በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየት /ገለታው ዘለቀ/

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የግል አስተያየት /ገለታው ዘለቀ/

የሃገራችን ፖለቲካ በፍጥነት በሚለዋወጡና አቅጣጫቸውን ለመተመን በሚከብዱ ሁኔታዎች ውስጥ ይዋኛል። ለእነዚህ በፍጥነት ለሚለዋወጡ ፖለቲካዊ ክስተቶች ገፊው ነገር (driving force የምንለው) ምንድን ነው? ካለን በተለይም ላለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ በመካሄድ ላይ ያለው ህዝባዊ ኣመጽ ነው። ይህ ኣመጽ በከፍተኛ ሁኔታ በፖለቲካው ላይ ተጽእኖ እየፈጠረ ነው። በብዙ ሃገራት ህዝቦች በአምባገነን ስርዓት ላይ ሲያምጹ 5 ዋና ዋና ክስተቶች ይፈጠራሉ። ህዝብ እምቢኝ ሲል አገዛዙ መረረኝ ብሎ ሲያምጽ አመጹ ተጽእኖ ፈጥሮበት የሚከሰቱት እነዚህ 5 ጉዳዮች፦

1. በገዢው ፓርቲ ውስጥ መሰንጠቅ፣ መፈረካከስና አለመረጋጋትን ያመጣል።
2. ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያጠነክራል፣ ያበረታታል፣ ያደራጃል፣ ወኔ ይሰጣል።
3. አዳዲስ መሪዎችን ከአመጹ መሃል ያወጣል::
4. የለሂቁን ልዩነት ያጠባል። በህዝቡ ዘንድ ኣንድነትን ያጠነክራል።
5. የዓለምን ድጋፍ ያገኛል ::
እነዚህ ክስተቶች በህዝብ ኣመጽ ጊዜ የሚከሰቱ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህን መመዘኛዎች ይዘን የኢትዮጵያን የሶስት ዓመት ተከታታይ የመረረ ትግል ፍሬ ስንመዝን መጀመሪያ ላይ በጠቅስነው መስፈርት በኩል ከሞላ ጎዳል ተጽእኖው ጎልቶ ይታያል። ገዢውን ፓርቲ ህወሃት ኢሃዴግን በከፍተኛ ሁኔታ ሲመታው ታይቷል። ኢሃዴግ ከህዝቡ ተቃውሞ የተነሳ እንደ ባቢሎን ቋንቋው ሲዘበራረቅ፣ ኣፈ ጉባኤው ሲወድቅ ሲነሳ፣ ስራ ኣስፈጻሚው ለጥፋቱ ሁሉ “ሙሉ ሃላፊነት እወስዳለሁ” ማሩኝ ኣይነት ሲናዘዝ ብዙ ብዙ ሲያደርገው ይታያል። ይህ የህዝብ ማእበል ገዢውን ፓርቲ ክፉኛ ሰንጎ ይዞታል። በርግጠኝነትም ወደፊት በዚህ መልኩ እንዳይቀጥል ኣድርጎታል። የህዝቡ ትግል በዚህ በኩል ጥሩ ውጤት ኣሳይቷል ማለት ይቻላል። ትግሉ ገና ሲቀጥል ደግሞ ገዢው ፓርቲ ኣልማረክም የተባልኩትን ኣላደርግም ብሎ ካመጸ ይህን ፓርቲ እስከ ሃቹ ሊበትነው ይችላል።

ተቃውሞውን ተከትሎ በገዢው ፓርቲ በኩል ለውጦች ኣሉ እንበል እንጂ ታዲያ ለውጡን በጥንቃቀ ማየት በጣም አስፈላጊ ነው። ከገዢው ፓርቲ ኣባል በሆኑት በኦህዴድና በብአዴን ኣካባቢ በተወሰነ ደረጃ ለስላሳ ቃላቶችን መጠቀም ታይቷል። ይህ በርግጥ የህዝብ ተቃውሞ ያመጣው ለውጥ ነው። ይሁን እንጂ ህዝቡ ለሚፈልገው ለውጥ ተስፋ የሚያደርገው እነዚህን ድርጅቶች ኣይደለም። ኢሃዴግ ጥፋቱን ያምንና በምድሪቱ ሰው እንደሌለ በጥልቀት ታድሼ የምቀጥለው እኔው ነኝ ኣይነት ነው ውሳኔው። ለውጡን ከመፍራቱ የተነሳ ከራሱ አባላት መሃል ህዝብ የሚፈልጋቸውን ቋንቋዎች እያናገረ የተበላሸበትን ቅቡልነት (legitimacy) በጥቂቱም ቢሆን ጠጋግኖ እድሜ መግዛት ይፈልጋል። ራሱ ህወሃት በረጅም ገመድ ያሰራቸውን የኦህዴድና የብአዴን ሰዎች ለዚህ ዓላማው ዋና መሳሪያ ኣድርጎ ያያቸዋል። በመሆኑም ህዝቡ ተቃዋሚን ተስፋ እንዳያደርግ ተቃዋሚውን እየመታ ለውጡ ከእጁ ሳይወጣ በቃላት እየደለለ ያለ ምንም መሰረታዊ ለውጥ መዋል ማደር ይሻል።

