ይድረስ በተለይ ለተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች -ነፃነት ዘለቀ

ይድረስ በተለይ ለተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች -ነፃነት ዘለቀ

በሰው የሚጠሉት ወይም እንደሚጠሉት የሚናገሩትን ራስ ሲያደርጉት የማያስጠላ ከሆነ የተሳከረ ስብዕና (MPD) ባለቤት የመሆን ችግር አለ ማለት ነውና በቶሎ መታከም ያስፈልጋል፡፡ እኔ ለምሣሌ በወንድሜ ወይ በጓደኛየ ላይ የማየውንና የምቃወመውን መጥፎ የመሰለኝን ምግባር እኔ ራሴ ባደርግና እንደነውር ባልቆጥር ትክክል አይደለሁም፡፡ ጨለማና ብርሃን ኅብረት እንደሌላቸው ሁሉ በአንድ ሰውነት ውስጥ ሁለትና ከዚያ በላይ ተቃራኒ ሰውነቶች ሊኖሩ አይችልም፡፡ እንደዚያ ያለ ችግር በፖለቲካው መስክ በጉልኅ እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ አንቀጽ መግቢያየ መሆኑ ነው፡፡

ትናንት የሀገራችን – በአዲሱ አጠራር – የፖለቲካ ተፎካካሪዎች በጠ/ሚኒስትሩ ተጠርተው ውይይትና የምሣም ግብዣ ማድረጋቸውን በሚዲያ ተከታትለናል፡፡ እጅግ በጎ ጅምር ነው፡፡ በሀገራችን ለዘመናት ስንመኘው የነበረና በነዚህ ባሳለፍናቸው ጥቂት የለውጥ እንቅስቃሴ ጎልቶ በታየባቸው ወራት ውስጥ እናያለን ብለን ያልገመትነው ነገር ነው፡፡ ፖለቲከኞቹ ከዚህ መልካም ጅማሮ ብዙ ነገር እንደተማሩ መገመት ይቻላል – ለመማር ፈቃደኛ ከሆኑ፡፡ በባህላችን እንካ ያሉት ዳቦ እርካሽ እንደሆነ መኖሩ አውኮን እንጂ በቀደምት አምባገነን ገዢዎች ዘንድ እንደዜጋና እንደሰውም መቆጠር ብርቅ እየሆነባቸው በየማጎሪያ ቤቶች እየታጨቁ ስንትና ስንት ግፍና በደል ይደርስባቸው የነበሩ ተቃዋሚዎች ይህንን የመሰለ ክብር ሲያገኙ ቢያንስ የጌቶች ጌታ የሆነውን ኅያው እግዚአብሔርን – የሚያምኑ ከሆነ ነው እሱም-  ቢበዛ ደግሞ ለዚህ ማዕረግ ያበቃቸውን የሕዝብ ትግልና የወጣቶች መስዋዕትነት ክብር ሊሰጡት በተገባ ነበር፡፡ ይቺ ዕድል እንዲህ በቀላሉ አልተገኘችም፡፡ እንኳንስ ተቃዋሚዎች ጠ/ሚ ዐቢይ ራሱ የንጹሓን ዜጎች ደምና አጥንት ነው ወደላይ አሽቀንጥሮ ለዚህ የታሪክ ኃላፊነት ያበቃው – ኃላፊነቱ ባለው እቶናዊ የሚጋረፍ ሙቀት የተነሣ የሚቀናበት ባይሆንም፡፡ ነገር ግን በሀገራችን የተለመደው ነገር ሌላ ሆነና ተቸገርን፡፡ አንድ ያገሬ የኔ ቢጤ (“ለማኝ” ላለማለት ነው) እንዲህ አለ ይባላል – “ስንቅ ያለቀበት ጌታ ‹ደጅህ ላይ ቆሟል› ብለህ ለጌታህ ንገረው!”፡፡ መግደርደርና መኮፈስ በመንደር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በላይኛው እርከንም መታየቱ እየጎዳን ነው፡፡… እንጂ አሁን “በምድርህና በሕዝብህ መሀል በሰላም ታገል” ተብሎ ተጠርቶ ሲያበቃ ሕዝብን ማመስና ትጥቅ አልፈታም ማለትን ምን ያመጣው ነበር? ለማንኛውም የነፃነትን አየር ገና በጨረፍታው ከመተንፈሳችን ያን ለዘመናት ያንገፈገፈንን የቆሪጥ አገዛዝ እንዳታመጡብን ተቃዋሚዎች አቅል ግዙልን፤ ከራሳችሁም፣ ከመንግሥትም ጋር በቀናነት ተግባቡ፡፡ እናንተስ ሾልካችሁ ብትሄዱ መውጫ መግቢያውን ታውቁታላችሁና ምንም አትሆኑም፡፡  ለኛ ለተገፋነው አስቡልን፡፡ …

የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን ስብሰባ በቲቪ ስመለከት ብዙ የተደበላለቀ ስሜት አደረብኝ፡፡ ጎላ ብሎ የተሰማኝ ግን ሀገራችን በሁሉም ረገድ ዕድለኛ አለመሆኗ ነው፡፡ በርካታዎቹ ፖለቲከኞች ዕድሜያቸው ከመግፋቱ የተነሣ ራሳቸውን ችለው ስለመራመዳቸውም ተጠራጠርኩ፡፡ እንዲህም አልኩና ራሴን ጠየቅሁ “ይሄ ፖለቲካ የሚሉት ነገር ጡረታ የለውም ማለት ነው?” ጥያቄየ ሳላስበው ቀጠለ “እነዚህ ሀፍረትና ይሉኝታ የሚባሉ ነገሮች ከትግራይ – ከወያኔ ትግሬዎች መፈልፈያ ዋሻ –  ብቻ ሣይሆን ከመላው ፖለቲከኞቻችን ጭንቅላት ውስጥም ሙልጭ ብለው ወጥተው ይሆን?” አልኩ፡፡ ነገር በሦስት ሲሆን ይጸናልና እንዲህ ስል ጥያቀየን ሰለስኩ – “በዚህ ሁኔታ የዚህች ሀገር የመኖር ዋስትና ምንድን ነው?” አዎ፣ ከ“ታላላቆች” እንዲህ ያለ ስሜት-አልባነት (insensitivity) ከተስተዋለ ከተራው ዜጋማ ምን ሊጠበቅ? “የዓሣ ግማት ከአናት” መባሉ ትክክል ነው፡፡ ሁላችን ተያይዘን የዝቅጠት ቁልቁለቱን የምንነጉደው አለምክንያት አልነበረም፡፡ ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን?

