ከቆሻሻ ኑሮና ሞት ለመላቀቅ ቆሻሻውን ስርዐት ማስወገድ /መሳፍንት ዘፈረንሳይ ለጋሲዮን/

ከቆሻሻ ኑሮና ሞት ለመላቀቅ ቆሻሻውን ስርዐት ማስወገድ /መሳፍንት ዘፈረንሳይ ለጋሲዮን/

ነገሩ ሁሉ ከድጡ ወደማጡ በሆነባት ሀገራችን በየጊዜው የሚፈራረቁት ሰቆቃዎች ልብን በሀዘን ካራ ማድማታቸውን እንደቀጠሉ ነው። ባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ከደረሱብን መዓቶች ጥቂቱን ብናነሳ፤ በረኃብ አለንጋ እየተገረፉ ደጃፋቸው ላይ ድፍት ብለው የቀሩትን፣ መብታቸውን ለመጠየቅ ሲጮሁ የጥይት ራት የሆኑትን፣ የኢሬቻን በዓል ለማክበር አምረው ደምቀው እንደወጡ ገደል ሰብስቦ ያስቀራቸውን፣ እንዲሁም በቅርቡ በቆሻሻ ናዳ ታፍነው እስከወዲያኛው ያንቀላፉትን ወገኖቻችንን በቁጭትና በመሪር ሀዘን እናስባለን።

እነዚህን አደጋዎች ይበልጥ አሳዛኝና አስከፊ የሚያደርጋቸው ደግሞ በሀገሪቱ የተንሰራፉት አምባገነንነት፣ ዘረኝነት፣ ምዝበራ፣ ራስወዳድነትና ግድየለሽነት ውጤት መሆናቸው ነው። በአስራዎች በመቶ እድገት ሽምጥ ስለሚጋልበው ኢኮኖሚዋ ነጋ ጠባ የሚዘመርላት የወያኔዋ ኢትዮጵያ ዘራፊዎቿ ከቪላ ቪላ እያማረጡ ሲኖሩና ቤተሰቦቻቸውን ለትምህርት፣ ለወሊድና ለህክምና ወደ ውጭ ሲልኩ፤ ደሀው በጥይት የሚቆላባትና የሚበላው አጥቶ ቆሻሻ ላይ የሚወድቅባት ሀገር ሆናለች። ብሄራዊ ውርደታችንም አሰቃቂ ደረጃ ላይ የደረሰባት ሀገር።

በቅርቡ የደረሰውና ከ115 ሰዎች በላይ በአሰቃቂ ሁኔታ ያለቁበት የቆሻሻ ናዳ አደጋም የዚሁ ሀቅ ምስክር ነው። በዚህ አደጋ ያለቁት ሰዎች በስርዐቱ ስግብግብነትና ደንታ ቢስነት ተገፍተው የተጣሉ ምስኪንና ረዳት አልባዎች ናቸው። መሬት እየዘረፈና ኮንዶሚኒየም እየገነባ ከመቸብቸብና በስጋና በሌብነት ለሚቀርቡት ወዳጆቹ ከማደል ውጭ ስራ የሌለው ይህ ስርዐት የህዝቡን መከራ ዞር ብሎ ባለማየቱ የምስኪኑ ደሀ መኖሪያ የቆሻሻ ክምር ላይ ሆነ። የት ወደቅህ ባይ የሌለው ምስኪን ሃብታም አላምጦ የጣለውን ሊለቅም ቆሻሻ ሲጭር እዚያው ተቀብሮ ህይወቱን አጣ – ድሮም ቆሻሻ ላይ ህይወት ያለ ይመስል። እናት ክንዷ ላይ ያቀፈቻቸውን ልጆቿን ይዛ አሸለበች። ከአንድ ቤተሰብ አምስትና ስድስት እየሆኑ ተያይዘው ሄዱ። በዚህ ዓይነት አሰቃቂ ሁኔታ ልጆቿን ያጣችው አዲስ አበባም መቀነቷን አስራ አስከሬን ስትለቅም ከረመች።

