የተቋማትን ስም የመቀየር አባዜ! /በአቻምየለህ ታምሩ/

የተቋማትን ስም የመቀየር አባዜ! /በአቻምየለህ ታምሩ/

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚለው ስም የተቋም ስም እንጂ የከተማ ወይንም የቦታ ስም አይደለም። ኦ.ኤም.ኤን. በቅርቡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተካሄደን አንድ «የምሁራን ውይይት» ሲያስተላልፍ ዩኒቨርሲቲውን «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ብሎ ጠርቶታል። ይህ በጣም ስህተት ነው። የተቋም ስም የመቀየር አባዜ የተጀመረው በደርግ ነው። የተፈሪ መኮነን ትምህርት ቤትን፣ እቴጌ መነን ትምህርት ቤት፣ የጎበና አባ ጥጉ መታሰቢያን፣ ወዘተን የቀየረው ደርግ ነው።

ከነጭካኔው የደርግ ታናሽ ወንድም የሆነው ወያኔም እንደገባ ሆለታ የጦር ትምህርት ቤትን፣ አባ ዲና ፖሊስ ኮሌጅን፣ ኃይለ ማርያም ማሞ ትምህርት ቤትና ሆስፒታልን፣ ወዘተን ስም ቀይሯል። ፋሽስት ወያኔ ስም ከመቀየር አልፎ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፍልስፍና እየተመራ የታላላቅ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያዎችን አፍርሶ ቦታውን ለወገኖቹ ሰጥቷል። ወያኔ የጀግናውን ኮሎኔል የአብዲሳ አጋን፣ የአርበኛውን ራስ አበበ አረጋይንና የአያታቸው የራስ ጎበና ዳጨን፣ የመጀመሪያው የክቡር ዘበኛ አዛዥን የሙሉጌታ ቡሊን፣ የቀልቤሳ ቤካን፣ ወዘተን መታሰቢያዎች በግሬደር አፍርሶ ቦታውን ለመለስ ዜናዊ ወርቆች አድሏቸዋል።

በወያኔና ደርግ ስማቸው የተቀየሩ አብዛኛዎቹ ድርጅቶች ኢትዮጵያውያን ቅን አሳቢዎች የግል ቤታቸውን እየሰጡ የመሰረቷቸውን ተቋማት ነው። ሕሊና ላለው ግን ኢትዮጵያውያን ቅን አሳቢዎች የግል ቤታቸውን እየሰጡ የመሰረቷቸውን ተቋማት ስም ማንም የመቀየር መብት የለውም።

እንደመሰለኝ ኦ.ኤም.ኤን. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ብሎ የጠራው የአዲስ አበባን ስም ላለመጥራት ነው። እንደመሰለኝ ነው ያልሁ። የአዲስ አበባን ስም ላለመጥራት ካልሆነ ግን ዩኒቨርሲቲው «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» አልነበረምና ስህተት ነው። የአዲስ አበባ ከተማን ፊንፊኔ ብሎ መጥራትና የተቋሙን አዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲን ስም «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ብሎ መጥራት አንድ አይደለም።

ተቋሙን አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ብሎ መጥራት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኙነት [ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የከተማ ስሞች አላልሁም] ናዝሬትና ደብረ ዘይትን አዳማና ናዝሬት ብሎ በመጥራት እንደማስተማር አይነት ነው። የተቋም ስም አይቀየርም። የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተቋማዊ ስሙ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ነው። የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስሙ መጠራት ካለበት በመጀመሪያው ስሙ «ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ» ተብሎ እንጂ ከመነሻው ጀምሮ ዩኒቨርሲቲው ተሰይሞበት በማያውቀው አዲስ ስም መሆን የለበትም።

ኦ.ኤ.ኤን. አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ብሎ የጠራው የአዲስ አበባ የቀድሞ ስም ፊንፊኔ ነበር ከሚለው የኦነግ ትርክት በመነሳት ነው። ለነገሩ ፊንፊኔ የሚለው ቃል ግንድ አማርኛ እንጂ ኦሮምኛም አይደለም። ስያሜውም የወጣው ፍል ውሀውን ፊን፣ ፊን ይላል ከሚለው ነው። የኦነግ ተማሪ የሆነ ሰው የአዲስ አበባ የቀድሞ ስም ፊንፊፌ ነበር ብሎ ሊያምንና ከተማዋን ፊንፊኔ ብሎ ሊጠራት ይችል ይሆናል። ስም የመቀየር ጉዳይ ካልሆነ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ስም ግን «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» አልነበረምና ዩኒቨርሲቲውን «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ብሎ ሊጠራ የሚችልበት አንዳች አመክንዮ ሊኖረው አይችልም።

የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የግል ንብረት ነው። ሆኖም ግን ንጉሠ ነገሥቱ የግል ንብረታቸውን ለኢትዮጵያውያን መማሪያ እንዲሆን አበርክተውታል። ከታች የታተሙት ሁለት ዶሴዎች ለዚህ ማስረጃዎች ናቸው። የመጀመሪያው ዶሴ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የግል ንብረታቸውን ለሕዝብ ጥቅም እንዲውል በማሰብ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ሲወስኑ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን በፊርማቸው አረጋግጠም ወደ ሕዝብ ንብረትነት ያስተላለፉበት ዶሴ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ የግል ንብረታቸው የሆነውን ግቢ ዩኒቨርሲቲ እንዲሆን ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከለወጡ በኋላ የተቋሙን ይፋዊ የስራ ጅማሮ አስመልክቶ የጣሉት የመሰረት ድንጋይ ነው።

ስለዚህ የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የቀድሞው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ይባል ነበር የሚል መከራከሪያ የሚያነሳ ሰው ከሌለ በስተቀር አበባ ዩኒቨርሲቲ «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ተብሎ ሊጠራ አይችልምና የተቋም ስም መቀየሩ መታረም ይኖርበታል። ኦ.ኤም.ኤንም ምክንያታዊ ሜዲያ ነኝ ካለ ወይ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደ ተቋም «ፊንፊኔ ዩኒቨርሲቲ» ይባል እንደነበር የሚያውቀው ካለ ማስረጃ ካለው ያቅርብና ያሳየን አልያም ስም በመቀየሩ ይቅርታ ሊጠይቅና ሊያስተካክል ይገባል!

LEAVE A REPLY