ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ በስደት ከዚህ አለም በሞት ተለየ

ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ በስደት ከዚህ አለም በሞት ተለየ

ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ከዚህ አለም በሞት ተለየ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ ከዚህ አለም በሞት ተለየ።ጋዜጠኛ ኢብራሂም በኬንያ ስደት ላይ በነበረበት ወቅት በጋጠመው ህመም ትናንት ሮቡዕ ከዚህ አለም በሞት ተለይቷል።ኢብራሂም በበርካታ የስፖርት ጋዜጦች ላይ በመስራት የሚታወቅ ሲሆን አሁን ከህትመት ውጭ በሆኑት ማራቶን፣ ኢትዮ ስፖርት ጋዜጣና አዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ሰርቷል። በ1997 ዓ.ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ በተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ታስሮ መንግስት ባደረሰበት ከፍተኛ ስቃይ ጉልበቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት እስካሁን ሲሰቃይ መቆየቱ ታውቋል።

ኢብራሂም ይሰራበት የነበረው “አዲስ ጉዳይ መጽሄት” በ2006ዓ.ም በመንግስት ልዩ ትዕዛዝ ከሌሎች ጋዜጦችና መጽሄቶች ጋር ከተዘጋና የተለያየ ጫና ከደረሰበት በሗላ ለስደት እንደተዳረገ ይታወቃል።

ኢትዮጵያ ነገ ድረ ገጽ ባልደረቦች የተሰማንን ጥልቅ ሃዘን እየገለጽን ለመላቤተሰቡ ወዳጆቹና ለመላለሙያ አጋሮቹ መጽናናትን እንመኛለን!

አድማስ ሬዲዮ፦ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ በበርካቶች ዘንድ ይታወቃል። በአገር ቤት በጋዜጦች፣ መጽሔቶችና በሬዲዮ የስፖርት ተንታኝነቱ ይታወቃል። ላለፉት በርካታ ዓመታት ከአገር በስደት ወጥቶ በኬንያ ይኖር ነበር። በደረሰበት ህመም ሲታከም ቆይቶ፣ ትናንት ረቡ ዕ ህይወቱ ማለፉ ተነግሯል።

በቅርብ የሚያውቀው አቤል አለማየሁ፣ ኢብራሂም ሻፊን እንዲህ ይገልጸዋል።

“በጥቁር እና ነጭ መለያ ለባሾቹና በአለን ሺረር ፍቅር የነደደ ነው።በእንግሊዝ ብ/ቡድን ፍቅር ያበደ ነው። አንድ ብቅ ስላለ ኮከብ እንግሊዛዊ እንደ እንግሊዝ ሚዲያዎች ሁሉ እሱም ጆሮህን እስኪዝል ይጨቀጭቅሀል። ከኢብሮ ጋር ሳወራ ዓይኑን ስለሚያጉረጠርጥብኝ እንግሊዞች ላይ የሚያተኩሩ መረጃዎችን ለማጣጣል እፈራለሁ።

የተማረውን ፖለቲካ የመተንተን ብቃቱ መልካም ቢሆንም ውሎና አዳሩ ግን እግር ኲስን ሲያላምጥ ነው። ከኢብሮ ጋር እግር ኲስን ማውራት ዕይታን ያሻሽላል። የአ.አ. ዩኒቨርስቲን ቡድን ያሰለጥን ነበር። ከብዙ አሰልጣኞች የተሻለ የሜዳ ላይ እግር ኲስን የማንበብ፣ የመረዳትና የማስረዳት አቅሙ የላቀ ነው። ለስላሣ ፊት ይኑረው እንጂ ብዕሩ ሸንቊጭ ነው። በስደት ባለበት ኬኒያ አልጋ ላይ ሆኖ ከህመም እየታገለ እንኲን ፌስቡክ ላይ ሀሳቡን ያንፀባርቅ ነበር።

በአንድ ወቅት በህመም ውስጥ ሆኖ ገንዘብ እንዲዋጣለት በስደት ያሉ ጒደኞቹ ሲያማክሩትና በአገር ቤት ላለው ኃላፊነት ደውለው ሲያወያዩ ስሰማ እምቢተኝነቱን ስለማውቅ “መጀመሪያ ራሱን ጠይቁት” ብዬ ነበር። ምላሹም No! ሆነ። “ሁሌ የሚያመኝ ነው ይሻለኛል” አለ። ኢብሮ እንደዚህ ነው። ስሙን ለገበያ ማዋል አልፈለገም። (በእርግጥ በውጪ አገር የሚገኝ ወንድሙ ይንከባከበው እንደነበር ሰምቻለሁ።) እንደነገሩኝ ከሆነ በአንድ ወቅት መንቀሳቀስ ባለመቻሉ የነበረበትን የሜዲካል ምርመራ ሄዶ ማድረግ ስላልቻለ እንጂ እንደሌሎች ባልደረቦቹ ወደ ሌላ አገር መሻገር በቻለ ነበር። ተሽሎት ፕሮሰሴን አጠናቅቃለሁ ብሎ ሲያስብ ሞት ቀደመው።

ዛሬ ሞትን ለማርዳት በነበረ የፌስቡክ እሽቅድምድም ላይ ሰዉ ሲራኮት ቂርቆስ የነኢብሮ ቤት ግን መጥፎውን ክስተት ስላልሰሙ ፀጥታ ወርሶት እንደነበር ወዳጄ ነግሮኛል።

በርካታ እግር ኲሰኞችን እና የስፖርት ጋዜጠኞችን ባፈራችው ቂርቄስ የበቀለው ጋዜጠኛ ኢብራሒም ሻፊ የቀድሞው ማራቶን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረ ሲሆን በኢትዮ ስፖርት ጋዜጣ እና አዲስ ጉዳይ መጽሔት ወርቃማ ጊዜ ነበረው። ሸገር ላይ የቀጥታ የእግር ኲስ ስርጭት ላይና ‘እንዳልክ እና ማኅደር’ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይም ሠርቷል።”

ነፍስ ይማር !!

LEAVE A REPLY