ይህ አሳዛኝ እልቂት የተከሰተበት ስፍራ ከ50 ዓመት በፊት ለቆሻሻ መቅበሪያነት (landfill) ሲመረጥ ከከተማው ያለው ርቀት በተገቢ ሁኔታ ታሳቢ ተደርጎ ነው። ይህን ለመገንዘብ ደግሞ በወቅቱ የአዲስ አበባ ከተማ የነበራትን የህዝብ ብዛትና ስፋቷን ከግምት ማስገባት ነው። ከግማሽ ምዕተ ዓመት አገልግሎት በኋላ በስፍራው የተከማቸው ቆሻሻ 36 ሄክታር ስፋት ያለው ቦታ ሸፍኖ 13 ሜትር ያህል ተቆልሏል (ይህ እንግዲህ ከክምሩ ስር 40 ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ ውስጥ ተቀብሮ ያለውን ቆሻሻ ሳይጨምር ነው)።

ይህ ሁሉ ሲሆን በዓመት 300 ሺህ ቶን የሚጠጋ ቆሻሻ እየተደፋበት የተገነባው ይህ ተራራ በህዝብም ሆነ በአካባቢው ላይ አደጋ እንዳያደርስ የተወሰደ አንድም እርምጃ የለም። ይልቁንም የትም የተጣሉ ድሆች ክምሩ ላይ ጎጇቸውን በላስቲክ ቀልሰው ሞት አይሉት ኑሮ ሲገፉበት ቆዩ። በዚህ ሳያበቃ፤ ሌሎች ምስኪኖችም አልጠግብ ባዮቹ ዘራፊዎች በቆሻሻው ዙሪያ ካለው መሬት ሸንሽነው በሸጡላቸው ቦታ ላይ እንደአቅማቸው ቤት ሰርተው መኖር ጀመሩ። እንደዚህ ያለውን ሀላፊነት የጎደለው ተግባር ወያኔ ከሚመራው በደናቁርት የታጨቀ ስርዓት ውጪ ማን ሊፈፅመው ይታሰበዋል።

የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ስፍራ ከጥይት መጋዘን ባልተናነሰ ከፍተኛ ጥንቃቄና ክትትልን የሚፈልግ አደገኛ ቦታ ነው። ጥንቃቄ የጎደለው የቆሻሻ አወጋገድ በቀጥታ ከምናያቸው አደጋዎች ባሻገር የማናስተውላቸውና በቀላሉ የማንረዳቸው እጅግ ከባድ ችግሮች በህብረተሰብና በአካባቢ ላይ ያስከትላሉ። በተከማቸ ቆሻሻ ውስጥ የሚፈጠሩ መርዛማ ንጥረ ነገሮች የአካባቢ አየርን ውሀንና አፈርን ይበክላሉ። በዚህም ሳቢያ በአቅራቢያው የሚኖሩ ሰዎች ለካንሰር፣ ለአስምና ሌሎች ከባድ በሽታዎች በቀላሉ ይጋለጣሉ። በእርጉዞች ላይ የመውለድ እክል ሲከሰት ህጻናትም የማደግ ችግርና ሌሎች የጤና መታወኮች ይደርስባቸዋል።

