በደምቢ ዶሎ ነፍሰ_ጡር እናትን የገደሉ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር...

በደምቢ ዶሎ ነፍሰ_ጡር እናትን የገደሉ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

/ኢትዮጵያ ነገ ዜና/፡- በትናንትናው ዕለት እኩለ ሌሊት አከባቢ በምጥ ጣር ተይዛ ወደ ደምቢዶሎ ሆስፒታል በመሄድ ላይ የነበረችን ነፍሰ_ጥሩ እናት ተኩሰው የገደሉ ሦስት የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል ተባለ።

ብርሀኔ ማሞ የተባለች የ35 ዓመት ወጣት ምጥ ተይዛ በባጃጅ ወደ ደምቢዶሎ ሆስፒታል በማምራት ላይ እያለች በልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት በተከታታይ በተተኮሰ ጥይት ተደብድባ መገደሏ ህዝብን አስቆጥቷል። የባጃጅ ሾፌሩን ጨምሮ አብረዋት የነበሩ ዘመዶቿም መቆሰላቸውን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል።

የደምቢ ዶሎ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ዛሬ ቀኑን ሙሉ የተቃውሞ ሰልፍ ሲያደርጉ የዋሉ ሲሆን ድርጊቱን የፈፀሙ የጸጥታ አካላት በህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል። ከሰዓት በሗላም ድርጊቱን ፈፅመዋል የተባሉ ሦስት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።

የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት ይህን ድርጊት የፈፀሙት ሌላ አካል መስሏቸው ሳያጣሩ ወደ ባጃጁ እንደተኮሱ መናገራቸውም ተጠቁሟል።

/ፎቶው በደምቢ ዶሎ ከተማ ዛሬ የተካሄደ ሰልፍ ነው/

LEAVE A REPLY