ባህር ዳር ዩንቨርሲቲ ለሁለት ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ሰጠ

ባህር ዳር ዩንቨርሲቲ ለሁለት ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ሰጠ


/ETHIOPIA Nege News/:- በባህር ዳር ዩንቨርሲቲ ለሀገራቸው በጎ አስተዋፅዖ ያደረጉ ላላቸው ሁለት ግለሰቦች የክብር ዶክትሬት ሰጠ

አንጋፋው ባህርዳር ዩንቨርሲቲ በተለያየ መርሀ- ግብር ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች ዛሬ ሲያስመርቅ ለሀገር በጎ አስተዋፅዖ አርድርገዋል በማለት ለዜማ ደራሲው አበበ መለሰና ለመቄዶኒያ መስራች ቢኒያም በለጠ የክብር ደክትሬት ሰጥቷል።

መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል መስራች አቶ ቢኒያም በለጠ ማዕከሉን በመመስረት አረጋውያን ና የአዕምሮ ህመምተኞችን ለመርዳት ከምስት ዓመት በፊት ነበር ቤተሰቦቹ በሰጡት ቤት ውስጥ ትንሽ ሰዎችን በመርዳት ስራውን የጀመረው።በአሁኑ ሰዓት በማዕከሉ ውስጥ ከ1500 በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ህመምተኞች እንደሚገኙም ታውቋል።

በዘመነ ኢህአዴግ እምብዛም ትኩረት የማይሰጠውን “አረጋዊያንና ህፃናትን” መከባከብ፤ አቶ ቢንያም በለጠ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለሌሎች መኖርን በማስተማሩ አርዓያ በመሆኑ የክብር ዶክትሬቱ ይገበዋል የሚሉ ወገኖች በርካታ ናቸው።

ክቡር ዶክተር ቢንያም በለጠ የክብር ዶክትሬቱን ከተቀበለ በኋላ ባህርዳር ዩንቨርሲቲን ካመሰገነ በኋላ በቂ ስራ ሰርቻለሁ ብየ አላስብም፤ ወደፊት መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመተባበር የተሻለ ለመስራት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡ ከጎኑ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን አመ ስግኖ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ላሉ ወጎች ድጋፋቸው እንዳይለየው ጥሪም አስተላልፏል።

ህወሓት/ኢህአዴግ ሀገሪቱን ከመቆጣጠሩ የህፃናትና አረጋዊያን መርጃ ተቋማትን ወደ ወታደራዊ ካምፖች በመቀየሩ ህዝብን ያሳዘነ ጉዳይ እንደነበር ይታወቃል። ለአብነትም ዝዋይ አካባቢ የሚገኘው “ህፃናት አምባን” መጥቀስ ይቻላል።

ሁለተኛው የክብር ዶክትሬት የተቀበሉት አርቲስት አበበ መለሰ ሲሆኑ የእነ ክቡር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰን “ኢትዮጵያ” የተሰኘውን ዘመን አይሽሬ ድንቅ ዘፈን ጨምሮ ሌሎች ከሁለት ሺህ በላይ የዜማ ግጥሞችን በመድረስ ይታወቃሉ።

ክቡር ዶክተር አበበ መለሰ ከአመታት በፊት ሁለቱም “ኩላሊቶቹ “ ከጥቅም ውጭ በሆኑበት ወቅት ኩላሊቱን በመስጠት ከፈጣሪ ቀጥሎ በህይወት እንድኖር ያደረገኝን ወጣት ሳሙኤል ተስፋዬንና ይህን ክብር የሰጠኝን ባህር ዳር ዩንቨርሲቲን አመሰግናለሁ ብለዋል።

ለሀገር አለፍ ሲልም ለአዓለም መልካም ተግባራትን ላበረከቱ ሰዎች “የክብር ዶክትሬት” መስጠት የተለመደ ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥም የተለያዩ ዩንቨርሲቲዎች ለተለያዩ ሰዎች በየዓመቱ ሽልማቱን ሲሰጡ ቆይተዋል። ነገር ግን ሽልማቱ ፖለቲካዊ እየተደረገ የማይገባቸው ሰዎችም በሽልማቱ ይካተታሉ በሚል የአንድ ሰሞን የማህበራዊ ሚዲያ መጨቃጨቂያ እንደሚሆን እናስታውሳለን። የዘንድሮው የባህርዳር ዩንቨርሲቲ ተሸላሚዎች ግን ሁሉንም ያግባቡ ይመስላሉ።

LEAVE A REPLY