የአንዱአለም አራጌ መልዕክት

የአንዱአለም አራጌ መልዕክት

ውድ ወገኖቼ ፦

በቅድሚያ የከበረ ሰላምታዬ ከውድ ሀገራችን ኢትዮጵያ

(አዲስ አበባ) በያላችሁበት ይድረሳችሁ !

ፈጣሪያችን ቸሩ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁንና ባለፈው ማክሰኞ June.5 .2018 በሰላም ሃገሬ ተመልሼ ከናፈኳቸውና ከናፈቁኝ ቤተሰቦቼ ጋር በደስታ ተቀላቅያለሁ።

ውድ ወገኖቼ፦

 ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ታላላቅ መሪዎች አንዱ ፣ በእጅጉ የማደንቃቸውና የምወዳቸው ታላቁ የኢትዮጵያ አንድነት ምሳሌ የሆኑት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ናቸው ።የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የኝህ ቆራጥ አስተዋይና ፍፁም አገር ወዳድ ታላቅ መሪ 150 ኛ ሙት ዓመት ዝክረ በዓል ላይ በክብር እንግዳነት ፍራንክፈርት (ጀርመን ) ላይ እንድገኝና ውጭ ከሚኖረው ወገኔ ጋር እንድገናኝ ፣ እንድወያይ አዘጋጁ “የኢትዮጵያን የውይይትና የትብብር መድረክ” ጋብዞኝ ጉዞዬን ወደ ጀርመን ሳቀና የተሰማኝን ደስታ ልደብቀው የማይገባ ሀቅ ነው ።

 ለዚህም እንደገና ለመድረኩ ዓባሎች ፣ ዓመራር አካሎችና በዚህ ዙሪያ ለተባበሩ በሙሉ በተለይም በቆየሁባቸው ቀኖች ሁሉ ከሩቅም ከቅርብም በሀሳብም በምክርም ካጠገቤ ሳይለዩ እንደወንድም ለተንከባከቡኝ ፣ ፕሮግራሞቼን በስነስርዓት ላጠናቀሩልኝና ስማቸውን ያንዱን አንስቶ የሌላውን ላለመተው ቅር እያለኝ ባልጠቅስም ባጠቃላይ ለሁሉም ያለኝን ክብርና ከፍተኛ ምስጋና ከልብ አቀርባለሁ ።

 በ 11 02 2018 ፍራንክፈርት ዓየር ጣቢያ ጀምሮ በፍራንክፈርት ፣ በበርሊን ፣ በኮለን ፣ በአምስተርዳምና ብራስልስ በተካፈልኩባቸው ህዝባዊ ስብሰባ ሁሉ ህፃናት ፣ አዋቂ ፣ ሴት ፣ ወንድ ሁሉ ሳይቀር አበባ በመያዝ አካባቢውን ፈረንጅ እስኪገረም ድረስ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ባህር አድርገው ለኔ የሚበዛብኝን ክብርና ሞገስ የተሞላበት አቀባበል ያደረጉልኝን:

እንዲሁም እንደ ኑረንበርግ ፣ ሙኒክ ፣ ዙሪክ ፣ ኮለን/ ቦን ከመሳሰሉ የተለያዩ ከተሞች ራቀን ሳይሉ እኔን ለማግኘት በግል አስተባብረው ላሳዩኝ ፍቅርና ላደረጉልኝ ሁሉ በማመስገን ወረታቸውን እግዚአብሔር ይክፈላቸው እላለሁ ።

 በዚህም ቆይታዬ በተጠቀሱት ከተሞችና በግል ፓሪስ በመጓዝ አግኝቼ በዕድሜም ፣ በዕውቀትም ፣ በስራ ልምምድም ከኔ ሊበልጡ ከሚችሉ ብልህ ሰወች ጋር ያደረኩት ውይይት እጅግ ጠቃሚ ፣ ገንቢና ትምህርታዊ እንደነበረም ባድናቆት ስገልፅ በኩራት ጭምር ነው ።

በአፀፋውም የተሰጠኝን አስተያየት ስመነዝረው ያ ሁሉ የተከፈለ መከራና ፍዳ ያተረፈው ውጤት ምክንያታዊ መሆኑን አረጋግጫለሁ ።

ውድ ባለቤቴ !

ውድ ልጆቼ !

ውድ ቤተሰብ ፣ ወዳጆቼ !

በኔ ሳቢያ የደረሰባችሁ መጉላላት ፣ የደረሰባችሁ ሰቃይ ፣ የመንፈስ ጭንቀት ያለ ምክንያት መሆኑን በዚህ የአውሮፓ ጉዞዬ ለኔ የተደረገው ክብርና ሞገስ ሁሉ ለናንተ ጭምር መሆኑን በምስክርነት አይቻለሁና በጋራ እንኩራበት ።

ፈጣሪያችንንም እናመስግንበት !

በመጨረሻም ወገኖቼ !

በተለያየ ምክንያት ከሀገራችሁ በስጋ ርቃችሁ በመንፈስ ግን ከወገናችሁ ፣ ካገራችሁ ሳትርቁ በሚደረገው ሁሉ ስትብሰከሰኩ ባስተዋልኩት መሰረት ለሃገራችን ሰላም ፣ ፍቅር ፣ መረጋጋት ፣ መተሳሰብ ዲሞክራሲና ፍትህ ወርዶለት ባንድነት አውሮፓ ያደረግነውን ክምችት ውድ አገራችን በቅርብ እንድንደግመው እመኛለሁ ! እፀልያለሁ !

ለዚህም ለህይወቴ በቀደድኩት የፓለቲካ ትግል ፈር ሳላወላዳ በመከተል የናንተን ድጋፍ መሰረት አድርጌ የምችለውን ሁሉ በማድረግ የበለጠ ወገኔንና ሀገሬን ለማገልገል ቃል እገባላችኋለሁ ።

እንደገና ክብርና ምስጋናዬ ለናንተ ነው !

ኢትዮጵያ ለዘላለም ተከብራ ትኑር !

አንዱዓለም አራጌ,,,,,, ከአዲስ አበባ ( ኢትዮጵያ )

 

LEAVE A REPLY