የዘንድሮ ኢሬቻ /ማህሌት ፋንታሁን/

የዘንድሮ ኢሬቻ /ማህሌት ፋንታሁን/

የኢሬቻ በዓል ከሚከበርበት እለት 3ት ቀናት ቀደም ብለን ነበር ቢሾፍቱ የገባነው።
በዋዜማዎቹ ቀናት
★★★
በከተማዋ በዓሉን የተመለከቱ ባነሮች በሆቴሎች፣ መንገዶች እና አደባባዮች ሲለጠፉ፤ የባህል ልብሶች፣ ስከርፎች፣ ኮፍያዎች እንዲሁም የተለያዩ ጌጣጌጦች በየመንገዱ እና በየሱቁ ሲሸጡ፤ ገበያውም ሞቅ ብሎ እስከ በዓሉ እለትም ቆይቷል። ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ የበአሉ ታዳሚዎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል። በዓሉ አንድ ቀን ሲቀረው ፤ የኦሮሞ ባህል ልብስ በለበሱ የኢሬቻ በዓል ታዳሚዎች ከተማዋ ደምቃ ነበር፤ አልፎ አልፎም በመንገድ ላይ ጭፈራ ነበረ፤ የበቀለ ገርባ፣ የመረራ ጉዲና፣ የዋቆ ጉቱ እና የሌሎች ኦሮሞ ጀግኖችን ምስል የያዘ የመኪና ላይ ስቲከር መነሃሪያ አካባቢ ሲሸጡ አይተናል፤ የሚሸጡት ልጆችም ጮክ ብለው “የኦሮሞ ጀግኖችን የያዘ ምስል ለመኪና” እያሉ ነበር የሚሸጡት። [እነዚህ ስቲከሮች የበአሉ እለትም በተመሳሳይ መልኩ ሆራ አርሰዲ ድረስ በሚወስዱ መንገዶች ሲሸጡ ነበር] በዓሉ ወደ ሚከበርበት ሆራ አርሰዲ ሃይቅ መግባት አይቻልም። ከተማ ውሰጥም የኦሮሚያ ፖሊሶች በብዛት አልፎ አልፎም የፌደራል ፖሊሶች ይታዩ ነበር። ይህ እና በዓሉ 1 ቀን ሲቀረው ከመንግስት የተሰጠው መግለጫ ህዝቡ እንዲሰጋ እና በበዓሉ ቀንም የሚከሰት መጥፎ ነገር ሊኖር እንደሚችል ፍርሃት ነበር።

የበዓሉ እለት
★★★
የኢሬቻ በዓል ተሳታፊዎች ከለሊቱ 10 ሰአት ጀምሮ ነው ወደ ሆራ አርሰዲ እየጨፈሩ ማለፍ የጀመሩት። ኢሬቻ የሚከበርበት ሆራ አርሰዲ ለመሄድ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ከመሆኑ በፊት ደርሰናል። አየሩ ዝናባማ ነበር። ጠዋት ቢሆንም በመንገዳችን በቡድን በቡድን ሆነው እየጨፈሩ ይሄዳሉ። ስንደርስ ወደ ሃይቁ መግቢያ ጋር ያለው የበዓሉ መድረክ ላይ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች የተወሰኑት ተቀምጠው የተቀሩት ቆመው ይታያሉ። ሆራ አርሰዲ ደርሰን ስንመለስ ዝናብ ማካፈት ጀመረ። መድረኩ ላይ የጭፈራ ድምፅ ይሰማል። መድረኩን ቄሮዎች ተቆጣጥረውታል። የገዳ ምልክት የሆነው ባለ ጥቁር ቀይ ነጭ ባንዲራን ሰቅለዋል። ጭፈራው የሳባቸው በአካባቢው የሚገኙ የነበሩ ወጣቶችም ወደመድረኩ ተቀላቅለው ለመጨፈር ተመሙ። ዝናቡ እየዘነበ ነው። ካፍታ ቆይታ በኋላ “Down down weyane” የሚል በጋራ የሚሰማ መፈክር ከመድረኩ ይሰማ ጀመር። መድረኩ አካባቢ የነበሩ ወጣቶቹ ወደ መድረኩ መሄዳቸውን ቀጠሉ። “Down down weyane”!!! ይህን መፈክር መድረኩን ከሞሉት ወጣቶች ሙሉ ይሰማ ነበር። የምናየው እና የምንሰማው አስደነቀን። ዝናቡ እየዘነበም ቢሆን በቡድን እየጨፈሩም ሆነ በተናጠል ወደ ሆራ አርሰዲ የሚደረገው ጉዞ አልተቋረጠም።

