ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸውን አስታወቁ

ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸውን አስታወቁ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፦ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከጠቅላይ ሚኒስትርነትና ከኢህአዴግ ሊቀ መንበርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታወቁ።

ያቀረቡትን የስልጣን መልቀቂያ ጥያቄ የደቡብ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ደህዴን)እና ኢህአዴግ በአውንታዊ መልኩ እንደተቀበላቸው ዛሬ በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። የኢህአዴግ ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለጥያቄያቸው የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚሰጥበትም አክለው ገልጸዋል።

አቶ ኃይለማርያም በሀገሪቱ ለተከሰተው ችግር መፍትሄ ለመስጠት የቻሉትን ማድረጋቸውን ገልጸው፤ አሁን ስልጣን ለመልቀቅ ዋና ምክንያት የሆናቸውም “በሀገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ፤ዋስትና ያለው ዲምክራሲ እንዲሰፍን ለማድረግ የመፍትሔው አካል መሆን አስፈላጊ ነው” ብለው ስላመኑ እንደሆነም ገልጸዋል።

ህዝብ ለሚያነሳቸው በርካታ ጥያቄዎች በርካታ ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ መስጠት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል። አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቦታቸው ሰው እስኪተካ ድረስ በሀላፊነታቸው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል።

የኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ በሚቀጥለው መጋቢት ወር እንደሚደረግ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየ ቢሆንም አንዳንድ ፍንጮች እንደሚያመለክቱት ወደ ነሐሴ ወር ሊዘዋወር እንደሚችል ሲጠቁሙ ሰንብተዋል።

ይሁን እንጂ አቶ ኃይለማርያም የስልጣን መልቀቂያ ማስገባታቸውን ተከትሎ የምክር ቤቱ ስብሰባ በቅርቡ እንደሚደረግ ይጠበቃል።

LEAVE A REPLY