የህዝበ ሙስሊሙን ትግል እና የኢህአዴግ ሰራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ

የህዝበ ሙስሊሙን ትግል እና የኢህአዴግ ሰራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ

የህዝበ ሙስሊሙን ትግል እና የኢህአዴግ ሰራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባን አስመልክቶ የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

‹‹የመንግስት ችግሮች ዋነኛ ሰለባ ሕዝበ ሙስሊሙ በመሆኑ የለውጥ ሂደቱንም በቅርበት ይከታተለዋል!!››

————————————–

ታህሳስ 30/2010 አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ

አገራችን ኢትዮጵያ ከባለፉት 6 አመታት ወዲህ በተለየ ሁኔታ መረጋጋት ተስኗት እንደቆየች ይታወቃል፡፡ የመረጋጋት እጦቱ ዋነኛ ምንጭ ደግሞ ከመንግስት መዋቅራዊ ድክመትና ብልሹ አሰራር የተነሳ ከጊዜ ወደጊዜ እየሻከረ የመጣው የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት ነው፡፡ በመሰረቱ በመንግስትና በህዝብ መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ህዝብ እንደዜጋ በአገሩ የሚጠበቅበትን ግዴታ በመፈጸም፣ መንግስት ደግሞ አገርና ህዝብን የማስተዳደር ኃላፊነቱን በፍትሐዊነት በመወጣት መርህ ላይ የሚገነባ ግንኙነት ነው፡፡ የመንግስት መዋቅሮች በየደረጃው ኃላፊነታቸውን መወጣት ሲሳናቸው ግን ዜጎች አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡም ቢሆን የዜግነት መብታቸው ዋስትና አያገኝም፡፡ ሰላማዊ አየር የመተንፈስ እድልም አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህም ዜጎች የትኛውንም ዓይነት የፍትህ ጥያቄ ሲያቀርቡ ሰላማዊነትን ቢከተሉ፣ ታጋሽነትንም ቢላበሱ መሻሻል የማይታይበት የመንግስት መዋቅራዊ ችግርና አቅጣጫ የሳተ ፖሊሲ የህዝብና የመንግስት ግንኙነትን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መውሰዱ አይቀሬ ነው፡፡

የመንግስት አገርን በህገ መንግስቱ መሰረት የማስተዳደር አቅም እጦትና ብልሹ አሰራር በቀጥታ ተጽእኖ ካሳደረብን የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ግንባር ቀደሞቹ ነን፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ ላይ የተዘረዘሩት የድርጅቱ ችግሮች በሙሉ ሰለባ ነበር፤ እንደሆነም ይገኛል፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ከሚጋፈጣቸው ችግሮች በተጨማሪ መንግስት ህግና ስርዓትን በሚጥስ አሰራር በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የዜጎችን የመረጡትን እምነት የመከተል መብት በይፋ የሚቀናቀን እርምጃ ወስዷል፡፡ ኋላ ላይም በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ፊት አውራሪነት ዋነኞቹ የአገሪቱ ህግ ተርጓሚ እና ህግ አስፈፃሚ ተቋማት ከህግ ውጭ አካሄድ የመረጡበት መንገድ በወቅቱ መንግስት በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎታል፡፡

ባሳለፍናቸው 6 ዓመታት የህግ አስፈፃሚ እና የፀጥታ አካላት በዜጎችና በመንግስት መካከል ሊኖር የሚገባውን በጎ ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ በጥላቻ እና መጠራጠር ላይ እንዲወድቅ አድርገውታል፡፡ ህዝብ መንግስትን የማያምን፣ መንግስትም በዜጎቹ ጉዳይ ኃላፊነት የማይሰማው ባእድ ሆነው እንዲቀጥሉ አድርገውታል፡፡ ይህ ጤናማ ያልሆነ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት መንግስትን ‹‹ለሁሉም ችግሮች መፍትሄ የኃይል እርምጃ ብቻ ነው›› ከሚለው እምነቱ ሊያወጣው ባለመቻሉ ከጊዜ ወደጊዜ ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ከፍተኛ የሆነ መቃቃር ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገ ሲሆን ውዲቷ አገራችንንም አሁን ወደምትገኝበት ቀውስ ገፍቷታል፡፡

