ሰሙነኛው – 1 /ያሬድ ሹመቴ/

ሰሙነኛው – 1 /ያሬድ ሹመቴ/

አንድ በገጠር የሚኖር እረኛ አባቱን ትምህርት ቤት እንዲያስገባው ይጠይቀዋል። አባትየው ደግሞ ልጁ ከብት እንዲያግድ እንጂ ትምህርት እንዲገባ አልፈለገም። ታዳጊው አባቱን በተደጋጋሚ ቢጨቀጭቅም ሊሳካለት አልቻለም።

በኋላ ላይ አንድ ዘዴ መጣለት ‘ጥሩ ከብት ጠባቂ አይደለም’ ለመባል ሲል፤ ቀኑን ሙሉ ግጦሽ ላይ አሰማርቶ ካዋላቸው ከብቶቹ መሀል እርጉዟን ላም ለብቻዋ እየነዳ ወንዝ አሻግሮ ጥሏት ይመለሳል። የቀሩትንም ከብቶች እየነዳ ወደቤቱ ይሔዳል።

አመሻሽ ላይ ከብቶቹ ወደ በረት ሲገቡ ለመውለድ የደረሰችዋ ላም መጉደሏን አባትየው አወቀ። ልጁንም “የት ሔደች?” ሲል ይጠይቀዋል። ልጁም “እኔ እንጃ” ሲል ይመልሳል። ምሽቱን ጭስ ቤት ውስጥ አስገብቶ በተመረጠ አርጩሜ ሲገርፈው ያመሽና በእናቱ አታካች ገላጋይነት ወደ መኝታ መደቡ ሄዶ ይተኛል።

ልጁም ሌሊቱን ሙሉ የግርፋት ሰንበሩን እያሻሸ ሲያለቅስ ያድራል። በማግስቱም እንደወትሮው ከብቶቹን ከቤቱ ይዞ ሲወጣ አንዲት ትንሽ ጊደር እበረቱ ውስጥ በገመድ አስሮ ትቷት ይወጣል።

ቀኑን ሙሉ ግጦሽ አሰማርቷቸው ያዋላቸው ከብቶች ይዞ ወደ ቤቱ ሲመለስ ጊደሯ በረሀብና በጥማት ተዝለፍልፋ ይደርሳል። አባትየውም ይህንን ስራውን ካየ በኋላ እየጎተተ ወደ ጭስ ቤት ይዞት ይገባል። እጁን የፍጥኝ አስሮ ሲገርፈው ያመሽና እዚያው እንዳሰረ ትቶት ወደ መኝታው ይሔዳል።

በንጋታው ከእስሩ ሳይፈታው እዚያው ትቶት ከብቶቹን ራሱ እየነዳ ወደ መስክ ይዟቸው ይሔዳና ለጎረቤቶቹ አደራ ሰጥቶ ወደ እርሻው ይመለሳል። ሙሉ ቀን ታስሮ በርሀብ ጭምር ሲሰቃይ የዋለው ታዳጊ አመሻሹ ላይ አባቱ ወደ ቤት እንደተመለሰ እንዲፈታው ይማጸነዋል። ነገር ግን አባትየው ከናካቴው “አንተ የምትፈታው በአባትህ መቃብር ላይ ነው” ሲል እራሱ ላይ ሳይቀር አሟረተ። እናቱም ብትሆን ከቁጠኛው አባቱ ልታድነው ባለመቻሏ እያዘነች ልጇ ላይ ጨከነች።

በዚህ ሁኔታ የሚበላውን ምግብ እናቱ እያጎረሰችው እንደታሰረ ወሎ አደረ። ቀናትም ነጎዱ።

ከእለታት አንድ ቀን አንድ የምስራች ቤታቸው መጣ። ታዳጊው ማመጽ በጀመረበት እለት ወንዝ አሻግሮ ትቷት የተመለሰው ላም የነፍስ አባታቸው አግኝተዋት ኖሮ ቤታቸው ወስደዋት ወልዳ ከርማ ከነጥጃዋ ወደ ቤታቸው መለሷት።