አንዱ አንዱን ሲያማ ጀምበር ልትጠልቅ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች በመንግሥት ወንበር ላይ ያሉትን “ሥልጣን ርስተ ጉልት መሰላቸው እንዴ? የሥልጣን ገደብ ተበጅቶለት መሪዎቻችንን በዙር ለምን አንመርጥም?” ለማለት የሚቀድሙት ተቃዋሚዎች ናቸው፡፡ ይህን የሚሉ ተፎካካሪዎችን በየድርጅታቸው በሚገኙ ወንበሮች አንዳንዶቹ ከ25 ዓመታት በላይ መጎለታቸውንና በፈረንጅኛው አነጋገር እዚያው ወንበር ላይ vegetate ማድረጋቸውን ሳስበው አፈርኩ፡፡ በሀገሬ ዕድልም አዘንኩ፡፡ ከተሰብሳቢዎቹ ውስጥ በጣም ጥቂት ጎልማሦችን ብቻ ነው ያየሁት፡፡ አብዛኛው ያረጀው ያፈጀው የኢህአፓውና በኋሊዮሽ አቆጣጠር ከዚያም የሚያልፈው ትውልድ ነው – አንዳንዶቹ እንዲያውም ከዐቢይ ጋር መግባባት ሊሣናቸው የሚችሉ ጎምቱዎች ናቸው፡፡ ደግነቱ የመድረኩ መሪ – ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ – ወጣት መሆኑ ትንሽ ተስፋ አጫረብኝ እንጂ ዱሮ ወጣት ሳለሁ የፖለቲካ ቡድን መሪ የነበሩ የያኔዎቹ አንጋፋዎች አሁንም በ80 እና በ90ዎቹ ዕድሜያቸው እዚያው ሙጭጭ ብለው ስመለከት በኢትዮጵያ ውስጥ ንግግርና ተግባር እጅግ የተለያዩ መሆናቸውን አስታወስኩ – አውሮፓ ውስጥ ብሆን ኖሮ – ብቻየንም ብሆን ሠልፍ ወጥቼ “shame on you dear octogenarians and nonagenarians!” እል ነበር – ዕድሜ ፀጋ መሆኑንና በአግባቡ ከተጠቀሙበት የሚያስከብር መሆኑን አውቃለሁና ትችቴን ከዐውድ ውጪ በሌላ መልክ እንዳትተረጉሙብኝ አደራ፡፡ ይህ ራስን የማምለክና ሌሎችም እንዲያመልኩብን የማስገደድ አባዜ ቤተ መንግሥቱን አልፎ ወደ ተቃዋሚዎች መውረድ ነገንም ከዛሬው በበለጠ እንድንፈራው ቢያስገድደን አይፈረድብንም፡፡ ክፉ ዐመል፡፡

በዚህች የበሬ ግምባር በማታህል ሀገር እንደሚባለው 70 እና 80 የፖለቲካ ኩይሣ ካለ የበሽታ እንጂ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ከ310 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አሜሪካ እንኳን ሁለት ታላላቅ ፓርቲዎች ናቸው ያሏት፤ ከዚህ አንጻር የኛ በርግጥም አለመታደል ብቻ ሣይሆን ትልቅ እርግማን ነው፡፡ ይሄ ሁሉ ፓርቲ ደግሞ በጎሣ የተመሠረተ ነው ማለት አንችልም፡፡ ለይምሰል ያህልም ቢሆን የሃሳብና የአመለካከት ልዩነትም አለበት፡፡ ስለዚህ ችግሩ የጎሣና የሃይማኖት ብቻ ሳይሆን እነሱን ሽፋን አድርጎ በሃሳብና በአመለካከት የተለያዩ በማስመሰል የጥቅምና የሥልጣን ፍትጊያ እንደሆነ መገመት አይከብድም፡፡ ከ“ፍቅር እስከመቃብር”  የሚቀጥል “የሥልጣን ጥም እስከ መቃብር” በሚል መጽሐፍ ቢጻፍ ጥሩ ነው፡፡

አንዲት ትል ከመሀል ሸዋ በጧት ተነስታ እየገሠገሠች ስትሄድ እዚያው መሀል ሸዋ አንድ ሰው ያያታል አሉ፡፡ “አንች ትል ወዴት ትሄጃለሽ?” ብሎ ይጠይቃታል፡፡ እርሷም “መተማ!” ብላ ትመልስለታለች፡፡ እሱም ይቀጥልና “ትደርሻለች?”ይላታል፡፡ እርሷም “ልብማ!” ትለውና መንገዷን ትቀጥላለች፡፡ እኛም በነዚህ ጎምቱ የፖለተካ አበጋሮች የዴሞክራሲ ጥማታችን ሊረካ ጫፍ ላይ ደርሰናል፡፡…

