ንጉሠ ነገሥት የሌላቸው የኢትዮጵያ ንገሦች /ይገረም አለሙ/

ንጉሠ ነገሥት የሌላቸው የኢትዮጵያ ንገሦች /ይገረም አለሙ/

አይተዳደርም ሁለት ኮርማ አንድ ቤት አንዱ ተሸንፎ ካላለ አቤት አቤት” ውርሰ ቃል

በዘመነ መሳፍንትም በሉት በፊውዳሉ፣ በአጼውም ይሁን በወታደራዊው ወይንም በተጋዳላዮቹ በየትኛውም የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ዘመን አንድም በህገ ሥርዓቱ አለያም በጉልበቱ የነገሠ ንጉሰሠ ነገሥት ነበር፡፡ በመሆኑም በየአካባቢው ራሱን የሚያነግሰውም ሆነ በንጉሠ ነገሥቱ የሚሾመው ንጉሥ እንዳሻው አይሆንም፡፡ ሥልጣኑ ገደብ ኃላፊነቱ ልክ አለው፡፡ጡንቻው ህሊናውን አደንዝዞት፣ አለያም ከማን አንሼ እብሪት ተጠናውቶት ራሴ ንጉስ ነኝ የምን ለንጉስ ማደር ነው ብሎ ያሻውን ለመስራት ቢሞክር፣ ትዕዛዝ አልቀበል አላከብር ማለት ቢዳዳው በንጉሰ ነገስቱ ትዕዛዝና ውሳኔ አንድም በህግ እንዲያም ካለ በጉልበት አቅሙን እንዲያውቅ ልኩን እንዲረዳ ይደረጋል፡፡
አቶ መለስ ግለሰብም ፓርቲም መንግስትም በነበረበት ዘመን ለጠቅላይ ገዥነት ለንጉሠ ነገሥትነት የመብቃቱ ምክንያት ለሥልጣን ከነበረው ስሰትና ሌባ እናት ልጇን አታምንም እንዲሉ ሆኖበት የፈጸመው በመሆኑ ያደረሰው ጥፋት ጥሎት የሄደው የከፋ ሥርዓት ከኢትዮጵያ እንዲህ በቀላሉ የሚነቀል አይደለም፡፡

ሰውየው በህግ ባልተጻፈ በድርጅታቸውም ውሳኔ ባላገኘ አቆላልፎ የመግዛት ተንኮል ሴራው ከሁሉ በልጦ ሁሉን በርቀት አቁሞ ሲሻው እንደ ባለሥልጣን እያስጠገና እያዘዘ ሲሻው ደግሞ ከደጅ አስቁሞ እንደ አሽከር እያመናጨቀና በአደባባይ ጭምር እያዋረደ ንጉሰ ነገስት ሆኖ ለመኖሩ ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ሊክደው የሚችለው አይደለም፡፡ ሆድን በጮማ ቢደልሉት፣ መንፈስን በአልኮል ቢያደነዝዙት ህሊና የሚባለው ነገር እንደ ሙጀሌ መነዝነዙ አይቀርም፡፡

የአቶ መለስን እኩይነት በቁሙ ከምናውቀው ከሞቱ በኋላ የተረዳነው ይበልጣል፡፡ እኛ በተቃውው ጉራ የተሰለፍነው አይደለንም ከህውኃት ጀምሮ በየደረጃው አባልም አጋርም የሚል መሸንገያ የተሰጣቸው ሁሉ አደባባይ አውጥተው አይናገሩት እንጂ የመለስ ተንኮልና ሴራ ግልጽ ብሎ የታያቸው ከሞቱ በኋላ ይመስለኛል፡፡