በቅርቡ በህዝብ ተቃውሞ ሲናጥ የቆየው መንግስት ብዙ እስረኞችን ፈቷል። ሌላው ቀርቶ በኦነግና በግንቦት ሰባት ኣባልነት ተጠርጥረው የተያዙትን ሳይቀር ፈቷል። የኢትዮጵያ ፓርላማ “ኣሸባሪ” ያላቸው ቡድኖች ናቸው እነዚህ ኣካላት። መንግስት ይህን ያህል ከተራመደ በሁዋላ በማግስቱ በመላ ሃገሪቱ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ኣወጀ። ይሄ ኣዋጅ ዓለምን ኣስገርሟል ኣስከፍቷል። መንግስት ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ያወጀበት ምክንያት ኣንደኛ የህዝቡ ጥያቄ ስለገባው ነው። እስረኞችን መፍታት የህዝቡ ጥያቄ ግብ እንዳልሆነ ያውቃል። የሚቀጥለው ጥያቄ ስላስፈራው ነው በድንገት ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ እንዲያውጅ ያደረገው። የህዝቡ ጥያቄ ሃገራዊ መግባባት ይፈጠርና ወደ ምርጫ ገብተን የምንፈልገውን እንምረጥና በመረጥነው እንተዳደር ኢሃዴግ የተባለው ድርጅት በቃን እንደሆነ ገዢው ፓርቲ ተረድቷል። ሁለተኛ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ የሚያሳየው ነገር ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከለቀቁ በሁዋላ ገዢው ፓርቲ ህዝብ ወደሚፈልገው ለውጥ ለመጓዝ እስካሁን ኣለመወሰኑን ያሳያል።

አሁን በሚደረገው የጠቅላይ ሚንስትሩ ምርጫ ምን ኣልባት ከራሱ ኣባላት ውስጥ ትንሽ ቅቡልነት ኣላቸው የሚላቸውን ሊጠቀም ይችል ይሆናል። ያም ቢሆን ግን የህዝቡ ጥያቄ የግለሰቦች ለውጥ ሳይሆን ኣጠቃላይ ሃገሪቱ ሽግግር ያስፈልጋታል ምርጫ እንግባ እስከሚል የሄደ በመሆኑ ማንንም ሾመ ማንን የህዝቡ ጥያቄ እንደማይቆም ስለተረዳ ነው ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ያወጀው። የሚገርመው ግን ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የህዝቡን ኣመጽ ይቀለብሳል ወይ? ብለን መጠየቅ ኣለብን። መቼም እስካሁን ድረስ የተደረጉ አመጾች ሁሉ መንግስት ፈቅዶ ኣይደለም። የመከላከያ ሰራዊት በአራቱም ማእዘን እየዞረ ሰልፈኛውን ሲበትን ሲገድል የነበረው ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ስለታወጀ ኣይደለም። ይህ ኣዋጅ በተግባር የሚያመጣው ለውጥ የለም። ነገር ግን በመርህ ደረጃ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ የሚታወጀው ህዝቡ የፖለቲካ ለውጥ ስለጠየቀ መሆን የለበትም። በመሰረቱ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በዓለም ሃገራት ኣልፎ ኣልፎ ይታወጃል። ለምሳሌ የተፈጥሮ አደጋ ሲገጥም፣ ከፍተኛ ጦርነት ሲመጣ፣ በሰው ሰራሽ ኣደጋ ጊዜ፣ በተላላፊ በሽታ ጊዜ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ይኖራል።