የኦሮሚያ ፖሊሶች ፍተሻ ቦታ ላይ ከፎሌዎች ጋር ሆነው ከመፈተሻቸው ውጪ በአሉ በሚከበርበት አካባቢ አልነበሩም። እንደ አምና እና ካቻምናው በጠነከረ መልኩ ወደ ሆራ ከሚሄዱትም ሆነ ከሚመለሱት “ያ ወያኔ!” ፣ “እምቢ! አንገዛም” ፣”በቃን!” የሚሉ መፈክሮች በብዛት ተሰምተዋል። ለተፈናቀሉ እና ለተጎዱ ወገኖች በተቀናጀ ሁኔታ እርዳታ ሲሰበሰብ ነበር። እነ በቀለ ገርባ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ጃዋር፣ ግርማ ብሩ እና ሌሎችን በስም እየጠሩ አወድሰዋል። “በቀለ ገርባ እና ዶ/ር መረራ ጉዲና ያስተዳድሩን” ፣ “መንግስት ራሱ አሸብሮ፤ ንብረታችንን መሬታችንን ሰርቆ እኛን አሸባሪ ይላል” ፣ “ጃዋር የኛ ኦኤም ኤን የኛ”፣ “ቻው ቻው ወያኔ!” ብለዋል— ቄሮዎች። የበቀለ ገርባን ምስል በትልቁ የያዙ ወጣቶች በርከት ብለው፤ በቀለ እንዲፈታ ሲጠይቁ እና መፈክር ሲያሰሙ ነበር።

ጠዋት የበዓሉ መድረክ ላይ በመደነቅ የሰማነው “Down down weyane” መፈክር፤ ቀኑን ሙሉ በየመንገዱ እና ሆራ አርሰዲ ሃይቅ ጋር ሲሰማ ነው የዋለው። አምና አንድ ጀግና ወጣት ያስጀመረው “Down down weyane” መፈክር ብዙ ሺህ ወጣቶች ሲሉት ነበር። ባለቤትነቱ የእውቁ ባለሃብት ዲንቁ ደያሳ የሆነው ሪፍት ቫሊ ኮሌጅ በር ላይም በስፒከር የተለቀቁ የተቃውሞ እና ሌሎች የኦሮምኛ ዘፈኖች ተከፍተው በርካቶች ተሰባስበው ሲዘፍኑ ፣ ሲጨፍሩ ነበር። ከቀኑ ወደ 10 ሰአት አካባቢ ሲሆን የኦሮሚያ ፖሊሶች በጭነት መኪና ሆነው ከተማዋን ሲዞሩ በዙሪያቸው ያሉ ምስጋናቸውን በጭብጨባና በጩኸት ሲገልፁ አይተናል።

ከሞላ ጎደል በጥቂቱ እይታ ይህን ይመስል ነበር የዘንድሮ ኢሬቻ። ድሮም በሰላም ያልቅ የነበረውን በዓል አምና መንግስት ራሱ በሰላም እንዳያልቅ ካደረገ በኋላ “በሰላም ተጠናቀቀ” እያልን እንድንገረም እና እንድንደሰት መሆኑ በጣም ያበሳጫል። አምናም አንድም ሰው መሞት እማይገባ እንደነበር እና የአምናውን ስህተት አጉልቶ ያሳየ ሆኖ ነው ያለፈው የዘንድሮ ኢሬቻ።

ክብር አምና በኢሬቻ በአል ላይ መንግስት በወሰደው እርምጃ ለተሰዉ!

/September 2017/

LEAVE A REPLY