የአብይ የጠቅላይነት መንገድ.. ወዴት?

የአብይ የጠቅላይነት መንገድ.. ወዴት?

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ወደ ስልጣን የመጡ ሰሞን አንድ የውጭ አገር ጋዜጠኛ አምባገነን የምትሆን ይመስልሃል ወይ ብሎ ቢጠይቃቸው፤ እኔ በፍጹም አምባገነን ሆኜ ስማቸው በ “M” ከሚጀምረው ከነመንግስቱና ሞቡቱ ጋር ስሜን ማየት አልፈልግም ብለው ነበር፡፡ ማለትና መሆን ሰማይና ምድር ናቸው፡፡ ስልጣን ላይ ከተደላደሉ በኋላ አፍሪካዊያንን የሚያስንቅ ክፉ አምባገነን ሆኑና ስማቸውን ከነሞሶሎሊ ጋር አስጠግተው ቁጭ አሉ፡፡

ከዚህ ቀደም በፌስቡክ ገጼ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አምባገነን የመሆን ዕድላቸው የሰፋ መሆኑን ገልጬ ነበር፡፡ ይሄን የምፈራውን በዘውግ ላይ የተመሰረተ ፌደሬሽን መላ ይበሉት እንጂ አምባገነንታቸውን ለጥቂት ጊዜ ለመታገስ ዝግጁነቴን አስፍሪያለኹ፡፡ ለዚህ ምክንያቴ ደግሞ በዋናነት እየገነቡት ያለው ታይቶ የማይታወቅ የህዝብ ድጋፍ (Mass support) ነበር፡፡ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ የተለመደ (Conventional) አምባገነንነትን የመውለጃ ቦታ መሆኑን ማንም አይጠፋውም፡፡

እያደር እያሰብኩት ስመጣ ግን አምባገነን የመሆናቸው ጉዳይ ጭራሽ አይቀሬ እየሆነ ይታየኛል፡፡ እንዲያውም አምባገነን ይሆናሉ ብዬ ከራሳቸወ ጋር ሁሉ በሚሊዮን ዶላር ብወራረድ የምበላቸው ይመስለኛል፡፡ ወደው ነው አምባገነን የሚሆኑት?!!

በቅርቡ ባደረጉት አንዱ ንግግራቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ አንዳንድ ጊዜ መንግስትም እኮ ወዶ አይደለም አምባገነን የሚሆነው፤ሲገፋ ፤ሲጠቃ መከላከል ይጀምራል፡፡ ሳያስበው መከላከሉ ወዳ ማጥቃት ይሸጋገርና ምንም የማይወጣለት አምባገነን ይሆናል የሚል ይዘት ያለው ንግግራቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እና ዐቢይስ ምን አማራጭ ይኖራቸው ይሆን አምባገነን ላለመሆን??

እሰኪ እንውረድ ላሳያችሁ…..

  1. ሁሉን አወቁ ዐቢይ?

ሊቀመንበር ማኦ ሴዱንግ አንድ ቀይ መጽሐፍ ነበራቸው፡፡ ይቺ ቀይ መጽሐፍ በወቅቱ መጽሐፍ ቅዱስን ተክታ በሁሉ ኪስ የምትገኝ መድሃኒት ተደርጋ ትወሰድ ነበር፡፡ መጽሓፏ ማኦ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አለ ተብላ በወሬ መሃል በሽቅድድም ካድሬዎች ሃረግ እየሳቡ የሚከራከሩባት ነበረች፡፡ ሁሉን አወቅ መጽሐፍ! እንደዚሁ አምባገነኑ ጋዳፊም የሁሉ ነገር መፍትሄ ከዚህ ይቀዳል የሚልበት አረንጓዴ መጽሐፍ ነበረው፡፡ ሊቢያውያን ህጻናት ይህችን አረንጓዴ መጽሐፍ በሳምንት ሁለት ሰዓት እያነበቡ ካላደጉ ሰው አይሆኑም ተብሎ ነበር! በጊዜው ይህችም መጽሐፍ የአለምን ስንክሳር የምታፍታታ ሁሉን አወቅ ነበረች፡፡

ወደኛው ስመለስ ዐቢይ የወታደራዊ ሳይንስ ስልጠና ይሰጣሉ፡፡ ለኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስለኪነት ምንነት እና ስለ ከያኒ ማንነት ሲያሰለጥኑ ይውላሉ፡፡ ለካቢኒያቸው ስለ አመራር ጥበብ ይተነትናሉ፡፡ ሁሉም ቦታ አሉ፤ሁሉንም ያውቃሉ!! ሁሉን ሲናገሩ በደማቁ ይጨበጨባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዐቢይ ምን አለ የሚባልበት ዘመን ሩቅ አይመስልም፡፡  እሳቸውስ ታዲያ ሊቀመንበር ማኦን ላለመሆን ምን አማራጭ አላቸው? ምንም፡፡ ይልቅ ጥያቄ የሚሆነው የእርሳቸው መጽሐፍ ቀለም ምንድን ነው የሚል ነው፡፡