የተነሳሁት ስለ መለስ እኩይነት ለመጻፍ አይደለም፣ብዙ የተባለበትም ነው፡፡ አሁን በኢትዮጵያ የሚታየው ንጉሠ ነገሥት አልባ ንጉሥነት የመለስ ስራና ሴራ ውጤት መሆኑ ነው ከመለስ እንድነሳ ያስገደደኝ፡፡ የመለስን ስራና ሴራ መለስ ብሎ ላጤነው ሲሻው ሀገሪቱ በጠቅላላ ስርዓት የሚባል ነገር የሌለባት ያስመስላታል፤ሲሻው ንጉሠ ነገስት የሌላቸው ንጉሦች ያሻቸውን የመሚያደርጉበት ፍጹማዊ ሁኔታ ያለ በማስመሰል ይጠቀምባቸዋል ብቻ ሳይሆን እየጠለፈ ለመጣልም ይጠቀምበታል፡፡በምንም ተአምር ግን ንጉሰ ነገስትነቱን አያስደፍርም፡፡ለመደፋር የሞከሩት እነ ስዬ እና ተወልደ የደረሰባቸው ግዜው ሩቅ አይደለምና አይረሳም፡፡

ዛሬ የኢትዮጵያ የመንግሥትነት ታሪክ ከመሰረቱ ተለውጦ እነማን መሆናቸው አይደለም ጭራሽ ቁጥራቸው የማይታወቅ የሚታዩም የማይታዩም አንድም እራሳቸውን ያነገሱ ሁለትም ከእነርሱ ፍርፋሪ በሚከጅሉ አጨብጫቢዎች አጋፋሪዎችና አዳናቂዎች እየታጀቡ እኔም በቦታዬ ንጉስ ነኝ ያሉና ለመሆንም የሚዳዳቸው፣ ያለምንምና ማንም ሀይ ባይነት ኢትዮጵያን እያመሷት ህዝቡንም ቁም ስቅሉን እያሳጡት ነው፡፡

ሁለት ዝሆኖች ሲራገጡ ሳሩ መጎዳቱ ባይቀርም አንዱ ማሸነፉ ስለማይቀር ከተራራ ላይ ሆነህ ተመልከት ፍልሚያው ሲያበቃ አሸነፊው መድከሙ ስለማይቀር ያኔ በትኩስ ጉለበት አሸናፊው ላይ ጉብ ማለት የሚል አባባል መኖሩ ቢታወቅም የእኛ ንጉሰ ነገስት አልባ ንጉሶች ማንነታቸውም ሆነ ብዛታቸው ብሎም የትነታቸው ስለማይታወቅ እንደዝሆኖቹ ምሳሌ እስኪለይላቸው ብሎ ለመጠበቅ የሚቻል አይደለም፡፡ እንደውም አንዳንዶቹ ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው ስራቸውን የሚያከናውኑት በሌሎች በመሆኑ እነርሱ ተለይተው ሳይታወቁ ሀገርና ህዝብ ሊያልቁ ይችላሉ፡፡

ለዚህ ቀላሉና የቅርብ ማጣቀሻ የሚሆነን የአቶ በቀለ ገርባ ጉዳይ ነው፡፡ አቶ በቀለ በዋስ እንዲፈቱ የወሰነው ጠቅላይ ፍርድ ቤት እዛ ውሳኔ ላይ የደረሰባቸውን ህጋዊ ምክንያቶች በዝርዝር ገልጹዋል፡፡በመሆኑም እንኳን ተወካይ እየላከ ችሎቱን የሚከታተለውና የውሳኔው ግልባጭ የሚደረድሰው ማረሚያ ቤት ቀርቶ ዜናውን በመገናኛ ብዙሀን የተከታተለው ሁሉ በቀላሉ የሚረዳው ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ክሱ ከሽብር ወደ መደበኛ ህግ ተቀይሮ እየተከራከሩ ባሉበት ጉዳይ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ ከታሰሩት ግዜ በላይ የማስያፈርድባቸው በመሆኑ የሚለው አጽኖኦት የሚሰጠው ነው፡፡ እንደው የጉዳዩን እንዴትነት ይበልጥ ለማሳየት ይህን አልኩ እንጂ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ካልተስማማው አቃቤ ህግ ይግባኝ ይጠይቃል እንጂ ማረሚያ ቤት ፍርድ ቤት ያሰናበተውን ታሳሪ አልቅ የሚልበት ወይንም ፍርድ ቤቱን ሽቅብ ተጠራርቶ ማብራሪያ የሚጠይቅበት ምንም የህግ መሰረት የለም፡፡ አለ የሚል ካለ በመጮህ ሳይሆን አንቀጽ ጠቅሶ ያስረዳ፡፡

