አራቱ የኦፌኮ አመራሮች ለ2ኛ ጊዜ ተፈረደባቸው

አራቱ የኦፌኮ አመራሮች ለ2ኛ ጊዜ ተፈረደባቸው

~”ጠበቆች ከተነሱ ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም” ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን

/በጌታቸው ሺፈራው/

የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት የድርጅቱ አመራሮች በድጋሜ በችሎት መድፈር ተፈረደባቸው። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት በእነ ጉርሜሳ አያኖ ክስ መዝገብ የተከሰሱትን ጉርሜሳ አያኖ፣ ደጀኔ ጣፋ፣ አዲሱ ቡላላ እና በቀለ ገርባ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባለመነሳታቸው ችሎቱን ደፍረዋል በሚል በአራቱም ላይ የ6 ወር የእስር ቅጣት አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ካልተነሱ ማንነታቸውን መለየት እንደማይቻል በመግለፅ ጠበቆቻቸው መክረው እንዲያስነሷቸው ጠይቋል።

ሆኖም ተከሳሾቹ “ባለፈው በመናገራችን ተቀጥተናል” በሚል አንነሳም ማለታቸውን በጠበቆች በኩል ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል። ተከሳሾቹ ስማቸው በሚጠራበት ወቅት ባይነሱም እጃቸውን ያወጡ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ካልተነሱ የፍርድ ቤቱን ሕግ ስላላከበሩ እርምጃ እንወስዳለን ብሏል። የተከሳሾቹ ጠበቃ አብዱልጀባር ሁሴን በበኩላቸው በፍርድ ቤት ማንነትን ማረጋገጥ የሚያስፈልገው ክስ ሲነበብ እንደሆነ፣ መዝገቡ ለዛሬ ጥር 28/2010 የተቀጠረው ለክስ መስማት (ማንበብ) ሳይሆን ፍርድ ለመስጠት ስለሆነ ጠበቆቹ ከቆሙ ተከሳሾች እንዲነሱ አይገደዱም ብለዋል። ሆኖም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ባለመቆማቸው ምክንያት የፍርድ ቤቱ ሰዓት በ30 ደቂቃ እንደባከኑና ድርጊቱንም ችሎት መድፈር መሆኑን በመግለፅ ውሳኔውን አስተላልፏል።

ተከሳሾቹ ጥር 10/2010 በነበረው ቀጠሮውም በችሎት መድፈር በ6 ወር እስር መቀጣታቸውን አስታውሶ፣ ከባለፈው አልተማሩም በሚል ለ2ኛ ጊዜ የ6 ወር እስር ቅጣት ወስኗል። ጥር 10/2010 ዓም ችሎት ደፍራችኋል በተባሉበት ወቅት በፍርድ ቤት የተናገሩት ተከሳሾቹ ስለዛሬው ውሳኔው አልተናገሩም።

በሌላ በኩል 8ኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ፣ 11ኛ ተከሳሽ በየነ ሩዳ፣ 12ኛ ተከሳሽ ተስፋየ ሊበንና 14ኛ ተከሳሽ ደረጀ መርጋ በቀጠሮው መሰረት ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን ዛሬ በችሎት መድፈር 6 ወር የተፈረደባቸውን አራቱን አመራሮች ጨምሮ በሁሉም ላይ ፍርድ ለመስጠት ለየካቲት 28/2010 ዓም ቀጠሮ ተይዟል።

LEAVE A REPLY