ጥቂት ስለአቶ ጽጌ፣ የአንዳርቸው አባት! /በጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ-ከአዲስ አበባ //

ጥቂት ስለአቶ ጽጌ፣ የአንዳርቸው አባት! /በጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ-ከአዲስ አበባ //

የአንዳርጋቸውን አባት (ጽጌ ወ/ማርያም)፣ በአካል የማውቃቸው ከእነብርጋድየር ጀነራል ተፈራ ማሞ ጋር አብረው ታስረው ክስ በተመሰረተባቸው ወቅት ልደታ ፍርድ ቤት ለክስ ሂደቱ ሲመላለሱ ነው – በ2001 ዓ.ም። ያኔ እሳቸው በጽኑ ታመው ነበር። ለፍርድ ቤቱም በተደጋጋሚ ስለጤናቸው ችግር ቢናገሩም የሚሰማቸው አልነበረም። በችሎት ውስጥም መቆም እጅጉን ይከብዳቸው ነበር፤ ስማቸው ሲጠራ።

ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ታስረው አራዳ ፍርድ ቤት ለጊዜ ቀጠሮ ሁሉም ተከሳሾች ሲቀርቡ፤ የነበረው ትዕይንት አይረሴ እና ዘግናኝ ነበር። አስፈሪ ድባብም ነበረው። የፍርድ ቤቱ ግቢ እና ውጪው ጠብ መንጃ በወደሩ ወታደሮችና ፖሊሶች የተሞላ ነበር። የእስረኞች ቤተሰብና ጥቂት ጋዜጠኞችም አንድ ቦታ ተሰብስበን እንድንቆም ይደረጋል። ያው መሳሪያ በቅርብ ርቀት እንደተወደረ! የአቶ ጽጌ፣ ኑኑ የምትባል ልጃቸውም በፍርድ ቤት ቀጠሮ ሁሌ ትገኝ ነበር።

እስረኞቹም በሽፍን ፒክአፕ የፖሊስ መኪናም በማንም ሰው እንዳይታዩ ተደርጎ፣ እጃቸው በካቴና ከመታሰሩ ባለፈ በድጋሚ ከውስጠኛው የመኪናው ብረት ጋር ይታሰሩም ጭምር ነበር። በዚህ ዘግናኝ መንገድ ብቻቸውን ተጭነው የመጡና ሰው እንዳያያቸው መኪናው ፊቱን ወደኋላ ዞሮ ፍርድ ቤቱ በራፍ ጋር በማቆም በድብቅ ችሎት ውስጥ አስገብተዋቸው የጊዜ ቀጠሮ ይጠየቅባቸዋል። ወዲያውም በተለመደው ጥብቅና ዘግናኝ መንገድ ይመለሱ ነበር። በካቴና የታሰሩ እጆች በድጋሚ ከመኪናው ብረት ጋር ይታሰራል። በአንድ መኪና ለሁለት ተጭነው የሚመጡ እስረኞችም ነበሩ። ያ ሽፍን የፖሊስ መኪና፣ ከ10 ጊዜ በላይ ከማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ እስረኞችን ያመልላስ ነበር። በግቢው ውስጥ የነበረው የመኪናው ፍጥነት ጦርነት አዘል የሆሊውድ ፊልምን ያስታውሰኛል። በወቅቱ የእስረኛ ቤተሰቦች ድምጻቸውን አንሳሰው ያለቅሱም ነበር።

ድርጊቱ ተመሳሳይ የነበረ ሲሆን ከወ/ሮ እማዋይሽ አለሙ በተጨማሪ አንዲት ሴትም ነበረች። ስሟን የዘነጋኋት። ተጠርጣሪ ባለቤቷ ስላልተገኘ እሷን አሰሯት። በጊዜ ሂደትም ተፈታለች። ይህቺን እስረኛ ወ/ሮ እማዋይሽ ከተፈታች በኋላ በመኖሪያ ቤቷ ልንጠይቃት ሄደን እማዋይሽን ልትይጠቃት መጥታ ተገናኝንናል። ያኔ የደረሰባቸው የግፍ እስር ስታስረዳን ነበር። ወ/ሮ እማዋይሽ ግን ስለማዕከላዊ የግፍ እስራቸው ማንሳት አትሻም።

