በአማራና ቅማንት ማህበረሰብ መካከል የተደረገው የህዝበ-ውሳኔ ውጤት ዛሬ ይፋ ተደረገ

በአማራና ቅማንት ማህበረሰብ መካከል የተደረገው የህዝበ-ውሳኔ ውጤት ዛሬ ይፋ ተደረገ

/ኢትዮጵያ ነገ አማርኛ ዜና/፦ እራሱን የ“ፌዴሬሽን ምክር ቤት” በማለት የሚጠራው የህወሓት ጉዳይ አስፈፃሚ ተቋም ለዘመናት በመከባበር አብሮ የኖረውን የአማራና የቅማንት ማህበረሰብን በመካከላቸው ቁርሾ ለመፍጠርና ለሁለት ለመክፈል ሲሰራ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን 42 ቀበሌዎችን ያለ ህዝብ ፍላጎት “የቅማንት አስተዳድር” በማለት ሲያካልል በ8 ቀበሌዎች ደግሞ ህዝበ-ውሳኔ መስከረም 7/2010 ዓ.ም ማድረጉ ይታወሳል። 7ቱ ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳድር መሆንን ሲመርጡ፤ በቆላ ድባ ወረዳ ስር የምትገኘው ሎምየ የተባለች ቀበሌ አዲሱን የቅማንት አስተዳድርን መቀላቀል እንደመረጠች በወቅቱ ተገልጿል።

ይሁን እንጂ በሎምየ በተካሄደው የህዝበ-ውሳኔ ምርጫ እድሜያቸው ለምርጫ ያልደረሰና ያልታወቁ መራጮች በመሳተፋቸው ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉም ተዘግቧል። ህወሓት ከጀርባ በመሆን ይመረዋል ተብሎ የሚታመነውን የሁለቱን ማህበረሰብ የመከፋፈል አጀንዳ ከፍተኛ ተቃውሞ አሁንም ድረስ እየቀረበበት ይገኛል።

ምርጫ ቦርድ የህዝቡን ውሳኔ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በላከለት መሰረት “ሰባቱ ቀበሌዎች በነባሩ አስተዳደር እንዲቀጥሉ፤ አንዱ ቀበሌ ደግሞ በአዲሱ የቅማንት አስተዳደር እንዲጠቃለል” በማለት ምክር ቤቱ መወሰኑን የደረሰን መረጃ ጠቁሟል።

ለፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የኢህአዴግ ህገ-መንግስት በክልሎች ወይም በሁለት ግዛቶች መካከል ለሚነሱ አለመግባባቶች መፍትሄ የመፈለግ ሀላፊነት የተሰጠው ቢሆንም የሚፈጠሩትን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል እንቅስቃሴ ሲያደርግ አይታይም።በአማራና ትግራይ መካከል፣ በትግራይና አፋር ፣በኦሚያና ጋምቤላ፣ በኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ እንዲሁም በቅርቡ ከ200 ሰዎች በላይ የሞቱበትና ከ200 ሺህ በላይ ሰዎች የተፈናቀሉበት የሶማሌና የኦሮሚያ ክልሎች ግጭት ተጠቃሽ ነው።

LEAVE A REPLY