የኛም ነገር እንደትሊቱ መሆኑ ነው፡፡ በ1983 እና ከዚያ ወዲህ እንደአሸን የፈላው ይሄ ሁሉ የፖለቲካ ድርጅት ጉዞው ወደ አራት ኪሎ ነው፡፡ ግን የትም ሳይደርስ ዕድሜውን ብቻ በመቁጠር አብዛኛው የድርጅት መሪ አራት ኪሎን በልቡ እንደሰነቀ አረጃና አሁን ጠማማ ጣሳ መስሎ በህልሙ ብቻ ጠ/ሚኒስትርና ፕሬዝደንት እንደሆነ ቀረ – ላልተለመደ ግልጽነቴ ይቅርታ፡፡ እንደሚመስለኝ እንደኛ እንደ ኢትዮጵያውያን ሥልጣንና ሀብት ወዳድ በዓለም ያለ አይመስለኝም፡፡ ለሥልጣን በተለይ ጉጉ ነን፡፡ ለዚያም ስንል አይደለም ሀገርና ሕዝብ ልጃችንንም ቢሆን ሳንሸጥ የማንቀር ብዙዎች ነን፡፡ መጥፎ ተፈጥሮ፡፡ ለዚህ ይመስላል እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ትንንሽ ዘውዶችን አናቱ ላይ ጭኖ እንደሚንቀሳቀስ አንዳንድ የፖለቲካና የማኅበረሰብ ሥነ ልቦና ተንታኞች የሚናገሩት፡፡ የሥልጣን ሱሳችንን በስያሜዎች ሳይቀር መገንዘብ እንችላለን፡፡ “የኢዴፓ ፕሬዝደንት፣ የመዐሕድ ፕሬዝደንት፣ የኢመማ ፕሬዝደንት፣ የኢ.ቤ.መ ፕሬዝደንት፣ የአኢወማ ፕሬዝደንት፣ የኢሠማ ፕሬዝደንት፣ የ‹መኢጠማ› ፕሬዝደንት…” የብዙ ተቋማትን ኃላፊዎች ወይም ሊቃነ መናብርት ስያሜ ስንመለከት “ፕሬዝደንት” ነው የሚለው፡፡… እንዲህ ከሆነ እኔም የስድስቱ ቤተሰቤ ፕሬዝደንት ሆኜ ራሴን በራሴ መሾሜን በዚህ አጋጣሚ ሳልገልጽ ባልፍ ይቆጨኛል፡፡ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ደግሞ በምክትል ፕሬዝደንትነት ተሰይማ የቤት እመቤትነት ሥራዋን እንድትቀጥል ዛሬ ማታውን የሹመት ደብዳቤዋን እሰጣታለሁ – በልጆቻችን ፊት፡፡ ከጊዜው የሴቶች ሀገራዊ የሥልጣን ክፍፍል አኳያ ግን ይህ ሹመት መመርመር ሳይኖርበት አይቀርም፡፡ ቢሆንም እኔ ግን ሞቼ እገኛታለሁ እንጂ የፕሬዝደንትነቷን ሥልጣን  አልለቅም፡፡ … ይሁን፡፡ ፈገግታም የሕይወት ቅመም ናት፡፡

እባካችሁ እናንት አረጋውያን የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች!

