መላኩ ፋንታን ያገኘሁት ዕለት | ሐብታሙ አያሌው

መላኩ ፋንታን ያገኘሁት ዕለት | ሐብታሙ አያሌው

አቶ መላኩ በሚኒስትር ማዕረግ የፌደራል ገቢዎች እና ጉምሩክ ዳይሬክተር ሆኖ በተሾመ ጊዜ ባስመዘገበው ፈጣን ለውጥ ይታወቅ ነበር። ኋላ በጉራ ፋርዳ ማንነት ላይ በተመሰረተ ጥቃት በተለይ በሽፈራው ሽጉጤ ልዩ ትዛዝ አማራ ይነቀል የሚለው የግፍ ደብዳቤ ለጥፋት በተላከ ጌዜ ያንን ግፍ በማውገዝ ቀዳሚ እንደነበረም የታወቀ ነው።

የመለስን ሞት ተከትሎ ባህርዳር በተደረገው የአዴፓ ጉባኤ ደግሞ ዛሬ ምሽጉን መቀሌ ያስቆፈረው በረከት ስምዖንን “የዚህ ምስኪን ህዝብ መፈናቀል ህመሙ ላንተ ብዙም ላይሰማህ ይችላል” በማለት እንደሸነቆጠው ይነገራል።

ከዚህም ከፍ ሲል የአማራ ክልል ተወላጅ ባለሃብቶችን በማስተባበር ክልሉን እንዲያለሙ ማግባባት መጀመሩ በበረከት ዘንድ በጎሪጥ እንዲታይ አድርጎት ነበር። እናም ቂመኛው የስምዖን ልጅ ቀን ጠብቆ ወህኒ ወረወረው። ከነዚያ ክፉ ቀኖች በአንዱ አቶ መላኩ ፋንታ ከአቶ ገብረዋህድ ጋር በካቴና የቁራኛ ታስሮ ከልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወደ ቀሊቲ ሊወሰድ በማረሚያ ቤት ፖሊስ ወደተከበበችው መኪና ሲገባ አይን ለአይን ተገጣጠምን።

ቀይዳማ መልኩ ገርጥቷል ሉጫ ፀጉሩ ቅጥ አምባሩ ጠፍቶ ብስጭቱን ለመግለፅ ግንባሩ ላይ ተገታትረው ወደሚታዩ ደምስሮቹ ተንጨባርረው አዘቅዝቀዋል። መቀመጫ ቦታ ስላልነበረ በካቴና ባልታሰረ አንደኛው እጁ የመኪናውን ወንበር ጨበጥ አድርጎ ሲቆም ልቤ አዘነለት።

ከኔ ጋር ቁራኛ ከታሰረው ጓደኛዬ ጋር በገባ ወጣ ተጠጋጋን እና እንደምንም አስቀመጥነው። ከኔ ኋላ ያሉት በተመሳሳይ ትብብር ገብረዋህድን ሲያስቀምጡት በቁራኛ የታሰረ እጃቸው ፊት እና ኋላ ተጠማዞ እንደተወጠረ ነበር። አማራጭ የለም በዛ ሁኔታ እስከ ቃሊቲ የሆድ የሆዳችንን እያወራን ተጓዝን።

ቀን ቢያስጎነብስህ እግዚአብሔር ያቀናል እንዲሉ…
አዴፓ አቶ መላኩ ፋንታ አልማን እንዲመራ ሹመት መስጠቱን ገልጿል። እሱም ለሹመት እኔም ኖሬ ለመፃፍ ደርሰናል !!

ይህ ሹመት ሽንፈት ለማይወደው ለበረከት ስምዖን ትልቅ ውርደት ነው፤ የመሸነፉ ማሳያ መቀሌ ሂዶ ደብቁኝ ማለቱ ብቻ አይደለም፤ በካቴና አስሮ ዘብጥያ የጣላቸው እሱ ያወደማትን አገር ሊሰሩ የመሪነት ወንበሩን መቆናጠጣቸውም ነው።

ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን !!

LEAVE A REPLY