  1. የኢህአዴግ መዋቅር

ዶ/ር ዐቢይ ኢህአዴግ አይደሉም ካልኩኝ ቆየሁ፡፡ አንዳንድ ወዳጆቼ፤ እራሱ “ ድርጅቴ ኢህአዴግ “እያለ ፤ አንተ ምን ቤት ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነህ ሲሉ ይከራከሩኛል፡፡ ብዙ አልከፋም፡፡ ግና የሰውዬው ብዙ ንግግራቸውና ድርጊታቸው፤ የኢህአዴግ ባህሪ አይታይበትም፡፡ ለምሳሌ የኢህአዴግ አስኳል የሆነው ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ለእርሳቸው ቁብ የሚሰጡት ጉዳይ እንዳልሆነ ፓርላማ ላይ ቀርበው ፤እንዲያውም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ስብሰባን  በግርድፉ በቀጥታ ለህዝብ እናቀርበዋለን ሲሉ ነበር፡፡ ይህ ብቻውን በድሮው ኢህአዴግ፤ እንኳን ከሊቀመንበርነት ከአባልነት ሊያሰርዝ የሚችል ወደር አልባ ጥፋት ነበር፡፡ ዶ/ር ዐቢይ አሁን ያለው የኢህአዴግ ቀጥተኛ ያልሆነ የጠቅላይ ሚንስትር ምርጫም (parliamentarian system) ብዙ እንዳልተመቻቸው ያስታውቃሉ፡፡

በሃዋሳ ከተማ ንግግራቸውን ደግሞ የሰውየውን አቋም ጠቋሚ ሆኖ አግኝቼዋለኹ፡፡ ሰውዬው ከዚህ ይልቅ ቀጥተኛ የሆነው  ምርጫ አንጀት አርስ ሆኖ እንደሚታቸው ከዚያ ንግግር ውስጥ መፈልቀቅ እጅግ ቀላል ነው፡፡ አሁን ባላቸውና ለመጭው ሁለት ዓመታት በደንብ እየመነዘሩ ከሚበሉት የህዝብ ተቀባይነት አንጻር ከማንም ጋር ቢወዳደሩ አሸናፊ እንደሚሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ የኢህአዴግና የአገሪቱ የመንግስት መዋቅር ግን ለዚህ ደናቃራ ነገር ነው፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ ወይም የኢትዮጵያ ምርጫ ስርዓት ዐቢይን የመሰለ “እንኳን እግሬን ደግሞ ለዐቢይ ህይወቴንስ ብሰጠው “ የሚባልላቸውን፤ ክፉውን ከሩቅ እንዲያረግላቸው ብዙ እህቶች እና እናቶች አምላካቸውን የሚማፀኑላቸውን፤ የሚሊዮኖች ድጋፍና ፍቅር ያለቸውን ሰው፤ ወስዶ የመቶ ሺህ ህዝብ ውክልና ወደሚጠይቁበት አጋሮ ይልካቸዋል፡፡ የመቶ ሺውን ህዝብ አዎንታ ካገኙ በኋላ ደግሞ ወደ 36 እርባና ቢስ የስራ አስፈፃሚዎች ዘንድ የዋንጫ ሊጫወቱ ይመጣሉ፡፡ ይህ በእውነቱ ከሆነ ለዶ/ሩ አያዋጣም፡፡ በአስር ሚሊዮን የሚቆጠር አፍቃሪያቸው እሳቸውን ጥበቃ ከደጅ እያደረ፤ወሳኙ ከሳቸው የፓወር ፖይንት ስልጠና የማያልፈው የ36 ሰው ጥርቅም የሆነው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ሲሆን እጅግ ያሳዝናል!! ስርዓቱን ወደ ፕሬዚደንታዊነት ለመቀየርም ጊዜ ያለም አይመስልም፡፡ ስለዚህ ያለው አማራጭ በየአባል ፓርቲው ያሉ አጠራጣሪ ሰዎችን በጥፊ ማጠናገርና ታማኝ ሰውን (Loyal to the King) ማምጣት ነው-ልክ ሰሞኑን ሺፈራው ሽጉጤና ሲራጅ ፈጌሳ ከፓርያቸው መሪነት እንደተነሱት፡፡ እንዲህ ከማድረግ የዘለለ አማራጭ ያላቸው አይመስልም፡፡