አንጀቴ እያረረ በራሴ እስከመቀለድ የበቃሁት በናንተ ሁኔታ ስለተበሳጨሁ ነው፡፡ አላስፈላጊ ብዛታችሁን በተመለከተ እንደተመከራችሁት ቢቻል ወደ ሁለት አለበለዚያም ወደ ሦስትና አራት ውረዱ፡፡ ሰባና ሰማንያ ፓርቲ ሕዝብን ያወናብዳል፣ የሀብት ምንጭንም ያራቁታል እንጂ ለሀገር አይጠቅምም፡፡ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ሊይዝ የሚችለው የጠ/ሚኒስትር ብዛትም አንድ ብቻ ነው፡፡ በመቶና ሁለት መቶ ሥፍራ ተቧድኖ ለአንድ ቦታ መወዳደር ደግሞ አላዋቂነት ነው፤ ሕዝብ ይታዘባችኋል፡፡ ስለዚህ የዚህ ሁሉ ጎራ ዋናው ልዩነት የሥልጣን ጉዳይ እንጂ ሌላ ባለመሆኑ በቶሎ ንቁና ተሰባሰቡ፡፡ በዘርና በሃይማኖት ፓርቲ መመሥረት ደግሞ የስብዕና ክስረት ነው፡፡ ይህን ከሌላው ዓለም ተማሩ፡፡ በተለይ በዚህ በሰለጠነ ዘመን በጎሣና በሃይማኖት መሰባሰብ ከእንስሳም መውረድ ነው፡፡ ለአንዲት ቦታ አትራኮቱ፡፡ ሕዝቡን አድምጡት፡፡ ሕዝቡ ከእናንተ በላይ የነቃ ነው፡፡ የዝምብ ልጃገረድንና የቁንጫ ጠንጋራን የሚለየውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ማታለል በፍጹም አይቻልም፡፡ በበቀደሙ ስብሰባችሁ ለምሣሌ ብዙ ሰው ሆዱን ይዞ ሲስቅባችሁ ተመልክቻለሁ፡፡ እኔም ፍርፍር ብዬ ስቄያለሁ፡፡ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ካሙዙ ባንዳንና ሮበርት ሙጋቤን በተቃውሞው ጎራ ተጎልተው እንደማየት ምን እሚያስቅ ነገር አለ?

የዚህችን ሀገር ፖለቲካ እያበለሻሸ ያለው ትውልድ እንደሚመስለኝ ከ60 እስ 90 አካባቢ ያለው የቀደመው ትውልድ ነው፡፡ እናንተ ቢቻል ዕረፉ፤ ባይቻላችሁና የመታየትና የመወደስ እንዲሁም የዝነኝነትና የታዋቂነት አባዜ ናላችሁን እያዞረ የሚያስቸግራችሁ ከሆነ በወጣቶች ጀርባ አማካሪ ሆናችሁ ለሕዝቡ ታዩት፡፡ በእናንተ ቦታ ግን የተማሩ ወጣቶችን ተኩና ከድካማችሁ ዐረፍ በሉ፡፡ ይሄ “ያለ እኔ ሀገር ትጠፋለች” የሚለው የምትክ-የለሽነት አስተሳሰብ (sense of indispensability – which is, to me, a psychopathic problem))  አሳውሯችሁ እንዳይቀር ወደ ኅሊናችሁ ተመለሱና ከእናንተ የተሻሉ ወጣት ዜጎችን በመተካት ሕዝቡን ካሱት፡፡ አሪስቶትል ይሁን ፕሌቶ እንዲህ ብሏል አሉ “ተማሪ ከመምህሩ ካልበለጠ መምህሩ ደከመ እንጂ ዘር አልተካም፡፡” ግሩም አባባል ነው፡፡ እኛ ግን የፈዘዘ ቅጂ (ኮፒ) እየተውንና ራሳችንን እምሰማየ ሰማያት እየሰቅልን መሥራት የሚገባንን ሣንሠራ ሀገሪቱን ሰው-አልባ አድርገን አስቀረናት፡፡ ዶ/ር ዐቢይን ተመልከቱ፡፡ ይህ ብላቴና ትናንት ማንም የማያውቀው ፈጣሪ ከሰማይ ዱብ ያደረገው የሚመስል የሀገር አለኝታ ነው፡፡ እግዜር ቢፈልግ ኖሮ ብዙ የደከሙትን ኢንጂኔር ግዛቸውን ወይም ፕሮፌስር በየነን ያስነሳ ነበር፡፡ ያ አቅቶት አይመስለኝም፡፡ ግን የሁሉንም ልብና ኩላሊት የሚመረምር ፈጣሪ እነጎልያድን ትቶ ትንሹን ዳዊት አስነሳ፤ ምናልባት ጎልያዶችን በጎልያዶች ማጥፋት አልፈለገ ይሆናል – የፈጣሪ ሥራ እንደዚህ ነው፡፡ ከዚህ እንኳን ብዙ መማር በተገባ፡፡

