የወልቃይት አማራ ማንነት የኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ

የወልቃይት አማራ ማንነት የኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ

/ኢትዮጵያ ነጋ ዜና/ ፡ – የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ የኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተፈቱ። ሰሞኑን ሲደረግ እንደሰነበተው የፖለቲካ እስረኞችን በተናጠል የመፍታቱ ሂደት ዛሬም ቀጥሎ የወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ የኮሚቴ አባላት፣ በመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ ፍርደኞች መካከል እንዲሁም በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባልነት ተከሰው የነበሩ 4 ወጣቶች መለቀቃቸው ተረጋግጧል።

ከወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ የኮሚቴ አባላት መካከል፦ መብራቱ ጌታሁን፣ አታላይ ዛፌ፣ ጌታቸው አደመና ተሻገር ወ/ሚካኤል ሲፈቱ “በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ተከሰው የእድሜ ልክ ፍርድኛ ከነበሩት መካከል ኮሎኔል ደምሰው አንተነ፣ ኮሎኔል አለሙ ጌትነት፣ ኮለኔል ጌታቸው ብርሌ፣ ኮለኔል ፋንታውን ሙሀባ፣ ሻምበል ተመሰገን ባይለየኝና ዋና ሳጅን የሸዋስ ምትኩ ተፈተዋል።

በአርበኞች ግንቦት ሰባት አባልነት “በሽብር” ተከሰው በእስር ላይ የነበሩት የቀድሞው የአንድነትና ሰማያዊ ፓርቲ አባላት ወጣት ዳንኤል ተስፋየ፣ ኤርሚያስ ፀጋየ፣ ፍሬው ተክሌና ቴዎድሮስ አስፋውም ከቂሊንጦ ወህኒ ቤት መውጣታቸው ታውቋል።

ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ይፈታሉ ተብሎ ከተነገረላቸው መካከል ብርጋዴር ጄኔራል ተፈራ ማሞና ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ እስካሁን አለመፈታታቸው ታውቋል።

LEAVE A REPLY