  1. የኢትዮጵያ ብሔርተኝነት

ብዙው ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ ነው፡፡ ዘውገኛ ነው አላልኩም፡፡ አገሩን ይወዳል፡፡ ይህች የሚወዳት አገሩ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት በሚስማር ተቸንክራ ነበር፡፡ አገር የጠሉ፤ ጮክ ብለው ኢትዮጵያ ማለትን መጠየፋቸውን በብሔር ብሔረሰብ እኩልነት ሲያሳብቡ ኖረው የሞቱ መሪዎች የነበራት አገር ነች፡፡ ብዙው እዚህ ጎራ ውስጥ የሚመደበው ኢትዮጵያዊ፤ እኔን ጨምሮ፤ይቺ የቆሰለች እናትን የሚያድን ይምጣ እንጂ አምባገነንም ቢሆን ያዋጣናል ባይ ይመስላል፡፡ In short, he shall accomplish three fold of his predecessors’ achievements to outshine them in the eyes of us, the Ethiopianists.  ለዚህ ምሳሌ የሚሆነው በቃላሉ ድጋፍ የማይቸረው ዲያስፖራ ለዶ/ር አብይ ዲሲ ላይ ተሰለፎ ድጋፉን መግለጹ ነው፡፡ ይህ መጠነ ሰፊ ድጋፍ ሰውዬው አምባገነን ከመሆን ውጭ አማራጭ ያሳጣቸዋል፡፡

  1. ኳሷ ሕወሃት

ኦህዴድና ብዐዴን ዘንድሮ ሕወሃትን እንደኳስ ሲቀባበሏት እያየን ነው፡፡ ሕወሃትን ቀድመው ኳስ ያደረጓት እርግጥ ራሳቸው ትላልቆቹ ሕወሃቶች ይመስሉኛል፡፡ ለዘረፋውም፤ ለትምክህቱም፤ ለግፉም፤ለብልግናውም ለከት ያጡ ወንበዴዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ እነዚህ ሰዎች ውስኪያቸው ላይ ጣል ካደረጉት በረዶ ቀድመው እንዴት ቀለጡ ብሎ የሚጠይቀው ብዙ ነው፡፡ የት ጠፉ? እንዲህ ቀላል ነበሩ ማለት ነው? ብዙ ሰው ይጠይቃል፡፡ ምስጋና ይድረሰውና ሁሌም ለማይረካ የስልጣን ጥሙ፤ህወሃትን ቀድሞ አጥፍቷት የጠፋው ሟቹ የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ ነው፡፡ የሰው ድሃ የሆነችው ሕወሃት እንደምንም 5 ዓመታት ተንደፋደፈች፡፡ ጥቂቶቹን እርጅናው ሲያናውዛቸው፤የተቀሩትን ደግሞ ብልግናቸው ገደል የከተታቸው ይመስላሉ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ደብረጺዮን ገብረሚካኤል(ዶ/ር) ስራው ይሰራ እንጂ የፌደራል መንግስቱ ስልጣን ላይ በሙሉ ኦሮሞ ተወላጆች መያዙ ግድ እንደሌላቸው ተናገሩ፡፡ ይህ ያልተለመደ ጭምትነት ከየት ተከሰተ? ዋና ዋና የመንግስት ሀላፊነቱ ይዞ የተረፈውን በብሔር ኮታ ሲያከፋፍል ከኖረ ፓርቲ ይህ አይጠበቅም፡፡ ይባስ ብለው ዶ/ር ደብረጺዮን ከለውጡ ጋር ልጓዝ እያሉ ነው፡፡ ይህስ ሽቁጥቁጥነት ከወዴት መጣ? እውነት ይሄ ትህትና የወያኔ ልጅ ነው?

ነገሩ ወዲህ ይመስለኛል፡፡

መቼም ኢትዮጵያ በታሪኳ እንደዘንድሮ የምእራባውያን እጅ ላይ የወደቀችበት ያለ አይመስለም፡፡ ሀገሪቱ ችግር ውስጥ ነች፡፡ የመንግስት ካዝና ባዶ ሆኗል፡፡ የምእራባዊያን የደህንነት መዋቅር እንደዛሬው ኢትዮጵያ ላይ የሚፏልልበት ጊዜም የነበረም አይመስለም!  በዲያስጶራ ያሉ አራማጆች የዶ/ር ደብረ ጽዮንን ኮምፒዩተር በመርበር ምን አይነት  “ ጌም “ እንደሚጫወት ሳይቀር ደርሰውበታል፡፡ ኢትዮጵውያን ይህን ማድረግ ከቻሉ፤የምእራባዊያን ሰላዮች ደግሞ ደ/ሩን ገመና ዝርዝር ማወቅ አይሳናቸውም፡፡

