ዶ/ር አብይ ለምን አዜብን ሾመ? /ጌታቸው ሺፈራው/

ዶ/ር አብይ ለምን አዜብን ሾመ? /ጌታቸው ሺፈራው/

ትህነግ/ህወሓት ባለፈው 27 አመት ያሳየን “ብቃት” ችግር ያለባቸውን፣ ሕዝብም ሌሎች የፖለቲካ ኃይሎች “አክ እንትፍ” ያሏቸውን እሱ ጋር በማስጠጋት ደካሞችን መጠቀሙ ነው። ለዚህ በምሳሌነት መቀሌ ሄደው “ነፍጠኛ እና ትምክተኛ ብለን የመሳደብ መብታችን ተነፈግን” እያሉ የሚያለቅሱትን የብአዴን ጡረተኞች መጥቀስ ይቻላል። እነ ህላዊ ዮሴፍ በትህነግ የተመረጡት ከሕዝብ የተጣሉ በመሆናቸው ነው። ይሰጡት የነበረው አገልግሎት ሕዝብን መዝለፍ፣ ለህዝብ የቆመውን ማስጠቃት ነበር።

~ዶ/ር አብይ አህመድ አዜብ መስፍንን የሜቴክ ቦርድ አባል አድርጎ ሾመ ሲባል ብዙ ደጋፊዎቹም ቅር ሳይሰኙበት አልቀሩም። ተቃዋሚዎቹም “ብለናችሁ ነበር” ብለዋል። አዜብን በእውቀቷ ሾማት የሚል አይገኝም። አዜም ከሰራተኞች ጋር ተግባብታ ትሰራለች ማለት አይቻልም። መለስ ዜናዊ በመተ ማግስት አንድ የውጭ ጋዜጠኛ የመለስ ዜናዊ አድናቂ መሆኑን ፅፎ ነበር። መለስን የሚያደንቀው ለኢትዮጵያ በሰራው መልካም አይደለም። በጎ አሰራም ብሎ ይመሰክራል። መለስ ዜናዊ ለጉብኝት ወደ ውጭ ሀገር በሄደበት ወቅት ጋዜጠኛው ለቃለመጠይቅ ቀጠሮ አስይዞ እየጠበቀ ነው። አንደኛው ክፍል ውስጥ። በወቅቱ ባልና ሚስቱ ይጨቃጨቃሉ። በአብዛኛው የሚሰማው የአዜብ ድምፅ ነበር። በመጨረሻ በሩን መለስ ጆሮ ላይ ጠርቅማበት ወጣች ይላል ጋዜጠኛው። እናም ጋዜጠኛው መለስ ዜናዊ ይችን ሴት ችሎ በመኖሩ ብቻ ጀግና ነው ይላል። በአጭሩ አዜብ ፀባይ የራቃት ሴት ነች። ለባሏ እንኳ ክፉ ናት።

~አዜብ የባሏን ስልጣን ተጠቅማ ብዙውን ባለስልጣን ከፍ ዝቅ አድርጋለች። በባሏ ስልጣን ተመክታ ብዙውን አዝዛለች። ሀብት አካብታለች። ባለስልጣናቱን ለባሏ ከማሳጣት ባሻገር ስልጣንና ገንዘብ የመስጠትና የመቀማቱ ስራ ላይ እንደነበረችበት ብዙዎቹ ይናገራሉ። አዛዥ ናዛዥ ነበረች። በመለስ ሞት ማግስት ግን ያ ሁሉ የአዜብ አቅም ተናደ።

~ከመለስ ሞት በኋላ ስለ አዜብ ብዙ ነገር ተብሏል። በሙስና ለማባረር ለማሰር አስፈራርተዋታል። በየ ግምገማው አብጠልጥለዋታል። በብሔራዊ ቴሌቪዥኑ ከማዕከላዊ ኮሚቴ መባረሯን አስወርተውላታል።

