አሁን ያለንበት ሁኔታ “ታስሮ የተፈታ ጥጃ” ሁኔታ ነው። መዝለል እና መቦረቅ – የነፃነታችንን ልክ መፈተን የምንፈልግበት ወቅት ነው። ምክንያቱም ነፃነታችን ከእስር የተፈታው ገና አሁን ነው፣ የዴሞክራሲ ባሕል አልነበረንም፣ በዚያ ላይ ያልተመለሱ እልፍ ጥያቄዎች አሉን። ይሁን እንጂ ሲደክመን እንሰክናለን። መዝለል ስለምንችል ብቻ አንዘልም። መርገጥ ስለምንችል ብቻ አንራገጥም። ያልተመለሱ ጥያቄዎችን በተደራጀ፣ በሕጋዊ እና ሠላማዊ መንገድ ታግለን ማስመለስ እንጀምራለን። ከዚያ በፊት ግን ዝላያችን እና እርግጫችን ለገዢዎቻችን የለውጡን ተስፋ ለመቀልበሻ፣ እኛን መልሶ ለመርገጫ ምክንያት እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል።
አንዲት ኤርትሪያዊት የትዊተር ተጠቃሚ፣ ‘ሰውያችሁ ባለ ግርማ ሞገስ እና ጥሩ ተናጋሪ በመሆኑ እንዳትሸወዱ፣ የእኛም መሪ እንደዛ በመሆኑ የለውጡን ተቋማዊነትን ሳናረጋግጥ ነው ለዚህ የተዳረግነው’ የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያውያን አቻዎቿ አስተላልፋለች። አዎ፣ የዛሬው ታላቁ አምባገነን ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የዛሬ 27 ዓመት ገደማ በኤርትራውያን ዘንድ ታላቅ ሕዝባዊ ይሁንታ ያለው መሪ ነበር።
“ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከራሳቸው መጠበቅ” በሚለው ጽሑፌ ‘ብዙዎቹ ነጻ አውጪዎች ኋላ አምባገነን ይሆናሉ’ ማለቴን እንደ ጅምላ ድምዳሜ የወሰዱብኝ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። እኔ ለማመልከት የፈለግኩት በአንድ ወቅት ‘ነጻ አውጪ’ የነበረ፣ ሌላ ግዜ ‘አምባገነን’ እንደማይሆን አያረጋግጥም ነው። ይህ እንዳይሆን ብቸኛው ዋስትና ‘ቁጥጥርና ሚዛን’ (check and balance) ነው። ትላንት ጓደኞቼ ስለ ኢዲ አሚን ዳዳ አንድ ጽሑፍ እያስነበቡኝ ነበር። ከዓለማችን የምንግዜም አምባገነኖች አንዱ የሆነው ኢዲ አሚን በሥልጣን አፍላው ዘመን በምዕራባውያን ሚዲያዎች ሳይቀር የተንቆለጳጰሰ ሰው ነበር። ሰውን አምባገነን የሚያደርገው ተቋማዊ ነጻነት አለመኖሩ እና የግለሰቦች ሥልጣን አለመገደቡ ነው።
ኢትዮጵያ ለውጥ ለምን አይዋጣላትም?
ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት አሁን ያለንበትን የለውጥ ተስፋ ጥላሸት ለመቀባት ወይም ተቀልብሷል ለማለት አይደለም። ለውጡ ከግለሰቦች በጎ ፈቃድ ወደ ተቋማዊ እውነታነት እንዲሸጋገር ካለኝ ጥልቅ ጉጉት ነው። ሁሉም ሰው የለውጡን አካሔድ በጥንቃቄ እንዲመለከተው ስለምፈልግ ነው።
ኢትዮጵያ እንዲህ የለውጥ ተስፋ ውስጥ የገባችው አሁን ብቻ አይደለም። የንጉሣዊው ስርዓት መደርመስ እና የመሬት ላራሹ መታወጅም ግዙፍ ሕዝባዊ ይሁንታ እና ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። የምርጫ 1997 ዋዜማ አገራችን የመጀመሪያውን ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ልታካሒድ ነው በሚል ትልቅ ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። ሌላው ቀርቶ የደርግ መውደቅ እና በሌላ ታጣቂ መተካት ትልቅ የለውጥ ተስፋ ፈንጥቆ ነበር።
ከ‘ያ ትውልድ’ ሰዎች አንዱ ገጣሚ ኃይሉ ገ/ዮሐንስ (ገሞራው) ‘ኢትዮጵያ ለውጥ የማይዋጣላት አበውን አጠያይቄ በነገሩኝ መሠረት “ተረግማ ነው”’ በሚል በ1993 ‘ኢትዮጵ’ መጽሔት ላይ ተከራክሯል። ዐፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ሲያጠፉ፣ ዐፄ ዮሐንስ በደርቡሾች አንገታቸው ሲቀላ፣ ልጅ እያሱ ሲገደሉ፣ አቡነ ጴጥሮስ በጣሊያን ሲረሸኑ፣ ደጃች በላይ ዘለቀ እና ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ በአደባባይ ሲሰቀሉ፣ ዐፄ ኃይለሥላሴ ሲገደሉ በአገራቸው አዝነው እና ተማርረው ነው በሚል ገሞራው ተከራክሯል።
እኔ ግን በእርግማን አላምንም። እንመን ቢባል እንኳ በጥቂቶች ጥፋት ብዙዎች የሚቀጡበት ምክንያትም አይኖርም። ለውጥ የማይዋጣልን ለቅድመ ለውጡ የምንከፍለውን መስዋዕትነት ሩቡን እንኳን ለውጡን ለማስጠበቅ ስለማንከፍል ነው። ከዚያም በላይ የከፋው ደግሞ ተረኛ ጨቋኝ እንመርጣለን እንጂ ነፃነትን ብቻ ዒላማ አድርገን ስለማንመርጥ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ደግመው ደጋግመው እንደተናገሩት ‘ኢትዮጵያውያን ተጨቋኝነትን እንጂ ጭቆናን አንቃወምም’።
ሁለቱ ፅንፎች
ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያለፉትን ሦስት ስርዓቶች ተቃውመዋል በሚል ነው ሥማቸው የሚነሳው። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን መምጣት በሙሉ ይሁንታ ከተቀበሉ ሰዎች ሁሉ የእርሳቸውን አስገራሚ የሚያደርገው የተቃዋሚነታቸው ታሪክ ነው። እንደ እርሳቸው ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን ወደ ሥልጣን ያመጣቸው ‘ኢትዮጵያ የተአምር አገር መሆኗ ነው፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን እንደማይታዋት ማሳያ ነው’።
በሌላ በኩል፣ ከኢንሳ ኃላፊነታቸው የተነሱት ጄኔራል ተክለብርሃን በትግራይ ቲቪ ቀርበው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ትሕነግን (TPLF) ለማጥፋት ያለሙ ሰው እንደሆኑ አድርገው ገልጠዋቸዋል። ‘አካሔዳቸው ፕሬዝደንታዊ ዓይነት ነው። ሕግ ይጥሳሉ፣ እስረኛ ይፈታሉ፣ አሸባሪ ይጠራሉ፣ ባድመን ሕግ ተላልፈው ያለ ቅድመ ሁኔታ ሰጥተዋል፣… እየተመራን ያለነው በጁንታ ነው’ ብለዋል።
ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ አንድነት ከምንም በላይ የሚያሳስባቸው ሰው ናቸው። የድጋፋቸው እና የደስታቸው ምንጭም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አመጣጥ ኢትዮጵያ ካሁን አሁን ወደ ቀውስ ገባች እየተባለ ባለበት በኢትዮጵያ ሥም እየማሉ የሚገዘቱ መሪ ሁነው፣ አመፁን ሁሉ ፀጥ ማስባል በመቻላቸው ነው። በተቃራኒው የትሕነግ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና ተቀባይነት ያስገኘላቸውን ለውጥ የሚቃወሙት ቀድሞ የነበራቸውን የበላይነት ስለሚቀማቸው ነው። የበላይ ፈላጭ ቆራጭ ለነበረ ሰው ዕኩልነት አዋጭ አይደለም። የለውጡ ድባብ ግን ከነዚህ ዕኩልነት አያዋጣንም ከሚሉት ውጪ ያሉትን ከሞላ ጎደል አስማሚ ነው። ለአገር ተቆርቋሪ የሆኑትን ከመፍታትም በላይ፣ ተሰደው የከረሙትንም ወደ አገር ቤት የሚመልስ የለውጥ ድባብ ነው ያለው።
ቀጣዩ ግጭት የሚነሳው በሁለቱ ፅንፎች መካከል ነው ብዬ እሰጋለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት የለውጥ መንፈስ ደጋፊዎች እና የለውጥ መንፈሱን በሚቃወሙት መካከል። የለውጡ መንፈስ ደጋፊዎች ብዙኃን ቢሆኑም በኢኮኖሚ እና በመዋቅር አልተደራጁም። የለውጡ መንፈስ ተቃዋሚዎች የድርጅት መዋቅሩ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊ አቅሙም አላቸው። ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገደምዳሜም ቢሆን ‘ለውጡን ጠብቁ’ የሚል መልዕክት የሚያስተላልፉት። በርግጥ ትሕነግም በመግለጫ ሳይቀር ተቃራኒው እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል። ለውጡን ጠብቁ የሚለው ጥሪ እና ዛቻ ብዙ አብዮቶች እንዲቀለበሱ ሰበብ የሚሰጣቸው “ፀረ አብዮቶችን የመመንጠር ዘመቻ” ጋር ስለሚመሳሰልብኝ ያስደነግጠኛል። ይሁን እንጂ የሚከተለውን ጥያቄ አቀርባለው።
የትኛውን ለውጥ እንጠብቅ?