በመሠረቱ በዚህች ዓለም ሁላችንም ነቁጥ ነን፡፡ ምንም ያህል እንማር፣ ምንም ያህል ሀብትና ገንዘብ ይረን፣ ምንም ያህል ዝነኞችና ታዋቂዎች እንሁን፣ በሕይወት ዘመናችን ምንም ዓይነት ተዓምር እንሥራ …  ዕድሜያችን ግን ውሱን ናት – ይህን ሌጣ እውነት ከተፎካካሪ ፖለቲከኞች ስብሰባ በጣም ተገንዝቤያለሁ፡፡ በሽታ ባያውቀን፣ ማጣት ባይደፍረን፣ ፍቅር ሞልቶ ቢፈሰን … እርጅናን ግን ልናስቀራት አንችልም፡፡ ታዲያ ለዚህች  ዕድሜ ብለን ለምን በሥልጣንና በሀብት ሱስ እንጠመዳለን? ለዚህች ከንቱ ዓለም ለምን የወገኖቻችንን ቁስል እያነፈረቅን በፖለቲካ ቁርቋሶ ሰበብ የሕዝብን ዕንባ በከንቱ እናፈሳለን? መንግሥቱና መለስ ኢትዮጵያን ልክ እንደእጅ ሥራ ዳንቴላቸው ቆጥረው ሲጫወቱብን፣ “እኔ ከሌለሁ ሁሉም የለም” ከሚል ዕብሪትና ትምክህት ያለነሱ ኢትዮጵያ አንድም መሪ ሊሆን የሚችል ዜጋ እንደማታፈራ አስበው ብዙ ተጫወቱብን፡፡ መጨረሻቸውን ስለምናውቀው አናነሳውም፡፡ ከንቱ ሰው መጨረሻውም ከንቱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የወላድ መካን አይደለችም፡፡ አይሳካልንም እንጂ የወላድ መካን ልናደርጋት የምንፋጭረው እኛው ነን – በተለይ ትልልቆቹ፡፡ ሰውን እንንቃለን፤ ወጣቱን በተለይ አናስጠጋውም – ልክ እንደዝንጀሮ አባት – ዐቢይ አህመድ ከዝንጀሮ አባቶች እንዴት እንዳመለጠ ይገርመኛል – ለነገሩ እንዴት እንዳመለጠ እርሱ ራሱ በአንድ ወቅት ተናግሮታል – ክፋታችን እኮ ወደር የለውም፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ከሀገራችን ይልቅ ለሥልጣናችን ቀናኢ መሆናችን ነው፤ ለሀብትና ለገንዘብ ስሱ ነን፡፡ እንጂ ብዙ የተማሩ ሰዎች አሉ፡፡ እነሱን እየመከርንና እያቃናን ወደ ኃላፊነት ብናስገባቸው በአዲስ አስተሳሰብ አዲስና ለሁሉም የምትመች ሀገር መሥራት በተቻለን፡፡ አሮጌ ምን ጊዜም አሮጌ ነው፡፡ በ83 የፖለቲካ ቅኝት 2011ን ልንመራው አንችልም፡፡ ዝንታለማችንን ዳውድ ኢብሳ ወይም በየነ ጴጥሮስ ወይም አረጋዊ በርሃ ወይም መርሻ ዮሴፍ እያልን መኖር አልነበረብንም፡፡ አሜሪካኖች የአንድን ሰው ፊት ከስምንት ዓመታት በላይ እንዳያዩ በህጋቸው የወሰኑት ወደው አይደለም፡፡ የመንግሥት ጥውርስ ጠበንጃ ስላለው – ታንክና መትረየስ ስላለው – ይሁን ግዴለም፤ የአንድን የፖለቲካ ተፎካካሪ መሪ ማለቴ “ፕሬዝደንት” ግን እንዴት ለ30 ዓመታት እንድመለከት ዕድሜ ይፍታህ ይበየንብኛል? ይችም ዕድል ሆና? እነዚህ ሰዎች ዛሬ ወይም ነገ ወደማይቀሩበት ሊሄዱ ይችላሉ፡፡ እነሱ ሄዱ ማለት ደግሞ ቢያንስ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ኢትዮጵያም ሄደች – እስከወዲያኛው ነጎደች ማለት ነው፡፡ ይብላኝ ለነሱ እንጂ ኢትዮጵያ ግን ትኖራለች፡፡ ዐፄዎቹ ሄዱ፤ መንግሥቱም ሄደ፤ መለስም ተጓዘ፣ “ኃይለ ማርያም”ም ከ“ሥልጣን” ወረደ – ኢትዮጵያና ሕዝቧ ግን አሁንም አሉ፤ ወደፊትም ይኖራሉ – እንዲያውም ከአሁኑ በተለዬ አምሮባቸውና በዓለም ላይ ደምቀው፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የፖለቲከኞቻችን ነገር መስተካከል ያለበት ነገር አለ፡፡ አስተሳሰባችን ካልተቀየረ የሀዘንና የልቅሶ ዘመናችን በአጭር ላይቋጭ ይችላል፡፡