~ከቤተ መንግስት እንኳን አልወጣም የሚያስብል የገገረ አመል ያላት አዜብ ከመለስ በኋላ የገፋችው፣ የጎነተለችው ሁሉ ዝቅ አድርጎ ሲያያት፣ ባገኘው አጋጣሚ ሲበቀላት፣ የለመደችውን ለማዘዝ ስትጥር ሲያፌዝባትና ሲያዋርዳት እንደተሸነፈች ሴት በር ዘግታ ከማልቀስ ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራትም። “መለስ ማረኝ” ብትለው፣ መለስ አይመጣም።

~ከእነ ገብረዋህድ ጋር በሌብነት ቂሊንጦ ታስረው የነበሩት የትህነግ ባለሀብቶች አዜብ ከማዕካላዊ ኮሚቴ ተባረረች ተብሎ በኢቲቪ በመነገሩ ሲጨፍሩ አድረዋል። አዜብ ያስቀየመችው ብዙ ነው። በእሷ ውድቀት የሚደሰተው በርካታ ነው። በአገኘው አጋጣሚ የሚያዋርዳት ሞልቷል። ከትህነግ/ህወሓት ሰፈር! በቀኗ ያደረገችው፣ ቀን ሲጥላት አግኝቷታል!

~ትህነግ በወልቃይት ጉዳይ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ አዜብ መስፍን “እኔ የወልቃይት ተወላጅ ነኝ። ወልቃይት የትግራይ ነው።” የሚል ሰፊ መግለጫ እንድትሰጥ ጠይቋት እንደነበር ተገልፆአል። በባሏ ስልጣን ተመክታ ስታዛቸው፣ ስታሾከሹክባቸው፣ ስትነጥቃቸው ከነበሩት የትህነግ ካድሬዎች ጋር በገባችው የከረረ ጠብ ምክንያት መግለጫውን አልሰጥም ብላለች። አዜብ መግለጫውን አልሰጥም ያለችው ለትህነግ አስተሳሰብ ወጥታ፣ ለእውነት ቆማ አይደለም። ነገም ከተመቻት መግለጫ ትሰጣለች። ነገር ግን ስታዝዛቸው የነበሩት ካድሬዎች ጋር በተፈጠረ አምባጓሮ መግለጫ ለመስጠት አይኗን በማታሽበት ጉዳይ ላይም አሻፈረኝ እንዳለች ተሰምቷል።

ታዲያ ይችን ሴት ዶ/ር አብይ ለምን ፈለጋት?

~አዜብ አቅም የላትም፣ ፀባይ የላትም። ሙሰኝነቷ የታወቀ ነው። በትህነግ ሰዎች ተጥላለች። “መለስ ማረኝ” ስትል ታመጭቀው የነበረው ባሏ ባይደርስላትም፣ ዶ/ር አብይ አህመድ ደርሶላታል። ዶ/ር አብይም የደረሰላት ደካማነቷን ፈልጎ ነው። በዚህ ወቅት ስታዛቸው፣ስልጣን ስትሰጥ፣ ስትነጥቃቸው በነበሩት የትህነግ ካድሬዎች የተናቀችውን አዜም መስፍንን ያክል ከትህነግ ሰፈር ታማኝ ሰው አያገኝም።

~ለአዜብ ዶ/ር አብይ ደም መላሽ ነው። ከስልጣን ያባረሯትን፣ በባሏ ተመክታ ስታሳጣቸው ስለነበር፣ ከመለስ ሞት በኋላ ያስለቀሷትን የትህነግ ጉምቱዎች ከስልጣን ገፍቷቸዋል። የተጣለችውን አዜብን እንደገና “ሹመት” ሰጥቷታል። ባትሰራበትም ባጇንም ለእነ ስብሃት ነጋ በማሳየት ትልቅ ደስታ ታገኛለች።

~ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን እንደመጣ “አብይ አያዘንም” ብለው ስልጣን የለቀቁት የሜቴክና የኢንሳ ኃላፊዎች ናቸው። ኢንሳ ላይ ተመስገን የሚባል አብይ እንደልቡ የሚያዘውን የብአዴን ካድሬ ተክቷል። ክንፈ ዳኘው አዜብ ቀን ሲጥላት ሲገላምጧት ከነበሩት መካከል መሆኑ ነው። ክንፈ ዳኘው ቢለቅም መስርያ ቤቱ በትህነግ ካድሬዎች የተሞላ ነው። እነዚህ ካድሬዎች የብአዴኑ አዲስ ሹመኛ አምባቸው መኮንን ደፍሮ አይናገራቸውም። ድክመታቸውን የምታውቀው፣ እንደገና ቀን ወጣልኝ የምትለው አዜብ ግን ልክ ልካቸውን ለመንገር፣ እንደፈለገችው ለማሳጣት፣ አስፈላጊ ከሆነም ከስልጣን እንዲባረሩ ለማድረግ ወደኋላ አትልም። ይህን ደግሞ አብይ ቃል ገብቶላት እንደሚሆን ግልፅ ነው። በመሆኑም አዜብ ወደ ሜቴክ የተላከችው በአምባቸው ጀርባ ሆነ እነ ክንፈ በሰገሰጓቸው ካድሬዎች ቀስት እንድትወረውር ነው። ሜቴክ ደግሞ ሰፊ ነው፣ ሀብታም ነው። ብዙ ቦታ ያደርሳል።

~ዶ/ር አብይ ለተጣለችው አዜብ ሲደርስላት፣ በሜቴክ የምታደርግለት ውለታ ብቻ በቂ አይደለም። አዜብ የትህነግ ሰዎችን ድክመት ታውቃለች። ማህበራዊ ህይወታቸውን ታውቃለች። ባሏ ስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የድብቁን ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ የትህነግን ካድሬዎች ውስጠ ሚስጥር ታውቃለች። የሜቴክ የቦርድ አባል አድርጎ ሲሾማት ብዙ ቅሬታ የደረሰበት አብይ፣ ሌላ ስልጣን ሊሰጣት አይደፍርም። ከዚሁ ተሸጉጣ ግን የትህነግን ሰዎች ውስጠ ሚስጥር ለእሱ በማቀበል፣ በአጭሩ በማሾክሾክ ቀላል የማይባል አበርክቶ ታደርጋለች። አዜብ መስፍን ዶ/ር አብይ ካደረገላት ውለታ፣ ያዋረዷትን የትህነግ ሰዎች በማሳጣት፣ አጋጣሚውን ሁሉ ተጠቅማ ለአብይ የተቻላትን በማድረግ ወደ ኋላ አትልም። አብይ አሁን ላደረገላት “ከአሁን በኋላ ብሞትም አይቆጨኝ” እንደምትል ግልፅ ነው። አብይም በቦርድ አባልነት ብቻ ደንበኛ መረጃ አቀባይ አግኝቷል። ዶ/ር አብይ የአዜብ ባል የሚታወቅበትን በደካሞች መጠቀም ስልት በአዜብ ጀምሮታል። ነገሩ በሰፈሩት ቁና ነው! የመለስ በደካማ የመጫወት ግፍ በሚስቱ ደርሷል! ጠንካራ በሬ፣ ከሞተ በሬ ቆዳ በተገኘ ጠፍር ተጠልፎ ይወድቃል። ዶ/ር አብይም የትህነግ ሰዎች ባሏ ሲሞት ጠብቀው በገደሏት አዜብ የምትባልት ጠፍር የበሬዎቹን የትህነግ/ህወሓት ፖለቲከኞች ለመጥለፍ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል። አዜብ በሜቴክ የቦርድ አባልነት የተሾመችው ትህነግን በመጥለፊያ ጠፍርነት ነው!

LEAVE A REPLY