ሙስሊሙ ማህበረሰብ የሚጠይቀው ህገ መንግስታዊ መብቱን ሆኖ ሳለ መንግስት ግን ለማስተናገድ ፍቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በወቅቱ አገራችን ከነበረችበት አንፃራዊ ሰላምና ፈንድቶ የወጣ ተከታታይ የህዝብ ጥያቄ አለመኖር አንፃር ሲታይ መንግስት የሙስሊሙን ጥያቄ የመመለስ አቅምም ጊዜም እንደማያጣ መገመት አይከብድም ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በመሩት የስራ አስፈፃሚና ማእከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እንደ ህዝብ ጥያቄ በጠረጴዛ ላይ የነበረው አንድ አጀንዳ የሙስሊሙ ጥያቄ መሆን ችሎ የነበረ ቢሆንም መፍትሄ ሊሰጡት ግን አለመፍቀዳቸው የሚታወስ ነው፡፡ ይህም የሆነው ሰሞኑን በወጣው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ እንደተጠቆመው ስልጣንን የህዝብ ማገልገያ ከማድረግ ይልቅ ውርስ አድርጎ የመውሰድ እሳቤ ህዝብን መናቅና ለጥያቄው ጆሮ መንፈግን በማምጣቱ በሂደት የተፈጠረ ነው፡፡

ከዚያ በቀጠሉት ጊዚያት ህጉን አክብሮ ሊያስከብር የሚጠበቅበት መንግስት ዋነኛው የህግ ተላላፊና ዜጎችን በህገ መንግስቱ ላይ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርግ አካል ሆኖ እንደቀጠለ ሁሉም ያስተዋለው ጉዳይ ነበር፡፡ በእስር ቤትና በፍርድ ቤት ሂደት ውስጥ የታዩ የሐሰት ምስክሮች፣ የዳኞች መድልኦ እና የእስረኛ አያያዙ የፍትህ ስርአቱን ወደሌላ ተጨማሪ የእንግልትና የጭቆና መሳሪያነት መቀየራቸውን መስካሪ ነበሩ፡፡ ምእመናንን ከመስጂድና ከየቤታቸው እያፈኑ በመውሰድ ይደርስ የነበረው ድብደባ፣ ዘረፋ እና ፆታዊ ጥቃት መንግስት በህዝብ ዘንድ በጎ ምስል እንዲያጣ አድርጎታል፡፡ በተለይም የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ዛሬ ላይ እንዲዘጋ ውሳኔ ባሳለፈበት ማእከላዊ በሚባለው የማሰቃያ ስፍራ በህዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና አብረዋቸው የታሰሩ አጋሮቻቸው ላይ የደረሱ ግፎች ከህዝብ ጆሮ መድረሳቸው የፈጠረው ተፅእኖ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም፡፡

በዚህ ሁኔታ መንግስት ያልተረዳው ትልቅ እውነታ ግን ህዝበ ሙስሊሙ ሰላማዊ ትግሉን ያደርግ የነበረው የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በማያይበትና በማይሰማበት ሁኔታ ውስጥ እንዳልነበረ ነው፡፡ ምናልባትም መንግስት የሙስሊሙን ጥያቄ በመግፋትና በኃይል በመድፈቅ ‹‹የተቀረው ኢትዮጵያዊ የሚያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎች ሳይነሱ አስቀድሜ ተስፋ ማስቆረጥ እችላለሁ›› የሚል የተሳሳተ ግምት ወስዶ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆነው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡

የሙስሊሙ ሰላማዊ ትግል ጥያቄዎቹ ንፁህ የፍትህ ጥያቄ መሆናቸውን በተግባር በማሳየት ዜጎች ያሏቸውን ቅሬታዎች በምን አግባብ ሊያቀርቡ እንደሚገባ መልክ ማስያዝ ችሏል፡፡ ጥያቄው ፍፁም አገራዊና ህገ-መንግስታዊ መሆኑን ለዓመታት በዘለቀው ሰላማዊ ትግል በተግባር አሳይቷል፡፡ ለዘመናት ሲነዛ የኖረውና መንግስትም በተደጋጋሚ ሰላማዊ ትግሉን ሌላ መልክ ለመስጠት ይጠቀምበት የነበረውን የሙስሊሙን እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ከአገራዊነት ይልቅ ዓረባዊነት መልክ የመስጠቱን ፕሮፓጋንዳ እርቃን አስቀርቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄያቸው በኢትዮጵያ ማእቀፍ ውስጥ ብቻ እና ብቻ መልስ እንዲያገኝ ባደረጉት በመስዋእትነት የተመላ ትግልም ለመላው ህዝባችን መልካም ተምሳሌት ሆኗል፡፡ በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አስቀድሞም መልካም አርአያ የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ ሙስሊሙ ባደረገው ትግል የተጓዘበትን ጎዳና እና ለሰላማዊ ትግል ሲል ያሳየውን በፅናት የታጀበ ትግል በመረዳት የዜጎች መብት የሚከበርባትን አገር ለመገንባት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ሰላማዊ የትግል መንገድን በመከተል ዓላማውን ሊያሳካ እንደሚችል የህዝብ ለህዝብ ተሞክሮ በመወራረስ አገራዊነቱን አጠናክሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት የአንድን የህብረተሰብ ክፍል ውስን የመብት ጥያቄዎች ለመመለስ አለመፍቀዱ ህዝብ የራሱን መብት በራሱ የማስከበር ጉዞ ካልጀመረ በስተቀር መንግስት በዜጎቹ ጉዳይ ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑን ግምት እንዲወስድ የገፋበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

በቀጣይ ዓመታት ህዝቡ ፍትሐዊ ጥያቄ ማቅረቡን ሲቀጥል የመንግስት አካሄድ ግን ከጊዜ ወደጊዜ አቅጣጫውን እየሳተ መሄዱን ነበር የቀጠለው፡፡ በአገራችን የህግ የበላይነት አለመኖሩና መንግስትም ኃላፊነቱን መወጣት እንደማይችል በዜጎች ዘንድ እምነት ማደሩ ዜጎች የሚያነሱት እያንዳንዱ ጥያቄ ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ እንዲያመራ ማድረጉ በተለይ ባለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት በስፋት ተስተውሏል፡፡ በየአካባቢው፣ በዋናነትም በኦሮሚያ ክልልና አንዳንድ የአማራ ክልል ከተሞች በተነሳው ፍትሐዊ የህዝቦች የመብት ጥያቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ውድ ህይወታቸውን ተነጥቀዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሳይከሰት ችግሩን በመነጋገርና ለፍትሐዊ ጥያቄዎች ፍትሐዊ ምላሽ በመስጠት መግታት ይቻል ነበር፡፡ ግና ችግሩን ወደ አገር አቀፍ አመፅነት ያሳደገው ዋናው እንቅፋት መንግስት ራሱ ዘግይቶም ቢሆንም ባመነው መልኩ የተስተዋለው የአመራሩ አቅም እና ፍላጎት አለመኖር፣ አለፍ ሲልም መንግስት ከህዝብ ጋር እልህ መጋባቱ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

