎ (ምርፋቅ) የገጠመኝ “ቀዳማይ የቱሪዝም ክለብ” የተባለ ቡድን “ወደ እንስሳ ኮቴ እና አዲስ ዓለም ከተማ በ195 ብር ያዘጋጀው የጉብኝት ጉዞ” ነበር። ከአቤል ጋር ትናንት አብረናቸው ሔድን።

የጉዟችን መደምደሚያ የነበረው መጀመሪያ በኢጄሬ ከተማ (ወይም እቴጌ ጣይቱ ባወጡላት ሥሟ አዲስ ዓለም) የሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ እልፍኝ ውስጥ ምሳ መብላት ነበር። (ይህንኛው አልተሳካም፤ አዳራሹ “ለመንፈሳዊ” አገልግሎት ተይዞ ነበር።) ቀጥሎ፣ በማርያም ቤተ ክርስትያን ሥር የሚገኘው ሙዚየም ውስጥ ያሉትን ከዳግማዊ ምኒልክ ዘውድ እና አልጋ አንስቶ፣ በሰገሌ ጦርነት ከንጉሥ ሚካኤል አሊ የተማረከ ሰይፍ እና ሌሎችንም መጎብኘት ነበር። ተሳክቷል። ከጉዟችን መደምደሚያ በፊት ግን በጣም ገራሚ ጠዋት አሳልፈናል። “እንስሳ ኮቴ” የተባለ ስፍራ ውስጥ።

አስጎብኝዎቻችን በሚንገጫገጨው መንገድ፣ በቅጥቅጥ አውቶቡስ እየወሰዱን ገለጻ ያደርጉልን ነበር።

“አሁን የምንሔድበት ይህ መንገድ፣ በ1896 የተሠራ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አስፋልት መንገድ ነው። ከአዲስ አበባ – አዲስ ዓለም 56 ኪሎ ሜትር ይረዝማል። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አዲስ አበባ የማገዶ እጥረት ገጥሟት ስለነበር፣ መናገሻ ከተማቸውን ወደ አዲስ ዓለም ሊያዞሩ ከወሰኑ በኋላ፣ ቤተ መንግሥታቸው ተሠርቶ እስኪያልቅ ከአውስትራሊያ መጥቶ የተዘራው ባሕር ዛፍ እንጦጦን አጥለቀለቃት። አዲስ አበባም መናገሻነቷ ቀጠለ።” በዚህ ሰዓት አዲስ አበባ የባሕር ዛፍን ውለታ ከፍላም አትጨርሰው እያልኩ እያሰብኩ ነበር።

30 ኪሎ ሜትር እንደተጓዝን ደጃፉ ላይ በሰም በተወለወሉ ጣውላዎች ላይ በኦሮምኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛ “ወደ እንስሳት ኮቴ የዱር እንስሳት መጠለያ እና የትምህርት ማዕከል እንኳን ደና መጡ” የሚል ጽሑፍ ያረፈበት በር ላይ ቆምን። ጊቢው በሽቦ አጥር የተከበበ ጫካ ነው። ወደ ውስጥ ሲዘልቁ ከከተማ ጭስ ተራርቀው፣ ከተፈጥሮ ሽታ ጋር ይገናኛሉ። በጊቢው ውስጥ በሰዎች በሕገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ አንበሶች፣ አቦ ሸማኔዎች፣ ጭላዳ ዝንጀሮዎች፣ ንሥር አሞራዎች እና ሌሎችም አሉ። ማዕከሉ የተቋቋመው “ቦርን ፍሪ” በተባለ የውጭ ድርጅት ነው። እንስሳቱ በማዕከሉ የዱር ኑሮ ከተለማመዱ በኋላ፣ ብቃታቸው ሲረጋገጥ ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ዱር ይለቀቃሉ። ብቁ መሆን ያቃተው እንስሳ ካለ፣ እዚያው በእንክብካቤ ዕድሜውን እንዲገፋ ይደረጋል።

የማዕከሉን ፋይዳ ለመረዳት የአንዱን አንበሳ ታሪክ መስማት በቂ ነው። ያ አንበሳ በአሳዳጊው በሰንሰለት ታስሮ ነው የኖረው። ሰንሰለቱ አንበሳው ሲያድግ እያጣበቀው በመሔዱ ምክንያት የነርቭ ስርዓቱ ተቃውሶ አሁን በከፊል ዓይነስውር ሆኗል። አንበሳው አሁን እንድታላምደው የተሰጠችውን ሴት አንበሳ ሳይቀር አንዳንዴ ይሸሻታል።

አስጎብኛችን ሥራውን በፍቅር የሚሠራ ሚሊዮን የሚባል ወጣት ነበር። በጫካው ውስጥ ወዲያ ወዲህ ስንል ቅጠላ ቅጠሎች እየበጠሰ በባሕላዊ መንገድ ምን እንደሚደረጉ፣ በሳይንሳዊ ላቦራቶሪ አልፈው ምን እንደሚሆኑ ጨምሮ የአማርኛም፣ የሳይንስ ሥማቸውን ይነግረን ነበር። የኮሴ እና ኮሰረት የመሳሰሉ ቅጠሎች ሽታ እንኳን በእጅ አሸት፣ አሸት ተደርጎ በመሐሉ ሲያልፉም ነፍስን በደስታ ያውዳል። አስጎብኛችን ሚሊዮን በመጨመርም፣ መጤዎቹ (እነ ባሕር ዛፍ እና ኦሜድላ) ምን ያክል ራስ ወዳድ (በኔ አተረጓጎም “ኢምፔሪያሊስት”) እንደሆኑና ሥራቸው ተንሰራፍቶ ምግብ ስለሚቦጠቡጥ አጠገባቸው ምንም ቅጠል እንደማይበቅል፤ በተቃራኒው አገር በቀሎቹ (እነ ግራር እና ዝግባ) ግን ቸር ከመሆናቸው የተነሳ እግራቸው ሥር ቁጥቋጦ ጥቅጥቅ ብሎ እንዴት እንደሚበቅል ያስረዳን በምሳሌ እያሳየ ነበር። ማዕከሉ ባለችው ሰባ ሔክታር ላይ፣ መጤዎቹን ዛፎች፣ በአገር በቀሎቹ ቀስ በቀስ ለመተካት ዕቅድ አለው። ይህን ሲያስረዳን፣ ቅድም የአዲስ አበባ ባለውለታ ያልኩት ባሕር ዛፍ ውለታው ሳይከፈለው መሰናበቱ እንደሆነ ተሰማኝ።

በእንስሳቱ ጉብኝታችን ወቅት፣ ጥቁር አንበሶቹ ተኝተው እና ርቀው ቢኮሩብንም፣ አቦ ሸማኔዎቹ ግን በቅርብ ርቀት አጫውተውናል። ግቢው ግን እንዲሁ፣ በጥቅሉ፣ ከተፈጥሮ ጋር ለተነፋፈቀ መድኃኒቱ ነው።

በመጨረሻም፣ አስጎብኛችን ሚሊዮን አንድ የቢቢሲ ቪዲዮ ዩቱዩብ ላይ ፈልገን እንድናይ ጋብዞን ነበር። እኔም፣ ሊንኩን የመጀሪያው ኮሜንት ላይ አስቀምጥላችኋለሁ።

LEAVE A REPLY