ከቆሻሻው ክምር መንጭቶ ወደ መሬት የሚገባው ፈሳሽ (leachate) እጅግ መርዛማ በመሆኑ አፈርን፣ የከርሰ ምድር ውሀንና ሌሎች የውሀ አካላትን ይበክላል። የአፈሩ ምርታማነት ስለሚቀንስ ድርቅና ረሀብ ይከተላል። የተመረዘውን ውሀ የሚጠቀሙ ሰዎችና እንስሳትም በሽታ ላይ ይወድቃሉ። እነዚህን ችግሮች ለመከላከል ሊወሰዱ ከሚችሉ እርምጃዎች መካከል የቆሻሻን መጠን መቀነስ (waste reduction) እንዲሁም ቆሻሻን መልሶ መጠቀም (recycling)፣ በአግባቡ ማቃጠል (incineration) እና ለማዳበሪያንት ማዋል (composting) ይጠቀሳሉ። ሀገራችን ካላት የአቅምና የተማረ የሰው ሀይል ማነስ ምክንያት እነዚህን እርምጃዎች ተግባራዊ ማድረግ አስቸጋሪ ቢሆን እንኳን፤ ዋነኛውና እጅግ ቀላሉ መወሰድ የነበረበት እርምጃ ሰዎችና እንስሳት በአካባቢው እንዳይኖሩም ሆነ እንዳይደርሱ ማድረግ ነው።

እንደወያኔ ያለ ደንታ ቢስ በሚፈነጭበት ሀገር ግን ይህ አይታሰብም። በሀገሪቱ በሰፈነው ራስ ወዳድነትና ውንብድና ሳቢያ ስንቱ የበሽታ ሰለባ ሆኖ አልጋ ላይ እንደቀረ ብሎም ለሞት እንደበቃ ቤቱ ይቁጠረው።ሌላው አሳዛኝ ጉዳይ ጭካኔው ዘርፈ ብዙ የሆነው ይህ ስርዐት አደጋው ከተከሰተ በኋላ ያሳየው ቸልተኝነት የተሞላበት ምላሽ ነው። እንደተለመደው ወያኔ ችግሩ አደጋው ሳይሆን የሟቾቹ ቁጥር እንደሆነ ራሱ የሚያውጃቸው ዜናዎች አሳብቀውበታል። ዘወር ብሎ ያላያቸውን ምስኪኖች መውቀስና በቸልተኝነት የታጀበ “ብሄራዊ ሀዘን” ማወጅ ማላገጥ ካልሆነ ምን ይባል ይሆን? በአንፃሩ ህዝቡ በራሱ ተነሳሽነት ያሳየው ፈጣን ምላሽና ለወገን ደራሽነት እጅግ የሚደነቅና የሚያኮራ ከመሆኑም በላይ ይህ ድንቅ ህዝብ ምን ያህል የማይመጥነው ስርዓት ላይ እንደወደቀ ተጨማሪ ማረጋገጫ ሆኗል። ምንም እንኳን ወያኔን መምከር የገደል ላይ ጩኸት ቢሆንም እመራዋለሁ ከሚለው ህዝብ አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ለመማር ቢሞክር ምንኛ መልካም ነበር።

ፅሁፌን ከማጠቃለሌ በፊት አንድ ወዳጄ ያካፈለኝንና እኔም ሙሉ በሙሉ የምስማማበትን ሀሳብ ልጥቀስ። ወዳጄ አደጋው በደረሰበት አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች የተደረገላቸውን ቃለመጠይቅ አዳምጦ የታዘበውን ሲያጫውተኝ አብዛኞቹ በገዢው ቡድን ተከታታይ በደል የሚደርስባቸው ብሄር ተወላጆች እንደሚመስሉ ጠቀሰልኝ። ይህ “ቤት የእግዚዐብሄር ኮንዶሚኒየም የገብረእግዚዐብሄር” በሆነባት አዲስ አበባ እየሆነ ስላለው ነገር የሚጠቁመው ትልቅ ነገር አለ። ስለሆነም ያገባናል የምንል ሁሉ በአደጋው የሞቱትንና የተጎዱትን እንዲሁም በአካባቢው የሰፈሩትን ሰዎች ማንነት አጣርተን ይፋ ማድረግ ይኖርብናል – የስርዐቱን ቆሻሻነት ፍንትው አድርጎ ለማሳየት።

የሞቱትን ነፍሳቸውን ይማርልን፣ ያለነውንም ለቆሻሻ ኑሮና ለቆሻሻ ሞት ከዳረገን ቆሻሻ ስርዐት ይገላግላን።

LEAVE A REPLY