ምእራባዊያኑ ደግሞ ለበጎ ይሁን ለመጥፎ ዐቢይን እንደወደዱት በተለያየ ምልክት አሳይተዋል፡፡ እንዲያውም ዐቢይ የማይመረጥ ከሆነ ዘግተን እንወጣለን ያለ ሁሉ የምእራብ አገር ኢምባሲ ነበር ወሬ ሲናፈስ ነበር፡፡ በብዙ ምክንያቶች ደግሞ ምእራባዊያን አሁን ሕወሃቶችን የሚጠሉ ይመስላል፡፡ እንዲያ ከሆነ ምእራባዊያኑ ደብረጺዮንን ትደመር እንደሁ ተደመር ካለዚያ ገመናህን ለአደባባይ እናሰጣዋለን የማይሉበት ምክንያትስ ምንድነው?? እናስ ደብረጺዮን ከመደመር ውጪ ምን አማራጭ አለው?

ሌላው ያለፉት 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደገበጣ ጠጠር ወዲያ ወዲህ ሲለው የነበረው አቦይ ስብሃት የተባለ ሽማግሌ (አያቶላው ይሉታል ብዙዎቹ) አሁን የለም፡፡ ዐቢይ በክብር ብሎ እየሳቀ በጡረታ ወደመኝታው ወስዶታል፡፡ አቦይ ስበሃት የዋዛ አልነበረም፡፡ አንድ ጊዜ የሰማሁት ወሬ ሁልጊዜ ይደንቀኛል፡፡ ዶ/ር መረራ ከእስር ቤት ሊወጡ ሲዘገጃጁ የቀድሞው የደኅንነት ምክትል ኀላፊ አቶ ገብረሥላሴ እስኪ “አንዴ ወዲህ ቅረብ” አለው አሉ፡፡ “ልትወጣ ነው?” “አዎ፡፡” “እንዲያስ ከሆነ እስኪ ለሁሉም ነገር፤ለክፉም ለደጉም፤ አቦይ ስብሃትን አውራው፤የሁሉም በር ቁልፍ ያለው እሱ ዘንድ ነው”

ጊዜ ድንቅ ነው፡፡ መቆየትም ደግ! ያን ያክል ዋናውን ቁልፍ ይዟል የሚባሉት አዛውንት ዛሬ እምጥ ይግቡ ስምጥ ጠፍቶ፤ድምጻቸው ሁሉ መናፈቅ ተጀምሯል፡፡ እውነት በህይወት ባይኖሩ ነው እንጂ የኤርትራ ልኡካን፤ ይሄ ነው የሚባል የህወሃት ሰው ሳይኖር፤ በቤተመንግስት ሲደንሱ አመሹን ሲሰሙ ማላታይን ጠጥተው ሞቱ የሚል ተጨማሪ ሰበር ዜና አይሆነንም ነበር??? ባይኖሩ ነው እንጂ!! ባይኖሩ… ፊታቸውን እየሞዠቁ ተንኮል ማውጣት ቢያቅታቸው ነው እንጂ!! ታዲያ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያለውን ህወሃትን አምባገነን ካልሆንክበት፤ ማን ላይ ልትሆን ትችላለህ? እርሳቸውም አርፈው ስለማይቀመጡ ለዶ/ሩ ምንም አማራጭ የላቸውም!!

