የሱዳን ወታደሮች በመተማ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

የሱዳን ወታደሮች በመተማ ወረዳ ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር መተማ ወረዳ በኢትዮጵያ ገበሬዎች ላይ የሱዳን ወታደሮች በቀሰቀሱት ግጭት በርካታ ገበሬዎች መሞታቸው ተገለጸ።ዛሬ ጠዋት በተቀሰቀሰው ግጭት በሁለቱም ወገን ሰዎች መገደላቸው ተሰምቷል።

የሱዳን ወታደሮች ግጭት የቀሰቀሱት በመተማ ወረዳ ደላሎ ቁጥር 4 እርሻና ኢንቨስትመንት በተባለ አካባቢ መሆኑ ታውቋል። የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የሚጠቀሙበትን የእርሻ መሬት እንዳያርሱ የሱዳን ወታደሮች መከልከላቸው ለግጭቱ ዋና ምክንያት መሆኑ ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ከሰዓት በሗላ ወደ አካባቢው በማምራት ግጭቱን ማስቆማቸውም ተጠቁሟል፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘላለም ልጃለም ለአማራ ቴሌቪዥን እንደገለጹት፤ የእርሻ መሬቱን ለረጅም ዓመታት እየተጠቀሙበት የሚገኙት የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ቢሆኑም የሱዳን ወታደሮች “የእርሻ መሬቱን መጠቀም ያለብን እኛ ነን”በማለት ግጭት መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ዘላለም አክለው እንደገለፁት“ሁኔታውን ለአካባቢው የሱዳን አመራሮች ያስረዱ ቢሆንም የሱዳን አመራሮች የተነገራቸውን ባለመቀበላቸው መግባባት አለመቻሉን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮዽያውያን አርሶ አደሮችና በሱዳን ወታደሮች መካከል በተፈጠረው ግጭት እስካሁን ቁጥራቸው ያልታወቀ አርሶ አደሮች የሞትና የመቁሰል አደጋ እንደደርሰባቸው ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ጉዳት የደረሰባቸው አርሶ አደሮች በመተማ ሆስፒታል እርዳት እየተደረገላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

የሱዳን የፀጥታ ሀይሎች በድንበር አካባቢ በሚኖሩ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ላይ በየጊዜው ጥቃት ሲያደርሱና ሲገሉ መቆየታቸው ይታወቃል።

LEAVE A REPLY