የኢትዮጵያው የመከላከያ ሚንስትር ስለ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ ሲናገሩ የአስቸኳይ ጊዜ ኣዋጁ መነሻ ህገ መንግስቱን ለመጠበቅ ነው ይላሉ። ይህ መነሻ በራሱ መሰረታዊ ችግር ኣለው።በመሰረቱ የኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ማለት የህግ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ህጋዊ የሆነ ህገወጥ ህግ ማለት ነው። ይህ ማለት ህብረተሰብን ከኣደጋ ለመጠበቅ ለጊዜው ከህገ መንግስቱ የተወሰኑትን ኣንዳንድ ኣንቀጾች ለጊዜው መሻር ማለት ነው።። ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ መጀመሪያ የሚሰብረው ህገ መንግስቱን ነው። በርግጥ የማይነኩ ኣንቀጾች ቢኖሩም ከዜጎች የእለት ከእለት ህይወት ጋር የተያያዙ ኣንዳንድ መብቶችን ሰብሮ ይታያል። ይሄ ነው ኣንዱ ዋና ጉዳይ። ህዝብ የመናገር ነጻነቴ ተነካ፣ እኩልነት ኣጣሁ፣ መልካም ኣስተዳደር ኣጣሁ ብሎ ሲጠይቅ ህገ መንግስቱ የሚፈቅደውን መብቴን አጣሁ ነው እያለ ያለው።

ህገ መንግስታዊ መብቴ ይጠበቅልኝ የሚለውን ህዝብ ኣቶ ሲራጅ ህገ መንግስቱን ለመጠበቅ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣውጀናል ቢሉት ራሳቸውን ሰውየውን ግምት ላይ ይጥላል። ህዝብ የታሰሩ ይፈቱ፣ ለውጥ እፈልጋለሁ ሲል አስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ኣይታወጅም። የአሜሪካ ኤምባሲ የዛሬውን ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በጽኑ እቃወመዋለሁ ያለው የኢትዮጵያውያን ጥያቄ የለውጥ ጥያቄ በመሆኑ ይህ ጥያቄ የሚፈታው በአፈና ሳይሆን በነጻ ውይይት የበለጠ ነጻነትን በማጎናጸፍ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው። በርግጥም በመግለጫው ላይ ለኢትዮጵያ መንግስት የመከረው ይህንን ነው። በዚህ ኣጋጣሚ የአዲስ ኣበባው የአሜሪካ ኤምባሲ ያወጣውን መግለጫ ብዙ ኢትዮጵያውያን አድንቀዋል፣ እውነትም ኣሜሪካ ከኢትዮጵያውያን የለውጥ ጥያቄ ጎን በጽናት ቆማለች እንዲሉ ኣድርጓል። የመናገር መብቴ ይከበር ለሚል ህዝብ ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ ሳይሆን ችግሩን የሚፈታው የበለጠ ነጻነት ነው የሚለው የአሜሪካ ኤምባሲ አሳብ ብሩህ ነው።

በዚህ አጋጣሚ የተባበርችው አሜሪካን ክቡር አምባሳደር ማይክል ሬይነርን ከልብ አመሰግናለሁ። ወደፊትም የኢትዮጵያውያን የለውጥ ጥያቄ ምላሽ እስኪያገኝ ከጎናችን እንደሚሆኑ ጥርጥር የለኝም። የኤምባሲው ሙሉ መግለጫ እነሆ
https://et.usembassy.gov/u-s-embassy-statement-ethiopian-governments-declared-state-emergency/

ሁለተኛውን ጉዳይ እንመልከት። በብዙ ሃገራት የህዝቦች ትግል ውስጥ ህዝብ ሲያምጽ ከፍተኛ ሞራል የሚያገኙት፣ የሚነቃቁት፣ በፍጥነት የሚደራጁት ተቃዋሚዎች ናቸው። በዚህ የኢትዮጵያውያን ትግል ወቅት እውነቱን ለመናገር የህዝቡ ትግል ሲያነቃቃው ሞራል እየሰጠው ሲደራጅ ብዙ ኣይታይም። ይሄ ጉዳይ ደግሞ ኣሳሳቢ ነው። ለምን ተቃዋሚው ኣይደራጅም? የህዝቡ ትግል ለምን በሃይል ኣላራመደውም? ካልን ህወሃት ኢሃዴግ በከፍተኛ ሁኔታ ሰርጎ በመግባት ፓርቲዎችን ስላሸመደመደ እስከ አመራር የራሱን ሰላዩች ኣስቀምጦ ስለሚኖር ነው። ኣንደኛው ዋና መንስኤ ይሄ ነው።