የዳኝነት ሥልጣን የሚለው የህገ መንግሥቱ አንቀጽ 79 በንዑስ አንቀጽ 1 “ በፌዴራልም ሆነ በክልል የዳኝነት ሥልጣን የፍርድ ቤቶች ብቻ ነው” ይልና በቁጥር 2 ላይ ደግሞ “በየትኛውም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማናቸውም የመንግስት አካል፣ ከማንኛውም ባለሥልጣን ሆነ ከማንኛውም ሌላ ተጽኖ ነጻ ነው” በማለት በማያሻማ ቃል የሚገልጠው ህገ መንግሥት ይህን ብሎ ብቻ ሳያበቃ በንዑስ ቁጥር 3 ላይ “ ዳኞች የዳኝነት ተግባራቸውን በሙሉ ነጻነት ያከናውናሉ፤ ከህግ በስተቀር በሌላ አይመሩም” ይላል፡፡ የቂሊንጦው ባለሥልጣናት ተግባር እነዚህንና መሰል የህገ መንግሥቱ አንቀጾች የሚረጋግጥ ነው፡፡ ታዲያ የዚህ ጽሁፍ አብይ ጭብጥ የሆነው ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ጋር ነው፡፡

ባለሥልጣናቱ የቱንም ያህል በፖለቲካ ቢታበዩ በጥላቻ ቢታወሩ በእብሪት ቢሰክሩ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አቅምም ሞራልም አላቸው ወይ ብለን ብንጠይቅ የምናገኘው ምላሽ አረ እንዴት ሆኖ የሚል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አይደለም ንጉስ መሆን ለመሆንም የሚመኙ አይደሉምና በምን አቅማቸው፡፡ አቅመ ቢስ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን ማመዛዘኛ ህሊና የሌላቸው መሆናቸው ሌሎች እንደፈለጉ የሚጠቀሙባቸው እቃዎች( አድራጎታቸው ይህ ስለሆነ ነው፣ለቃሉይቅርታ) ስላደረጋቸው ከጀርባ ሆነው ለሚሻኮቱት ንጉሶች የመሻኮቻው ሚዳ ሆነው በሜዳው ላይ ያገኙትን ሁሉ ይረግጣሉ ለምን ብሎ የሚጠይቅ ማንነት፤ እንዴት ብሎ የሚጠይቅ ወኔ የላቸውምና ነገ ለፍርድ ሊያስቀርባቸው የሚችል የህገ መንግሥት ጥሰት በገሀድ ይፈጽማሉ፡፡

የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በመናኛ ካድሬ ሲጣስ ዛሬ የመጀመሪያ ሆኖ አይደለም ይህን ማንሳቴ፡፡ በፊት የሚደረጉት ሁሉ በጠቅላይ ገዢው በንጉሰ ነገስት መለስ ስለነበር ድርጊቱም አድራጊውም አስደራጊውም በግልጥ ይታወቅ ነበር፡፡ ለምሳሌ በአጋጣሜ ተገኝቼ የአይን ምስክር ለመሆን የበቃሁበት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ችሎት በዋስ የተፈታው ስዬ የችሎቱ ውሳኔ ተጥሶ ታፍኖ ተመልሶ ወደ እስር ቤት የተላከው ጠባቂዎቹ ከአቶ መለስ በደረሳቸው የራዲዮ ትዕዛዝ ነው፡፡ የበቀለ ገርባን ግን ማን ሊሆን ይችላል ብለን ብዙ ንጉሶችን እያነሱ ከመጣል ባለፈ እገሌ ነው ብሎ መናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ስሙን ካነሳሁ አይቀር ደጋግሜ በጋዜጣ ጠይቄው ያለመለሰልኝን ጥያቄ ለስዬ ላቅርብ፡፡ የአፈና መዋቅሩን ከአደራጁት አንዱ ነህና እንዴትና በምን ሁኔታ ለምንስ ዓላማና ግብ ብታዘጋጁት ነው አንተን ከዶሮ ማነቂያ አፍኖ ለመውሰድ የቻለው? አንተን “ጦርነትን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መስራትም የምትችለውን” ቀንደኛ ህውሀት ከመንገድ አፍኖ ለመውሰድ የበቃ የአፈና መዋቅር ለሌላው ዜጋ ይበገራል ብሎ ማሰብ እንደማይቻል እየታወቀ ይህን በመጽኃፍም ያለማንሳትህ ለምን ይሆን ?