በህገ መንግስታዊ አግባብ እልባት ሊያገኙ የሚገባቸው የህዝብ የመብት ጥያቄዎች ሌላ ስር የሰደደ ችግር ለመውለዳቸው ዋነኛው ተጠያቂ መንግስት መሆኑ በስራ አስፈፃሚው መግለጫው በግልፅ ተጠቅሷል፡፡ ፌዴራላዊ ስርዓቱን በህገ-መንግስቱ መሰረት የመተግበር ፍላጎት አለማሳየቱም ለዘመናት በአብሮነት የኖሩ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ግጭት ቀስቅሷል፡፡ በዚህ በአመራሩ ኃላፊነት አለመወጣት ምክንያት የተቀሰቀሰውን ግጭት በህዝባዊነት ስሜት ለመፍታት ይህ ነው የሚባል ጥረት ሳይደረግ መቆየቱ በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ታይቶ የማይታወቅን የዜጎች ከቀያቸው መፈናቀልና ሞት አስከትሏል፡፡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበውን ሪፖርት ብቻ ብንወስድ እንኳን ከ700 ሺህ በላይ ዜጎቻችን ለረጅም ጊዜያት ከኖሩበት ቀዬ መፈናቀላቸው መላው ህዝባችንን በአገሩ ላይ ተስፋ ያስቆረጠ ከባድ ክስተት ነበር፡፡ ከሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈናቀሉና በግጭቱ ሰበብ ህይወታቸውን ያጡ ዜጎቻችን ጉዳይ ሁላችንንም ያሳዘነ ሲሆን እስካሁንም እልባት አለማግኘቱ አገራችን ወዴት እያመራች እንደሆነ እንኳን በአግባቡ ለመረዳት የማያስችል አደገኛ አለመረጋጋት አስከትሏል፡፡

በአካባቢው የተፈጠረው የዜጎች ሞት እና መፈናቀል እንደማንኛውም ዜጋ ከሚያሳዝነንም በላይ እንደሙስሊም ደግሞ በቀጥታ የሚመለከተን እና ለአፍታም ችላ የማንለው የወገኖቻችን ችግር ነው፡፡ ወገኖቻችንን ለሞትና መፈናቀል የዳረጉ፣ እንዲሁም የሁለቱን ወንድማማች ህዝቦች አብሮነት ያደፈረሱ አካላት ለፍርድ ሲቀርቡ ማየትንም እንደማንኛውም ዜጋ እንፈልጋለን፡፡

ህዝብ ላይ የደረሱ ተደራራቢ በደሎች የፈጠሯቸው ያልተቋረጡ የህዝብ ትግሎች መንግስት በዜጎች ላይ ያደረሰውን በደል እና እንደ መንግስት የፈጸማቸውን ጥፋቶች ቢዘገይም እንዲያምን አድርገውታል፡፡ በቀላሉ መፍትሄ ሊያገኙ የሚችሉ ችግሮችን በየደረጃው ለመፍታት አለመፍቀድ ችግሮች ተከማችተው የመንግስትን ስልጣን እና የገዢውን ፓርቲ እንደ አንድ ድርጅት የመቀጠል ህልውና የሚፈታተኑበት ደረጃ ላይ አድርሶታል፡፡ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ መነጋገርን ያልፈቀደው መንግስት ጉዳዩ የአገርም የስልጣንም ህልውና ደረጃ በደረሰበት ወቅት ሙሉ አቅሙን በዚያ ላይ አድርጎ ይገኛል፡፡ የመንግስት ባለስልጣናትና አመራሮች በወራት እድሜ በየእርከኑ በስብሰባና በግምገማ ተጠምደዋል፡፡

ቀድሞ የህግ አስፈፃሚዎች ለትዝብት እንዲጋለጥ ያደረጉትን የመንግስትን ገመና ዛሬ ከፍተኛው የመንግስት አመራር በአደባባይ እየመሰከረው ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር አገራችን የለየለት ቀውስ ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ ባለችበት በዚህ ወቅት ችግርን መረዳትና ለመፍታት ቁርጠኝነት ማሳየት አማራጭ የሌለው እንደመሆኑ መጠን የሰሞኑ መንግስት መግለጫ እንደ በጎ እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