መንግስት በመድብለ ፓርቲ ርዓት ከመነሻው ኣያምንም። መድበለ ፓርቲን የሚጠቀምበት ለምእራቡ ዓለም ማታለያ ነው። የኢትዮጵያ ደህንነት ሰራተኛ ዋና ስራ ተቃዋሚን ማዳከም ነው። ህወሃት ኢሃዴግ የለውጥ ጥያቄ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚመጣ ይልቅ ከራሱ ከአባለቱ ቢነሳ ይሻለዋል። ከዚህ ኣያያዙ የተነሳ የህዝቡ ተቃውሞ ያየለውን ያህል ተቃዋሚው ሃይል ሲያገኝ ኣልታየም። ፖለቲካው በዘውግና በአንድነት ሃይል መከፋፈሉም ኣንዱ ሌላ ችግር ነው። የሆኖ ሆኖ ግን ተቃዋሚው ኣልወጣም ኣልታየም ማለት የለም ማለት ግን ኣይደለም። ኣንድ ቀን ነጻ ኣየር ቢፈጠር በጥቂት ወራት ውስጥ እንደ ቅንጅት ኣይነት ፓርቲ ተደራጅቶ ህዛብዊ ተቀባይነት ያገኛል። ሶስተኛው ጉዳይ ከተቃውሞ መሃል ኣዳዲስ ትንታግ ፖለቲከኞች መታየት ኣለመታየታቸው ነው። በ1997 ዓ.ም በነበረው ንቅናቄ ጊዜ ኣዳዲስ መሪዎች ብቅ ብለው የህዝቡን ልብ ማርከው ነበር። ህዝቡም እነዚህን ልጆቹን ሲያይ ጊዜ በፍቅር ወደቀ። ለውጥ ያለ ልክ ፈለገ። ይሁን እንጂ ያ መልካም ኣስተዳደር ዴሞክራሲ የተጠማ ህዝብ ያ የለውጥ ወራቱ ተበላሸበት።

ዛሬ የሚታየውና ለሶስት ዓመታት የቆየው ህዝባዊ ኣመጽ ኣዳዲስ መሪዎችን በማስተዋወቅና በማውጣት በኩል ጉልህ ውጤቱ ኣይታይም። በዓለም ታሪክ ውስጥ የተነሱ ታላላቅ መሪዎች ህዝባዊ አመጽ የወለዳቸው ናቸው። ማርቲን ሉተር ኪንግ ከሲቪል ራይት ንቅናቄ የተገኘ ምርጥ መሪ ነው። ማንዴላ ከንቅናቄ የወጡ ኣመጽ የወለዳቸው ናቸው። የህዝብ ትግል ሲነሳ ኣዳዲስ መሪዎችን ይፈጥራል ይጨምራል። በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ውጤት ጎልቶ ያልታየው እንደተለመደው የህወሃት ደህንነት በተለይ ተኩሮ በዚህ ኣካባቢ ስለሚንቀሳቀስ ነው። ብቅ የሚሉትን እያሰረ፣ ደብዛቸውን እያጠፋ፣ እያሸማቀቀ ስለሚኖር ነው። ይህም ሆኖ ግን ትግሉን እየመሩ ያሉ ቄሮዎች ሲገለጡ ኢትዮጵያውያን የሚኮሩባቸው ናቸው።

