ጠ.ሚ/ትሩ ከተቃዋሚዎች ጋር ተነጋገሩ አረና በትግራይ ጉብኝታቸው የውይይት ጥያቄ አቅርቧል

ጠ.ሚ/ትሩ ከተቃዋሚዎች ጋር ተነጋገሩ አረና በትግራይ ጉብኝታቸው የውይይት ጥያቄ አቅርቧል

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከታዋቂ ግለሰቦች፣ ከሲቪክ ማህበራት ተወካዮችና ከሀይማኖት አባቶች ጋር በብሄራዊ ቤተ-መንግስት ዛሬ ማምሻውን ተወያዩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእራት ግብዣ ሰዓት ባደረጉት ንግግርም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሟላ ፖሊሲን ይዘው በመቅረብ ብቁ ተፎካካሪ መሆን እንደሚገባቸው ማሳሰባቸውን ተገልጿል።

ባለፈው ቅዳሜ በጅጅጋ ትናንት ደግሞ በአምቦ ከተማ ከህዝብ ጋር ውይይት ያደረጉት ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድ ነገ ወደ መቀሌም እንደሚያመሩ ቀደም ብሎ በወጣው ቅድመ ዝግጅት ተገልጿል።

በሌላ በኩል በትግራይ ብቻ የሚቀሳቀሰው አረና ፓርቲ ጠ/ሚኒስትሩ መቀሌን በሚጎበኙበት ወቅት ለማነጋገር የጊዜ ቀጠሮ እንዲያዝለት ለትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በደብዳቤ መጠየቁን አስታውቋል።

ለትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ዶክተር ደብረፅዮን በፃፈው ደብዳቤ በ“ሀገራችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ጉዳዮች፣ በሰብኣዊ መብት አያያዝ፣ የፖለቲካ እስረኞች ከእስር የሚፈቱበት ዕድል እንዲመቻች (በትግራይ እስካሁን የተፈታ የፖለቲካ እስረኛ ባለመኖሩና የዓረና አባላት፣ የደምህት አባላት፣ በኦሮምያ ታስረው የሚገኙ ተጋሩና ሌሎች እንደተቀሩት የሃገሪቱ ዜጎች እንዲፈቱ ለማስረዳት) የፖለቲካ ምህዳሩ በሚሰፋበትና አሳታፊ የሚሆንበት ዕድል እንዲመቻች ከጠቅላይ ምኒስትሩ መመካከር እንፈልጋለን።” በማለት ጠይቀዋል።

በኢትዮጵያ በተለይም ባለፉት ሦስት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩና ሲሰደዱ በትግራይ አንጻራዊ ሰላም የነበረ ቢሆንም አረና ፓርቲ አንደ ህወሓት ፕሮፖጋዲስቶች የትግራይ ተወላጆች በሌላ የሀገሪቱ ክፍሎች ግድያ፣ እስራትና የንብረት ዘረፋ ይደርስባቸዋል በማለት ሲናገሩ ቆይተዋል።

LEAVE A REPLY