…..አቶ ጽጌ ላይ ቀርቦ የነበረው ክስም እንዲህ የሚል ይዘት ነበረው። “ከእንግሊዝ ሀገር ሲመለሱ የግንቦት ሰባትን ዓላማ የሚያስረዱ በራሪ ወረቀቶችና ጽሁፎች በሻንጣቸው ውስጥ ይዘው መጥተዋል። …የመንግስት ባለስልጣናትን ለመግደል፣ ለሽብር ድርጊት ለመፈጸም … ብር ከውጭ አምጥተው ለሰዎች ሰጥተዋል ….”

አቶ ጽጌ ወልደማርያም፣ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ቢገልጹም፤ ከእድሜ ልክ ፍርድ አላመለጡም ነበር። ከፍርዱ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት በቃሊቲ ከታሰሩ በኋላም የመፈታታቸውን ዜና ሰምተናል።

እኔም የዚህን የፍርድ ቤት ሂደት እስመከጨረሻው ድረስ በዝርዝር በያኔ አውራንባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ እዘግብ ነበር። አቃቤ ህግ ግን “የምስክሮችን ስም ጠቅሰህ በዝርዝር ዘግበሃል” የሚል ክስ ለችሎቱ አቅርቦብኝ ነበር። ፖሊስም ቢሯችን ድረስ በመምጣት ዋና አዘጋጁ (ፍጹም ማሞ) እና እኔን ይዘው ማዕላከዊ ወንጀል ምርመራ ሄዱ። ሌሎች ሁለት ጋዜጦችም ነበሩ።

“ነገ ፍርድ ቤት ትቀርላባችሁ። ስለዚህ እዚህ ታስራችሁ ትቀርባላችሁ ወይም የአምስት ሺህ ብር ዋስ ራሳችሁ ፈርማችሁ ጠዋት እዚህ ትመላጣችሁ?” የሚል አማራጭ አቀረልበን – መርማሪው። እንርቀባለን ብለን በጠዋት ማዕላከዊ ደርሰን ወደፍርድ ቤት ወሰዱን። ፍትህ አዳራሽ ሙሉ በሙሉ ጢም ብሏል። ሁሉም ተከሳሾች አሉ። የእኛ ጉዳይ ቀደመና የአቃቤ ህግ ክስና የዳኞች ጥያቄ ቀጠለ። እኛም በየተራ አስረዳን። የመሃል ዳኛው በእኔ ዝርዝር ዘገባ ደስተኛ አለመሆናቸው በቁጣ ንግግራቸው ያስታውቅ ነበር። “የፍርድ ሂደቱን ለማዛባት ነው ሆነ ብለህ የምትሰራው!” …የሚል ሃይለ ቃል ጭምር ሰነዘሩ። ቃላችንን ከተቀበሉ በኋላም ለውሳኔ ቀጠሩን። በመጨረሻም “በመጨረሻም ማስንጠቀቂያ ታልፋችኋል” የሚል መልስ ተሰጠን።

…ከረዥም ዓመት በኋላ ዛሬ፣ አቶ ጽጌ የልጃቸውን ፍቺ በመጠባበቅ ላይ ቃሊቲ በራፍ ላይ ሆነው፤ በስንታየሁ ቸኮል በኩል የተለቀቀችውን ይህቺን ፎቶግራፍ ስመለከት ማዘኔ አልቀረም፤ በዓመታት እንግልቸው። የአቶ ጽጌ ፎቶግራፍ ወደዘጠኝ ዓመት ትዝታ ቢመልሰኝ ይህቺን ከተብኩ።

ለአቶ ጽጌ ጤናና እድሜ እመኛለሁ። ልጃቸውንም ከፍቺ በኋላ አቅፈው ለመሳም ያብቃቸው! እፎይ ይበሉም!

ኢትዮጵያ!

LEAVE A REPLY