ንጉሰ ነገስት አልባ ንጉሶች ለመበራከታቸው ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ቢቻልም ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው፡፡ከወራት በፊት በሶማሊ እና በኦሮምያ ክልሎች መካካል የተቀበረውን የመለስ ቦንብ አፈንድተው ሲራኮቱ የሁለት ሀገር ግጭት እንጂ በአንድ ፌዴራል ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክልሎች፣ በአንድ ንጉሰ ነገስት የሚመሩ ንጉሶች አይመስሉ እንደነበር ታዝበን አልፈናል፡፡ ግን ግን እናንተዬ ስኳር ነጋዴው ንጉስ የትኛው/የትኞቹ ሆነው ነው እኛ በ60 ብር ኪሎ ስኳር አጥተን በህገ ወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ስኳር የጫኑ መኪናዎች በቀያችን አያልፉም ባሉ ዜጎች ላይ አምቦ ላይ ጥይት እንዲዘንብባቸው ለማድረግ የቻሉት፡፡ እነዚህ ላቅ ያለ ሥልጣን ያላቸው መሆን አለባቸው፡፡ እንደው መቼስ ይሆን የሀገራችን ታጣቂዎቸ ካነገቱት መሳሪያ የሚሻሉ የሚሆኑት? እኛስ መቼ ይሆን ግፉ ጎፍንኖን በወያኔ መገዛት በቃን አራት ነጥብ የምንለው፡፡( በቃል ሳይሆን በተግባር በስሜት ሳይሆን በእምነት)

እነዚህ እየተደራደርን ነው የሚሉን ምን ብለን እንደምንጠራቸው የቸገሩን የዘመናችን ጉዶችስ ከየትኛው ንጉስ ወይንም ንጉሶች ጋር ይሆን የሚደራደሩት? ሊነግሩን ይችላሉ፡ ጉዶች ማለቴ ነገር ለማካበድ ብዬ አይደለም፣ አይነት ብዛታቸው የማይታወቁት ንጉሶቻችን በሥልጣናችን አትምጡ እያሉ ከሚፈጽሙት ግድያ አልፈው ምንስ ወዴትስ ብንነግድ ምን አገባችሁ ማን ሆናችሁ ነው የእኛን መኪና መንገድ የምትከለክሉ ብለው ጦር አዝምተው ግድያ ከፈጸሙ ሰዎች ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር ይህንንም እንደ ጀብዱ ማውራት ጉዶች ሊያሰኛቸው የሚችል ሆኖ ስለታየኝ ነው፡፡

ሌላው አስገራሚ የእኛ ነገር ራሳቸውን ካነገሱት ወይንም ለማንገስ ከሚጣጣሩት መካከል ንጉስ ምርጫ መያዛችን ነው፡፡ አንድ ሰሞን አንዱን የብአዴን ሰው ማሞካሸቱ ጣራ ነክቶ ነበር፡፡ ምን ቢያሰማምሩት ብረት ወርቅ አይሆንም እንዲሉ ያ ብዙ የተባለለት ሰው መሆን የሚችለው ራሱን እንጂ የሚባለውን አይደለምና የሆነውን ሆነ፡፡ ሰሞነኛው ተሞጋሽ ባለ ሳምንት ደግሞ ከኦህዴድ ሆኗል፡፡ ይህም በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ ወይንም ሰልፋችን ከዚህ ነው ከሚሉት ውስጥ ግልጽ ዓላማና ግብ የሌላቸው መኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

LEAVE A REPLY