አራተኛው ነገር ደግሞ የለሂቁ ክፍፍል መቀነሱ፣ በህዝቡ መካከል ኣንድነት መጠናከሩ መታየቱ ነው። በርግጥ በህዝብ መካከል ከፍተኛ የአንድነት ስሜት ኣይሎ ይታያል። ኣንድ ጊዜ ጎንደር ላይ በነበረ ተቃውሞ ወቅት የኦሮሞው ደም የኔም ነው የሚል ድምጽ ከተሰማ በሁዋላ በኣማራና በኦሮሞ፣ በደቡቡና በሰሜኑ በሁሉም ብሄሮች መካከል ኣንድነቱ ጠንክሮ ይታያል። ይህ የህዝቡ ኣመጽ የሚያመጣው ውጤት ነው። ያለፈው ሶስት ኣመት ኣመጽ ይህን ፍሬ በማሳየቱ ብዙ ሰው ለሃገሪቱ መጻኢ እድል ያለውን ተስፋ ኣብርቶለታል። በሌላ በኩል በለሂቁ መካከል ያለው ክፍፍል መቀነስ ግን ጎልቶ ኣልታየም። በርግጥ የተጀማመሩ ህብረቶች ኣሉ። ይሁን እንጂ እንደ ቅንጅቱ ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የለሂቅ ክፍፍል መቀነስ እስካሁን ኣልተመዘገበም። ለዚህ ችግር መንስኤው ያው የመንግስት የደህንነትና የስለላ መዋቅር በዚህ ኣካባቢ ጠንካራ ቤሆኑ ነው። በርግጥ ታዲያ እያደር እየተሻሻለ መሄዱ ኣይቀርም፣ የስለላውን መረብ እየበጠሰ መጠናከሩ ኣይቀርም ብሎ ማመን ይቻላል።

አምስተኛው ጉዳይ የዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ መማረክ ነው። የኢትዮጵያውያን ትግል በዚህ በኩል ተሳክቶለታል። አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በታሪካችን ባላየነው ልክ ይህን መንግስት እየተቃወሙ ከህዝቡ ጥያቄ ጎን ቆመው ሲታገሉ ይታያሉ። አሁን የወጣውን ኣስቸኳይ ጊዜ ኣዋጅ በተመለከተ የአሜሪካን ኤምባሲ በከፍተኛ ሁኔታ ኣልስማማበትም በሚል ሃይለኛ ቋንቋ አውግዞታል። በዲፕሎማሲው መስክ ያፈራነው ፍሬ በዚህ የሚገለጽ ብቻ ሳይሆን H.Res 128 ህግ ሆኖ ይጸድቅ ዘንድ በአሜሪካ ኮንግረስ በሂደት ላይ ነው። በዚህ ደረጃ የዓለም ኣቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያወያን የመረረ ተቃውሞ ተማርኳል። ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥን ለማምጣት ከፍተኛ ሃይል ነው።በአጠቃላይ የህዝቡን ተቃውሞ ስንገመግም አንድነትን እያጠናከረ፣ በአብዛኛው በብሄሮች መካከል ፍቅርን እያሳደገ ነው የመጣው።

አልፎ ኣልፎ የሚነሱ የብሄር ግጭቶችም በገዢው ፓርቲ ሆን ተብሎ የተቀነባበሩ ተደርገው በህብረተሰቡ መታየታቸው የሚያሻየው ህዝቡ ኣንድነቱን እያሳደገ በዚህ ትግል ውስጥ ኣንድነቱን ጠብቆ ይዞ እንዳለ ነው። ይህ በጎ ርምጃ ሲሆን በሚቀጥለውም የመጨረሻው የትግሉ ምእራፍ ይህ ኣንድነት መጠናከር ኣለበት። በሁለተኛ ደረጃ የፖለቲካው ለሂቅ ከማንኛውም ጊዜ በላይ ሰርጎ ገቦችን እየመነጠረ እያወጣ ክፍፍሉን መቀነስና ለህዝቡ ተስፋ መሆን ኣለበት። ህዝቡ ከኢሃዴግ መሃል ኣንዱ የተሻለ ቋንቋ ሲናገር ያንን ሰው የሚያሞካሸው ተቃዋሚው ተጠናክሮ ስለማያይ ነውና በዚህ ወቅት ተቃዋሚው መጠናከር ልዩነትን ማጥበብ ኣለበት።

ሌላው ጉዳይ አዳዲስ መሪዎችን ማውጣት የህዝቡ ስራ ነው። ታለንት ያላቸውን መሪዎች በተለያዩ ማህበራዊ ኣጋጣሚዎች ማሳደግና መሰባሰቢያ ማድረግ ያስፈልጋል። ፓርቲዎችም ለነዚህ ኣዳዲስ መሪዎች ቦታ መስጠት በኣዳዲስ ኣስተሳሰቦች መራመድ ያስፈልገናል። የዓለም አቀፉ ኮሚኒቲም ትግሉን አጠናክሮ እንዲቀጥል የዲፕሎማሲ ትግላችንን መቀጠል ነው።

LEAVE A REPLY