  1. የጃዋር ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ

አንባቢ ትዝ ይለው እንደሆን ጃዋርና ባልጀሮቹ መጀመሪያ አካባቢ ዶ/ር አቢይን እንደ ጀርባ ቅማል ጥምድ አድርገው ይዘዋቸው ነበር፡፡ ጃዋር ከዶ/ሩ ይልቅ አቶ ለማን እጅጉን ይደግፍ ነበር፡፡ የነገሩን ስር ደግሞ በዚያን ወቅት አቶ ለማ ከዶ/ር ዐቢይም የተሻሉ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ሆኖ የሚያቅበዘብዛቸው ሰው! አቢይ በወቅቱ መድረክ ያላገኘ የጀርባ አጃቢ ነበር፡፡ ታዲያ እንዴት ኦቦ ጃዋር በኢትዮጵያዊነት ሱስ የሰከሩትን አቶ ለማን በዚያ መልኩ ሊያደነቅና ሊቀበል ቻለ የሚል ጥያቄን የማያነሳ ፖለቲከኛ ቢኖር እሱ ፤ ከዶር ዐቢይ ጋር “ ፍቅር ይዞኛል… ምን ይሻለኛል..”  እያለች ከምትዘፍን በወጣትነት እና በጎልማሳነት መሀል ያለች እመቤትን ይመስላል፡፡  ለምን “ከለማ ውጪ ወደ ውጪ” አለ ጃዋር? ለምን አቶ ለማ የተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዳልሆኑና ባለው ህግ መሰረት ጠቅላይ ሚንስትር እንደማይሆኑ እየተረዳ ህጉን ትንሽ ዘምበል አድርጉት(Don’t break it, Just bend it) ብሎ ኢህአዴግን ሊመክር መጣ? ስራው ያውጣው ብሎ ማለፍ ይቻል ይሆናል፡፡ ጥያቄው ግን አለ፡፡ ይልቅ አሁን እየተቅለሰለሰም ቢሆን ዶ/ር ዐቢይን እንዴት ሊቀበል ቻለ? ምእራባዊያን አንተ ሥርዓት ያዝ ብለውት ይሆን?? ጥያቄ ነው!! ዶር አብይ ደግሞ እንደደምበኛ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታታይነታቸው የጃዋር ለውጥን በደንብ ያዩታል ብዬ እገምታለሁ፡፡ መቼም ሊወዱት አይችሉም፡፡ይልቁንም ጃዋርን የአቶ ለማ የቤት ሰራ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ምእራባዊያን ከጎናቸው ካሉ ደግሞ ጃዋርን ፊት ከመንሳትም አልፈው ሊያጠናግሩት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ እንዲያ ከሆነ ግን ለዶ/ር አብይ ከአምባገነንነት ውጭ ምን ያዋጣል?  ምንም፡፡

  1. የዘውገኞች መንገድ

መጪው ጊዜ ለዘውገኞች ብሩህ አይመስለኝም፡፡ በክፋት የተተከለው የጎሳ ፖለቲካ ዛሬ ሀገሪቱን አዳክሞ ከመንገድ አቁሟታል፡፡ ለአቅመ ብሄር ደርሰዋል፤ራሳቸውን ማሰተዳደር ይችላሉ ያላቸው ጎሰኞች፤ዛሬም ከሃያ ሰባት ዓመት በኋላ፤እንኳን እራሳቸውን ሊያስተዳድሩ ይቅርና ሰውን እንደሚዳቆ ቀስት ወርውረው የሚገድሉ ማፈሪያዎች ናቸው፡፡ የኔ ጎሳ አደለም ያሉትን ምስኪን በቁሙ እሳት የሚለቁበት አረመኔዎች ናቸው፡፡ መጤ ነው ያሉትን ታዳጊ በድንጋይ ወግረው የሚገሉ፤አራዊቶች ናቸው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ ለማንም ቀን የሚያወጣ አይደለም፤ጎሳዬን እወክላለሁ ከሚለው ልሂቅ ውጪ!!

አሜሪካ ኢትዮጵያ እንድትከፋፈልና እንድትጠፋ የምትፈልግ አይመስልም፡፡ ከዚያ ይልቅ አገልጋይ ሆና እንድትቀጥል እንጂ፡፡ በመሆኑም በመጪው ጊዜ ለጎሳ ፖለቲከኞች የምትሰጠው ቦታ እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም፡፡ የሚቀጥለው ምርጫ ላይ ደግሞ ለዐቢይ ትልቅ ፈተና የሚሆነው፤ ኦሮሙማን(Oromuma) የት አደረስከው የሚል ጽንፍ ፖለቲካ አቀንቃኞች የሚያድቦለቡሉት ጥያቄ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ እነዚህን መመለስ ካልቻላችሁ  አይናችሁ ላፈር የሚል ነገርም ሊሰማ ይችላል፡፡ ዐቢይ ይህን የሚታገስበት ትከሻውም የሚሳሳ ይመስለኛል፡፡ ከፊቱ ዞር የሚያደርጋቸው ሰዎች ብዙ ናቸው፡፡ እናሳ በዚህ ሂደት ዶር አብይ አምባገነን ቢሆኑ ይገርም ይሆን?  እረ በፍጹም!

ኢትዮጵያን አንድነቷን አስጠብቀው ካቆዩለት በሕወሃት መራሹ ስርዐት ለኖረ ኢትዮጵያዊ በዶ/ር ዐቢይ የሽግግር ዘመን አምባገነን ዘመን መኖር እንደማይከብደውና እንደማይጎረብጠው ጸሐፊው ይገምታል፡፡

LEAVE A REPLY