የአቶ በረከት መልቀቂያ ዜናና የሕወሐት ሴረኝነት /ኢ/ር ይልቃል ጌትነት/

የአቶ በረከት መልቀቂያ ዜናና የሕወሐት ሴረኝነት /ኢ/ር ይልቃል ጌትነት/

አሁን ባለንበት ሁኔታ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ከባድ ችግር ውስጥ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን ድርጅቱ ያለበትን የውስጣዊ ችግር የእድገት ደረጃ በጥሞና ለመረዳት እያንዳንዱን ክንዋኔ በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ የውስጣዊ ድርጅት ሽኩቻውን በአጠቃላይ ሀገራዊ ፖለቲካ ፋይዳው ጋር ሚዛን በመስራት ለእውነት የተጠጋ ትንተና ላይ ለመድረስ ሁለቱን ማለትም የድርጅት ውስጣዊ ሽኩቻውንና ሀገራዊ ፋይዳውን ሚዛን ላይ አስቀምጦ ማየት ያስፈልጋል፡፡

ሕወሐት እጅግ ሚስጥራዊ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱን የመምራት ኃላፊነትም በእነሱ ትክሻ ላይ መውደቁን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ በዚህ ሁሉ ሀገራዊ ምስቅልቅል ውስጥ የአቶ በረከትን መልቀቂያ ይፋ ማድረግ ለምን አስፈለገ? ለዚህ ጥያቄ ለእውነት የቀረበ መልስ ለማግኘት ሁለት መላምቶችን ማቅረብ ይቻላል፡፡
አቶ በረከት የድርጅቱ ጭንቅላት እንደሆኑ ይታመናል፡፡ አቶ አባዱላ የይስሙላ ፓርላማም ቢሆን በዓለም አቀፍ ግኝኙነት ደረጃ ሲታይ የነበሩበት ቦታ ትልቅ ገፅታ ነው፡፡

የእነዚህ ባለስልጣኖቸ መልቀቅ ሕወሐት/ኢሕአዴግ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞና ሁሉንም ነገር መቆጣጠር አቅቶት ባለስልጣኖቹ ተስፋ በመቁረጥና በመደናገጥ ሀገራዊ ኃላፊነት መውሰድ የማይችሉበት ደረጃ ላይ በመድረሳቸው በግላቸው እየወሰኑ ነው ማለት ነው፡፡

በመሆኑም እነዚህ ትልልቅ ባለስልጣኖች በእንድ ጊዜ ስልጣን መልቀቃቸው ከፍተኛ ችግር መኖሩንና ለሀገራዊ የፖለቲካ ለውጥ መቃረባችንን መገመት ይቻላል፡፡

ሌላው በአሁኑ ሰዓት ኦህዴድ ከሕወሐት የበላይነት በብዙ መልኩ የማፈንገጥ አዝማሚያና በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር አጀንዳ መጋራትና የአላማ መደበላለቅ አለ ብሎ ሕወሐት ያምናል፡፡ የአባዱላ ገመዳ መልቀቅና ለመልቀቁ የሰጠው ምክንያት የኦሮሞን ህዝብ ለማነሳሳትና አባዱላ የህዝባዊ እንቅስቃሴው ቀጥተኛ ያልሆነ መሪ /informal leader/ ለመሆን በኦሮሞ ፖለቲከኞች የተቀነባበረ ነው በሚል ሕወሐት ይህንን የድርጅት ሽኩቻ ሚዛን ለማስጠበቅ የአቶ አባዱላን መልቀቅ በህዝብ ዘንድ በተለይም በማህበራዊ ሚዲያው ያገኘውን የዜና ሽፋን ለመበረዝና በአባዱላ ምክንያት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረውን የፖለቲካ ትኩሳት ዝቅ አድርጎ ማሳየት ስለነበረበት አቶ በረከት በተመሳሳይ ሁኔታ ከስራ እንዲለቁና የዜና ሽፋኑን እንዲቆጣጠረው አድርገዋል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡

ይህንን ግምት የሚያጠናክረው ሕወሐት እጅግ ሚስጥራዊ ድርጅት መሆኑ፣አቶ በረከት ይሰሩበት የነበረው ቦታ ከህዝብ ገፅታ የራቀ በመሆኑ ዜናውን በአሁኑ ደረጃ ይፋ ሳያደርጉ በዝግታ መልቀቅ የሚችሉበት እድል ሰፊ በመሆኑ፣አቶ በረከትም በድርጅቱ ውስጥ ያላቸው ቦታ ከፍተኛና ሴራን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው፣በድርጅትም ሆነ በሀገራዊ ፖለቲካ የእሳቸው መልቀቅ ዜና ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ጠንቅቀው የሚያውቁ በመሆናቸው ድርጊቱ ታስቦና ታቅዶ የተደረገ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

በፖለቲካ ስራ ውስጥ አንድ ከባድ አደጋ ሲያጋጥም ያንን ዜና ለመሸፈንና አቅጣጫ ለማስቀየር አዳዳዲስ ዜናዎች ፈጥሮ አቅጣጫ ማስቀየርና ችግሩን ለመፍታት ትንፋሽ የማግኛ ዘዴ አድርጎ መጠቀም የተለመደ ተግባር ነው፡፡

ለማጠቃለል አሁን ያለው እውነታ በተራ ቁጥር 1 ተገለፀው ከሆነ ሀገራችን በፈጣን የለውጥ ማዕበል ላይ ስለሆነች ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን በጥንቃቄና በአስቸኳይ ከባድ ሀገራዊ ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ያለው እውነታ በተራ ቁጥር 2 ላይ የተገለፀው ከሆነ የውስጥ የድርጅት ሽኩቻ ለትግሉ ከፍተኛ አስተዋፆ ቢኖረውም ጊዜ የሚሰጥና በተረጋጋ ሁኔታ አስቦ ትግሉን ለመምራት የሚቻልበትን ዕድል ይፈጥራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

LEAVE A REPLY