የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት አወዛጋቢ ውሎ

የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት አወዛጋቢ ውሎ

/Ethiopia Nege News/፦  የእነ ዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝገብ አስር ተከሳሾችን የካተተ እንደነበረ የሚታወስ ነው። አምስቱ ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ በአሰቃቂ ሁኔታ በእስር ቤት ካሳለፍ በኋላ ነፃ ናችሁ ተብለው ሲለቀቁ ቀሪዎቹ ደግሞ  ጥፋተኛ መባላቸው ይታወቃል።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነፃ ቢያሰናብታቸውም (ሀብታሙ አያሌው፣ የሽዋስ አሰፋ፣ ዳንኤል ሽበሽ፣ አብርሀ ደስታና አብርሀም ሰለሞን) የፌደራል አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ ተቀባይነት በማግኘቱ በተከሳሾችና በአቃቤ ህግ መካከል የቃል ክርክር  መደረጉ አይዘነጋም። ይሁን እንጂ መዝገቡ ለወራት ሳይቀሳቀስ ከቆየ በኋላ ሰሞኑን አወዛጋቢ በሆነ መልኩ የተወሰኑትን ተከሳሾች ቀርበው እንዲከላከሉ 4ኛው ወንጀል ችሎት አዟል።

አቶ የሽዋስ አሰፋ (የሰማያዊ ፓርቲ ሊ/መንበር) ከሀምሌ 2006 እስከ ግንቦት 2008 በእስር ካሳለፉ በኋላ ነፃ የተባሉ ናቸው።

አቶ የሽዋስ የዛሬውን የፍ/ቤት ውሎ እንዲህ ይናገራሉ፦”ትናንት ከቀኑ 9:30 አካባቢ ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተደወለልኝ መጥሪያ ለመስጠት እንደፈለጉኝ ያለሁበትን ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀው ሄጀ እንድወስድ ጠየቁኝ። እኔም በዚያ ፍጥነት ለመድረስ እንደማልችል ገልጨ ለዛሬ ጠዋት እንደምሄድ ነግሬ ብዘጋጅም ስልክ በተደጋጋሚ ደወሉ እኔም ያንኑ መልስ ሰጠሁ። ዛሬ ጠዋት ቃሌን አክብሬ ማዕከላዊ ተገኘሁ በነዘላለም ወርቅአገኘሁ መዝገብ ይፈለጋልና [በአድራሻው አፈልላልጋችሁ አቅርቡት] የሚል መጥሪያ ላይ አስፈርመውኝ። በፓሊስ መኪና ወደ ልደታ የፌ/ከ/ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት አቀረቡኝ። ዳንኤል ሺበሺም ከ24 አካባቢ በፖሊስ ቀረበ በችሎት የተሰየሙት ዳኞች የነንግስት ይርጋን መዝገብ ካዩ በኃላ እኛን ጠርተው ትንሽ ተመካከሩና አቶ የሺዋስ አሰፋ የተጠሩት በስህተት ነውና ይቅርታ መመለስ ይችላሉ። አቶ ዳንኤል ሺበሺ ለሰኔ 16 ምስክር ይዘው ይቅረቡ፤ ለአቶ አብርሃ ደስታ መጥሪያ ይድረሰው በማለት አሰናበቱን።” በማለት ውሏቸውን አብራርተዋል።

የቀድሞው አንድነት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ ዳንኤል ሽበሽ  ባለፈው ህዳር ወር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የታሰሩ ሲሆን ከፍተኛ የጤና እክል እንደገጠማቸውና በቂ ህክምናም ማግኘት እንዳልቻሉ ለቅርብ ጓደኞቻቸው መግለፃቸው ይታወሳል።

በሌላ በኩል የአረና ፓርቲ ሊ/መንበር አቶ አብርሀ ደስታ ለዛሬ በፖሊስ ታስረው ፍ/ቤት እንዲቀርቡ ፍ/ቤቱ ያዘዘ ቢሆንም ግልፅ ባልሆነ ምክንያት ዛሬም ለሁለተኛ ጊዜ እንዳልቀረቡ ታውቋል።

  /Ethiopia Nege May 23, 2017/

LEAVE A REPLY