መንግስት አካሂደዋለሁ የሚለውን የለውጥ ጉዞ መዳረሻ የሚወስኑት የችግሮችን ስር መሰረት መለየት መቻል እና ችግሮቹን ለመፍታት የሚኖረው ቁርጠኝነት ናቸው፡፡ በመሆኑም አሳሳቢው ጉዳይ ሁኔታውን የስልጣን ጉዳይ ብቻ አድርጎ በመውሰድ የስልጣን ላይ እድሜን ለማራዘም ያለሙ የጥገና ለውጦችን ማምጣት መፍትሄ እንደማይሆን ማወቁ እና ዋናዎቹን ችግሮች ችላ በማለት የችግሮቹን መገለጫዎች በማከም አገራዊ ቀውስን በዘላቂነት ማስተካከል እንደማይቻል መረዳቱ ነው፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ከመሰረታዊ የዜግነት መብቶቹ በተጨማሪ እንደ አንድ የእምነቱ ተከታይ ለዓመታት የታገለላቸው አጀንዳዎች ዛሬም መልስ የሚሹ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ሙስሊሙ የሃይማኖት እና የመንግስትን መለያየት በተግባር ማየት ይፈልጋል፡፡ የትኛውንም ዓይነት ሃይማኖታዊ አመለካከት ተከታዮቹ በነፃነት እንዲያምኑ ከመፍቀድ ባለፈ የመንግስትን ትከሻ ተደግፎ በህዝብ ላይ እንደማይጫንበት ማስተማመኛ ይፈልጋል፡፡ በእምነት ነክ እንቅስቃሴዎች እና በተቋም ግንባታ ሂደት በየጊዜው የሚታዩ ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ እገዳዎች ህገ ወጥ በመሆናቸውም ፈጽመው እንዲነሱለት ይፈልጋል፡፡ የአገሪቱ ግማሽ አካል የሆነው ሙስሊሙ ማህበረሰብ ይህ ነው የሚባል ተቋማዊ መብቶች የሌሉትና ተቋሞቹም በመንግስት አይዞህ ባይነት ከህዝቡ ተነጥለው ህዝቡን በመከፋፈልና በማስጠቃት ተግባር ላይ መሰለፋቸውን ማስቆም ይፈልጋል፡፡ ለዘመናት ከአገራችን ባህልና ታሪከ ጋር የተቆራኘውን ህዝባችንን በስጋት የመሳል አካሄድ እንዲቆምም ይሻል፡፡ ይህ ለሙስሊሙም ለአገራችንም የተሻለው አካሄድ ነው፡፡

የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ያሳለፋቸው ውሳኔዎች አተገባበራቸው በሂደት የሚታይ ሆኖ በጥቅሉ በመልካም እርምጃነት የሚወሰዱ መሆናቸውን በድጋሚ ማስታወስ እንወዳለን፡፡ የተነሱት አብዛኛዎቹ አጀንዳዎች ህዝበ ሙስሊሙ ለዓመታት ሲጠይቃቸው የነበሩና መንግስትም ሊመልሳቸው ሲችል ፈቃደኛ ያልነበረባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከዚህ አንጻር መብት በመጠየቃቸው ብቻ ከህግ አግባብ ውጭ ፖለቲካዊ ክስ እየተለጠፈባቸው የታሰሩ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች በየቦታው እየማቀቁ ያሉ ታሳሪዎችን መፍታት የመንግስትና የህዝብን ግንኙነት ለማሻሻል አንድ መነሻ ተግባር ነው፡፡