ለቀናት ታስሮ የሰነበተው ታዳጊ በነፍስ አባታቸው ሸምጋይነት በማግስቱ ከእስሩ እንደሚፈታ ተነገረው። የዚህ ግዜ ታዳጊው የነፍስ አባታቸውን በእናቱ አማካኝነት ካስጠራቸው በኋላ እንዲህ ሲል ጠየቃቸው።

“አባ ለምንድነው ነገ ትፈታለህ የተባልኩት? ትፈታለህ ሳልባል ለምን አልፈታም?” ሲል ጠየቀ

“እኔ እንጃ ምክንያቱን አላውቅም አባትህ ነው የሚያውቀው ልጄ” ብለው መለሱ

“አባቴ እኔን የሚፈታኝ በድጋሚ ጥሩ እረኛ እንድሆንለት ስለሚፈል ነው ወይ?”

“ምን አውቄ ብለህ ነው ይሄንን!” አሉ ግራ ገብቷቸው።

“እንግዲያውስ እርስዎ ለምን ሸመገሉ?” ሲል ይጠይቃቸዋል።

“አንተን ከስቃይ ማዳን፤ እናትህን ከሰቀቀን ማትረፍ፤ እና አባትህን ከቁጭት ማዳን፤ ምን ክፋት አለው ልጄ?” አሉት። ታዳጊውም ትንሽ ካሰበ በኋላ እንዲህ አላቸው።

“አባቴ ነገ እኔን ሊፈታኝ የፈለገው፤ የማሰርና የመፍታት አቅሙን ሊያሳየኝ እና ወደ እረኝነቴ ሊመልሰኝ እንጂ ቀድሜ የጠየቅኩት ትምህርት ቤት ሊያስገባኝ አይደለም። እና ደግሞ እናቴ ነገ እኔ ስፈታላት እልል ብላ ደስታዋን መግለጿ ስለማይቀር አባቴ ቤተሰቡ ሁሉ የተደሰተ ሊመስለው ይችላል። እርሶም ቢሆኑ ሲለማመጡት ውለው በመጨረሻ እንደሚፈታኝ ስለነገርዎት ደስ ብሎዎት ወደ ቤትዎ ይገቡ ይሆናል። እኔ ግን ነገ ስፈታ የፊጥኝ እስሩ ብቻ እንደሚቀርልኝ እንጂ ፍላጎቴ እንዳልተሟላ እናንተ አይገባችሁም።” ሲል ተናገረ።

የነፍስ አባትየውም እንዲህ አሉት “ልጄ! መጀመሪያ ብትፈታ እና ከዚያ የሚሆነውን በሂደት ብናየው አይሻልም?” አሉት።

ልጁ ግን እንዲህ ሲል መለሰ “ከተፈታሁ በኋላ ግን መልሶ እንደማያስረኝ በግዝት ይሰሩልኝና ይፍታኝ። አልያ ግን ትምህር ቤት ሳልሔድ መቅረቴን ከእስር በመፈታት ብቻ አምኜለት የምቀመጥ ከመሰለው መሳሳቱን ይንገሩልኝ” አላቸው።

ነፍስ አባትየውም አባቱን ለማናገር እየወጡ በሩ ላይ እንደቆሙ ዞረው የፊጥኝ የታሰረውን ልጅ እያዩ እንዲህ አሉት። “ልጄ አባትህ ይህንን የጭስ ቤት ሊዘጋው አስቧል። እንዲያውም ከዚህ በኋላ ያንተ መታሰሪያ እንደማይሆን ነግሮኛልና እንኳን ደስ አለህ” አሉት።

ልጅየውም እንዲህ ሲል መለሰላቸው። “ጭስ ቤቱን ከዝጋ በኋላስ የጊደሯን መታሰሪያ በረት ለኔ እንደማያደርገው በምን አወቁ?” አላቸው

ነፍስ አባትየው “ሆ ሆ በል ደህና ሁን። የዛሬ ልጆች ጥያቄያችሁ አያልቅ”

፨፨፨፨፨
(ይቀጥላል)

LEAVE A REPLY