የለውጡ ማነቆዎች /ፈይሳ በዳኔ/

የለውጡ ማነቆዎች /ፈይሳ በዳኔ/

ኢትዮጲያ የንጉሱን ስርአት አልፈልግም ብላ ከጣለች በሁዋላ በርካታ የፖለቲካ አመለካከቶችን እና ታሪካዊ ኩነቶችን አስተናግዳለች፡ ከያኔው ሶሻሊዝም እስከአሁኑ ግራ የገባው አቢዮታዊ ዲሞክራሲአዊ አስተዳደር ረስ፡፡ ከንጉሱ ከዙፋንመውረድ ጀምሮ ሀገራችን በርካታ መልካም አጋጣሚዎችን ብታገኝም በተለያየ ሰአት ሀይልን ይዘው የነበሩ አካላት እንዲሁም ህዝቡ ሊወጡ የሚገባቸውን ሃላፊነት መወጣት ባለመቻላቸው ዛሬ ለደረስንበት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ማህበራዊ ቀውስ ተዳርገናል፡፡ሆኖም ግን ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆናጠጠ ከ27 አመታት በኋላ በኢትዮጲያ ሰማይ ላይ የተሻለ የሚመስል የፖለቲካ ለውጥ እንቅስቃሴ በመታየት ላይ ነው፡፡ ጥያቄው ይህን መልካም አጋጣሚ እንደከዚህ በፊቶቹ ይባክናል ወይስ አንጠቀምበታለን ? ውጡን ሊያደናቅፉ የሚችሉ ክስተቶች ከኢህአዴግ ከራሱ ውስጥ ወይስ ከውጪ የሚመጡ ናቸው የሚለው ነው፡፡

በእርግጥ የአሁኑ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አስደናቂ በሆነ መልኩ ህዝቡን ማነቀሳቀስ (መደመር) ችለዋል፡፡ ግን ግን ይህ የመደመር ፖሊሲ ወይም አስተሳሰብ ሀገሪቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ያደርሳታል ወይስ ግዜያዊ ስሜታዊነት ነው? የሚለው ሌላኛው መነሳት ያለበት ሀሳብ ነው፡፡እንደሚታወቀው የኢትዮጲያ ህዝብ በአብዛኛው በተለያዩ ከተሞች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጎን መቆሙን እና ለመደመርም ያለውን ፍላጎት በግልፅ አሳይቷል ነገር ግን እነዚህ የመደመር እና የድጋፍ ሰልፎች በሚያስደንቅ መልኩ ተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸው ማህበረሰቦች ያደረጉት ሰልፍ እንደሆነ እና ከኢትዮጲያዊነት ይልቅ ሁሉም የየራሱን የፖለቲካ እምነት ያራመደበት መሆኑን ለማወቅ ይዘውት የወጡትን ሰንደቅ አላማ መመልከት ብቻ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጲያን እና ኢትዮጲያዊነትን የሚወክለው የትኛው እንደሆነ፤ ይህንን የተራራቀ አስተሳሰብ እንዴት ማስታረቅ ይቻላል የሚለው የአዲሱ ተቅላይ ሚኒስትር ዋነኛው የቤት ስራ እንደሆነ ለመገመት ምንም አነት ቀመር አያስፈልግም፡፡ ሌላኛው እና ዋነኛው ጉዳይ እነዚህ ሰልፎች ላይ ታርጌት የተደረጉ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ እንዲሁም ብሄር ተኮር የሆነ ጥላቻን ያዘሉ መፈክሮች እና ንግግሮች ሌላኛው የሀገሪቱ እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈተና ምንጮች እንደሚሆኑ ኣያጠራጥርም፡፡

የሆነው ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይዘውት የመጡት አዲስ አስተሳሰብ የሚደነቅ እና የሚበረታታ ነው፡፡ ሆኖም ግን የሚፈለገውን ሀገራዊ መግባባት እና ለውጥ ለማምጣት ከባድ ጫና እንደሚገጥማቸው ኣያጠራጥርም፡ ይኸውም፡-