በአገራችን የመደራጀት ነፃነት እንዲጎለብት ቢደረግ ዜጎች በተደራጀ መልኩ ለራሳቸውና ለአገራቸው በሚበጁ ተግባራት ላይ የሚሳተፉበትን እድል ይጨምራል፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት ከማንም በላይ ተጠቃሚ የሚያደርገው አገራችንን ነው፡፡ ፍትህ ከዳቦ ባልተናነሰ ሁኔታ ማስፈለጉን እንደገመገመ የገለፀው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለፍትህ መስፈን ልዩ ትኩረት ቢሰጥ ለአገራችን መልካም ስም፣ ለህዝባችንም እፎይታ ያመጣል፡፡ የመንግስት ዋነኛ ተግባርና ኃላፊነት የዜጎችን ፍላጎት ማሟላት እንጂ ዜጎችን በሁሉም አጀንዳዎችና እርከኖች በመጠርነፍ ነፃነታቸውን መንፈግ ባለመሆኑ ያንን አሰራር ማስቀረት ከተቻለ በመንግስትና በህዝብ መካከል የሚኖረው ግንኙነት እየተሻሻለ ይሄዳል ብለን እናምናለን፡፡

የትኛውም ህዝብ ከአገሩ ፀብ የለውም፡፡ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለው ግንኙነትም ሰዋዊ የውዴታና የጥላቻ ግንኙነት አይደለም፡፡ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነት በዜጎችና ዜጎችን ለማስተዳደር ኃላፊነት በተሸከመው አካል መካከል ያለ አስተዳደራዊ ግንኙነት ነው፡፡ ግንኙነቱን እና አጠቃላይ አገራዊ መግባባቱን የሚወስነውም የአስተዳደራዊ ግንኙነቱ የጤናማነት ደረጃ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተን ማስታወስ እንወዳለን፡፡ የህዝብ ጥያቄ ለህግ ተገዥ የሆነ መንግስት እና ሁሉንም ዜጎች በፍትሐዊነት ተጠቃሚ የሚያደርግ ምሉእ እድገት የሚታይባትን ኢትዮጵያ ማየት ነው፡፡ ይህንን ትግሉንም መንግስት የትኛውንም ጥያቄ ለመስማት ፍቃደኛ ባልሆነበት አስቸጋሪ ወቅትም ቢሆን ቀጥሏል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ለዓመታት ያደረገው ትግል በአገራችን ኢ-ፍትሐዊነት እንዳይቀጥል የማድረጉ አንድ አካል እንደመሆኑ መጠን ከዚህ በኋላ የሚካሄዱ ተኃድሶዎች ህዝብ በትክክልም ተጠቃሚ የሚሆንበትን የለውጥ መንገድ የሚከፍቱ ከሆነ የህዝበ ሙስሊሙም ጉዞ ይህንን አገራዊ ለውጥ ታሳቢ የሚያደርግ ይሆናል፡፡ በመንግስት ቃል የተገቡት አገር አቀፍ የለውጥ አቅጣጫዎች ወደመሬት እንዲወርዱ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ይህ እውን የማይሆን ከሆነ፣ የህዝበ ሙስሊሙ መሰረታዊ ጥያቄዎችም በተያያዥነት መፍትሄ የማያገኙ ከሆነ ግን ህዝበ ሙስሊሙ ትግሉን በፅናትና በስፋት ይቀጥላል፡፡

በሰላማዊ ትግላችን ወቅት ብዙዎች የታሰሩት፣ የተሰደዱት እና የሞቱት ለተከበረ ዓላማ ነው፡፡ ይህ ዓላማ ደግሞ ከሃይማኖታዊ ቀናኢነት የመነጨ፣ ማንም የማይበደልባትና ፍትህ የሰፈነባትን አገር እውን ሆና ከማየት ታላቅ ዓላማ ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ሙስሊሙ ህዝባችን ባለፉት ዓመታት ለሃይማኖት ነፃነቱና ለአገራዊ መብቱ መከበር ባደረገው ትግል ይኮራል፡፡ ለከፈለው መስዋእትነት ምንዳውን ከአላህ እየጠበቀ ውጤቱን እስከሚያይ በፅናት ይቀጥላል!

LEAVE A REPLY