ሩህሩሆቹ ጓደኞቼ! /ጌታቸው ሽፈራው/

ሩህሩሆቹ ጓደኞቼ! /ጌታቸው ሽፈራው/

ማሂ ቂሊንጦ ልትጠይቀኝ መጥታ እሷም በተሰቃየችበት ማዕከላዊ አንዲት ከሻሸመኔ የመጣች እህታችን የተፈፀመባትን አጫወትኳት። “ባልሽን ካላመጣሽ” እየተባለች ስቃይ ደርሶባት በምርኩዝ ስለምትንቀሳቀስ እህታችን ነበር ያወራኋት። ወሬዬን ሳልጨርስ ቀና ብዬ ሳያት ማሂ እያነባች ነው። ጨዋታ ብቀይርም ስሜቷን መቀየር አልቻልኩም።

በሌላ ጊዜ፣ ልደታ 4ኛ ወንጀል ችሎት ታድመናል። 19ኛ ወንጀል ችሎት ሌላ መዝገብ ስለነበር እና ስንከታተለው የነበረው መዝገብ ስላበቃ ሁላችንም ወጣን፣ ከማህሌት በስተቀር!

ማህሌት 19ኛ ወንጀል ሌላ መዝገብ እንዳለ ብታውቅም ከ4ኛ ወንጀል ችሎት መውጣት አልፈለገችም። ሁሉም ተከሳሾች ወጥተዋል፣ ከአንድ ተከሳሽ በስተቀር! በመሆኑም ይህ ተከሳሽ ብቻውን ያለ ታዳሚ መቅረቱ ጥሩ አልነበረም። ማህሊት ይህን አንድ ተከሳሽ ጉዳይ ለማየት ቀረች። ሌላ ጊዜም ታዳሚ ከሌለ ተከሳሾችን ጥላ አትወጣም። ሌላ ችሎት የምትፈልገው መዝገብ ቢኖር እንኳ ጥላ አትወጣም!

አሁንም ሌላ ጊዜ ነው፣ እሷ የጠዋት ችሎት ተከታትላ ወደ ግል ጉዳይ መመለስ ነበረበት። እኔ ደግሞ ከሰዓት አንድ ችሎት መከታተል ነበረብኝ። ወደ ቤቴ እንድሄድ መከረችኝ። ወደ ቤት መሄድ እንደማልፈልግ ስታውቅ አብራኝ ወደ ችሎት ተመለሰች። ወደ ጉዳዩዋ መሄድ እንዳለበት ብነግራት አልሰማችኝም። የተመለሰችበትን ምክንያትም ብጠይቃትም አልነገረችኝም። ከሰዓት የነበረውን ችሎት ጨረሰን ስንወጣ የተመለሰችበትን ምክንያት ደግሜ ጠየኳት። “ዛሬ አርብ ነው፣ አርብ ደግሞ በአብዛኛው የሚያስሩበት ቀን ነው፣ ብቻህን ካገኙህ ያስሩሃል ብየ ነው” አለችኝ። ስለ ማሂ ሰብአዊነት ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል።

በፍቄ፣ በክፉ ጊዜ ከጎኔ ከነበሩት ጓደኞቼ መካከል ነው። የ4ኛ ወንጀል ችሎት በሆነ ባልሆነው ሲያሸማቅቀን ለእኛ አጋርነቱን ለመግለፅ ፍርድ ቤት ያዘወትር ነበር፣ እኔ ከተሰማኝ በላይ ስለኔ ሲጎዳ አስተውያለሁ! ስለማሂ ሲሰማው አስተውያለሁ!

በፍቄ ለትራንስፖርት የሚኖረኝ አይመስለውም፣ ሁሌም ዝም ብሎ የሚቸግረኝ ይመስለዋል። ፍርድ ቤት ውስጥ የተባለውን ሁሉ አቀርቅሬ ስመዘግብ ስለሚያስተውል ብዙ ማስታወሻዎቼ ከእሱ የተበረከቱልኝ ናቸው። አንደኛው ሳያልቅ፣ ሌላ ገዝቶ ይሰጠኛል።

በእስረኞቹ ጉዳይ የሚደረጉት ዘመቻዎች ግንባር ቀደም ነው፣ የእስረኞችን በደል ለሕዝብ ለማሳወቅ ወደኋላ የማይልሰው ነው!

ስለ እስረኛ አብዘተው የሚጨነቁት፣ ጓደኞቻቸው ይታሰራሉ ብለው የሚጨነቁት ማሂና በፍቄ ዛሬ በእስር ላይ ናቸው!

LEAVE A REPLY