1. አሁን ያለው የፌደራል መንግስት አደረጃጀት ብሄርን እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ መሆኑ እና በዚህም ምክንያት በርካታ ኢትዮጲያዊያን በዘራቸው ምክንያት ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ እተፈናቀሉ መሆኑ፤ ለዚህም እንደማሳያ ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ አማሮች፤ ከሶማሊ ክልል የተፈናቀሉ ኦሮሞዎች፤ ከሲዳማ የተፈናቀሉ የወላይታ ተወላጆች፣ በጉጂ ህዝብ እና በጌዲኦ ህዝቦች፤ በጉራጌ እና ቀቤና ህዝቦች አጎራባች ከተሞች በተፈጠሩ ግጭቶች የተከሰተው የህዝቦች መፈናቀል፡፡ ምንም እንኩዋን ይህ አደረጃጀት ከላይ ለተጠቀሱት ችግሮች መንስኤ ቢሆንም፤ በሀገሪቱ የሚገኙ አንድ አንድ ብሄረሰቦች ከዚህ የተሻለ የፌደራል ስርአት ሊኖር የችላል ብለው አለማመናቸው እና ለመቀበልም ዝግት የሌላቸው መሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጀመሩት ለውጥ ትልቅ እንቅፋት ሊሆን መቻሉ አያጠራጥርም፡፡
2. የተጀመረው የመደመር እና የአንድነት ጉዞ አግላይ መሆኑ (ተገልያለው ብሎ የሚያምኑ ግለሰቦች፣ ቡድኖች፣ ብሎም ከኣንድ ብሄርተውጣጡ ልሂቃን መኖራቸው)፣ ወደፊት ከባድ መዘዝ ሊኖረው መቻሉ ሌላኛው የአዲሱ ለውጥ ማነቆ ሊሆን መቻል እድሉ ቀላል አይሆንም፡፡
3. ሌላኛው እና ተጨማሪው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር፣ የፍቅር፣ እና የአንድነት ስብከት ውጪ እስከ አሁን ወደፊት ሊከተሉት አና ሊያራምዱት ሰለፈለጉት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚያዊ እና የማህበራዊ ለውጥ አቅጣጫ በግልፅ አለማስቀመጣቸው ቀጣይ የሀገሪትዋ እጣፈንታ ምን ሊመስል አንደሚችል መገመት አለመቻልም ተያይዞ ሊነሳ የሚችል ትልቅ ጥያቄ ነው፡፡
4. አራተኛው እና ዋነኛው በስረዐቱ ውስጥ በተለያዩ የስልጣን እርከን ላይ ያሉ የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች ለውጡን ለመቀበል እና ለማቀላጠፍ ያላቸው ፍላጎት ሌላው እና ዋነኛው ማነቆ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ባለፉተ 27 አመታት ለስልጣን መደላድል ያመቸው ዘንድ በምርጫ ቦርድ፣ በከተማ አስተዳደሮች፣ በክፍለ ከተማዎች፣ በቀበሌዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ዜጎች ባላቸው የትምህርት ዝግጅት እና ብቃት ሳይሆን ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት እና ወገንተኝነት ይኸውም የገዢው ፓርቲ አባል እና ደጋፊ መሆን እንደዋና መመዘኛ እየተቆጠረ ከመንግስት ስራ ይልቅ የፖለቲካ ተልእኮን እንዲያስፈፅሙ እና የአንድ ለአምስት የስለላ መዋቅርን እንዲያስፈፅሙ የተመደቡ ከመሆኑም በዘለለ ለእነዚህ የስርአቱ ደጋፊዎች ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማዘጋጀት ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ሀብት ብክነትን አስከትለዋል እያሰከተሉም ነው፡፡ ነገር ግን ከአንድ አመት ከስድሰት ወር በዃላ ሀገራችን ቀጣዩን ምርጫ እንደማስተናገዷ መጠን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢናገሩም፤ ከላይ የተጠቀሱት በተለየዩ የመንግስት ሀላፊነት ላይ ያሉት ግለሰቦች ለነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫ ዝግጁ ሆናሉ ብሎ ማሰብ እና መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ምክንያቱም የምርጫው ውጤት የመንግስትን ለውጥ የሚያስከት ከሆነ ጥገኛ ባለስልጣናት እና አስፈፃሚ አካላት በትምህርት ዝግጅታቸው እና ባላቸው ልምድ የተሻሉ ለሆኑ ዜጎች ቦታቸውን ለመልቀቅ የገደዳሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህ አካላት በአሁኑ ሰአት በትልቅ ስጋት አና ውጥረት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ከዚህም የተነሳ አነዚህ ሰወች እስካሉ ድረስ በኢትዮጲያ ውስጥ ነፃ እና ፍትሀዊ ምርጫን መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዙሪያቸው ከፍተኛ ባለስልጣናትን የደህንነት ሀላፊውንም ጨምረው በሌሎች ቢቀይሩም በደህንነት እና በሰራዊቱ መዋቅር ውስጥ በግልፅ የሚታይ ለውጥን መፍጠር አልተቻለም ይህም ቀጣዩን ምርጫ ከባድ ከሚያደርጉ በሀገሪቱ ውስጥ ያለውንም የመድብለ ፓርቲ ስርአት ከሚያዳክሙ ጉዳዮች ውስጥ በዋነኛነት ሊነሳ የሚችል ነው፡፡

በአጠቃላይ በሀገራችን የታየው የለውጥ ጭላንጭል እና ተስፋ ከባድ ፈተናዎች እንደሚጠብቁት መገመት ጨለምተኝነት አያሰኝም ይልቁንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በዙሪያቸው የሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሊያስቡበት እና ትኩረት ሰተው ሊሰሩት የሚገባ የቤት ስራቸው መሆን አለበት፡፡

ቸር ያሰማን!!!

LEAVE A REPLY