እስረኞችን የመፍታት እርምጃው ለውጥ ነው። ይሁን እንጂ ድርጊቱ የተፈፀመው በሕጋዊ አግባብ ሳይሆን በፖለቲካ አመራሮቹ መልካም ፈቃድ ነው። (እርግጥ አሁን ዐዋጁም እየተሻሻለ ስለሆነ በአስቸኳይ መፍትሔ የተስተካከለው በሕግ እየፀና ነው እና ትክክለኛ አካሔድ ነው። ይህንን ግን በሁሉም ረገድ እንዲቀጥል ማድረግ ነው ‘ለውጡን መጠበቅ’ ማለት ሊሆን የሚችለው።) በሕግ ያልተፈቀዱ ባንዲራዎች ያለምንም ስጋት አደባባይ ላይ እንዲውለበለቡ ተፈቅዷል። በእርግጥ ሕጎቹ ፍትሓዊ ባለመሆናቸው ድርጊቱ/ለውጡ መልካም ነው። ነገር ግን በፖለቲካ አመራሮቹ ይሁንታ ብቻ የተደረገ ስለሆነ ሕጋዊ ዋስትና የለውም። የባንዲራን ጉዳይ እንደምሳሌ አነሳሁት እንጂ በሁሉም እርምጃ አካሔዱን ማስተዋል እና መገምገም አለብን።
የፖለቲካ መሪዎች የመፍቀድ መብት ካላቸው፣ የመከልከልም ይኖራቸዋል። የፖለቲካ መሪዎች ሥልጣን ተለጥጦ በጎ ፈቃዳቸው ለብዙኃኑ ተስማሚ እስከሆነ ድረስ ችግሩ አይስተዋልም። ችግሩ ይህንኑ ሥልጣናቸውን ለብዙኃኑ ተስማሚ ባልሆነ መንገድ የተጠቀሙበት ግዜ ነው የሚመጣው። በርግጥ ቅንነት ከፖለቲካ ምኅዳራችን የተሰወረ ነገር በመሆኑ አሁን መከሰቱ ግሩም ነው። ነገር ግን የብዙኃኑ ተጠቃሚነት በጥቂት ባለሥልጣናት ቅንነት እና በጎ ፈቃድ ላይ ተንጠልጥሎ መቀመጥ የለበትም። ምክንያቱም ደግሞ ባለሥልጣናቱ ዘላለም የማይኖሩ ከመሆኑም ባሻገር ቅንነታቸውም ዘላለም ላይኖር ይችላል።
መፍትሔው የተለያዩ ተቋማት ነጻ እና ገለልተኛ እንዲሆኑ አድርጎ መገንባት ነው። መወገን ካለባቸውም ለሕዝብ እና ሕገ መንግሥቱ መሆን አለበት። ለውጡን ስንደግፍ የምናየው ለውጥ ሕጋዊ ዋስትና እንዲኖረው፣ ተቋማዊ ነጻነት እንዲጠናከር፣ የፍትሓዊ ሕግ የበላይነት እንዲስፋፋ ግፊት በማድረግ መሆን አለበት። አለበለዚያ ይህም ዕድል ያመልጠናልና ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለለትን ለውጥ በዚህ መንገድ እንጠብቅ።