እናም ውድ ወንድሞቼና አባቶቼ!

       እባካችሁን ልቀቁን! የተሸከማችሁትን ታሪካዊ ኃላፊነት ለወጣቱ አስረክቡ፡፡ ወደ ፍቅርና መተሳሰብ ማዕድም ቅረቡ፡፡ የቆዬ ቂማችሁንና ጥላቻችሁን ትታችሁ መጀመሪያ እርስ በርሳችሁ ዕርቅ አውርዱ – የጎሪጥ መተያየታችሁን ተውት፤ ለወጣቱ ትውልድ አርአያ ሁኑ፡፡ ብታዩት የአሁኑ ትውልድ ከእናንተ ቂምና በቀልን እንጂ ሌላ ነገርን ስላልተማረ ትቷችሁ የራሱን ኑሮ በራሱ ዓለም እየኖረ ነው፡፡ እናንተ ግን በዱሮው በሬ እያረሳችሁ በ “ማን አባት ገደል ገባ” የልጆች ጨዋታ ትቆራቆሳላቸሁ፡፡ በመሀሉ  ሀገርን ለማፍረስ ቀን የሚጠብቁ ወገኖች የእናንተን አለመስማማት እንደወርቃማ ዕድል ይጠቀማሉ፡፡

ዕድሜ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ከሚጻፈው፣ ከሚነገረው፣ ከሚታየው፣ በራስ ላይ ከሚደርሰው የሕይወት ተሞክሮ  መማር ካልተቻለ ከምን ይማሯል? በራስ ዓለም ብቻ በምናብ እንደተመላለሱ ማርጀት ለአወንታዊ የካርማ መዝገብ (Karmatic Record) ጠቃሚ አይመስለኝም፡፡ ከፀጉር መሸበት ጋር የሚመጡ ብዙ ነገሮች አሉ፤ እነዚያን አለመገንዘብ ሽበትን ማስወቀስ ይሆናል – ድንጋይና እንጨትም ይሸብታሉና፡፡ እናም ነገ ዛሬ ሳትሉ እናንተ ታረቁና በትረ መኮንናችሁን ለወጣቱ ስጡ፡፡ ስታስረክቡም 70 እና 80 ኢትዮጵያን ሳይሆን አንዲት ኢትዮጵያን አስረክቡ፡፡ በቃ፡፡ ለመማር በጣም ዝግጁ ነኝ፤ ባጠፋሁ ይቅርታ፡፡ netsanetz28@gmail.com

LEAVE A REPLY