“የሚያጀግነውን የሚያውቅ ህዝብ የተባረከ ነው” | በውቀቱ ስዩም – ከየካ

“የሚያጀግነውን የሚያውቅ ህዝብ የተባረከ ነው” | በውቀቱ ስዩም – ከየካ

ባገራችን የነገስታት መታሰቢያ ሀውልት ማቆም: በጀግና ተዋጊዎች ስም ጎዳናዎችንና ትምርትቤቶችን መሰየም የተለመደ ነው። አገሩ በሙሉ በጦርና ጋሻ ምልክት የተሞላ ቢሆንም አሁንም በወታደሮች: በጌቶችና በእመቤቶች ስም ሀውልት የማቆም ግፊቶች ቀጥለዋል። በፖለቲካው ግርግር መሀል: ለህዝብ መንፈሳዊ እና አእምሮአዊ እድገት መዋጮ ያደረጉ ሰዎች ተዘንግተዋል።

ለምሳሌ ዛሬ ድረስ ላዝማሪ ሀውልት ማቆም ተስኖናል። ግን አዝማሪዎች ባይኖሩ ጀግኖች አይኖሩም። ባልቻ ሳፎን የምናስታውሳቸው ወይዘሮ ፃድቄንና ሀሰን አማኑን የመሳሰሉ አዝማሪዎች ገድላቸውን እንዳንረሳቸው አድርገው ስለዘመሩልን አይደለምን? ከባልቻ ያልተናነሰ ጀብድ የፈፀሙ ጀግኖች አዝማሪ አይንና ቀልብ ስላልረፈባቸው ተዘንግተው ቀርተዋል። ያጋነንሁ ከመሰላችሁ ይበልጥ ሞቅ ላርገው!! አዝማሪ የሌለው ህዝብ ትውስታ የለውም።

ቀደምቶቻችን ቤተ -እምነት እንጂ ቤተ-ሙከራ ገንብተው አላወረሱንም። በዚህ ምክንያት አገሩ የሳይንስና ምርምር ምድረበዳ ሆኖ ቆይቷል። በድሃ አቅማችን: ወደ ጨረቃ መንኮራኩር መላክ ብናስብ ቅብጠት ይሆናል። ወደ ጨረቃ ዙሮ መሽናት ቂጥኝ ያስይዛል ብሎ የሚያምን ትውልድ እንዳይኖር ለማድረግ ራሱ ብዙ ይቀረናል። ባለምአቀፍ ደረጃ ለሳይንስ መዋጮ ያደረጉ ሊቃውንታችን ብሄራዊ ጀግኖች አድርጎ ማስተዋወቅ አንዱ መፍትሔ ነው ብየ አስባለሁ::
“የጋቢሳ እጄታ ጎዳና ” : የ አክሊሉ ለማ መታሰቢያ : አየር ማረፍያ : “የ ተወልደ ገብረእግዚያብሄር ፓርክ ” ማየት እመኛለሁ። አገርን ዳርድንበር ከጠላት የሚከላከልንን ብቻ ሳይሆን ከጠንቀኛ ባክቴርያና ቫይረስ የሚከላከለንን ማጀገን ይጠብበቅብናል።

ለዘር ማንዘርህ ብቻ መዋደቅ እርፍና በሆነበት አገር: ሰው ሳይመርጡ ሰው የሚያገለግሉ ሰዎች የጀግና መታሰቢያ ያስፈልጋቸዋል። “የጀግነት ሁሉ አባት ፍቅር ነው” ይል ነበር ይድነቃቸው ተሰማ። የሜቄዶኒያውን ቢኒያምና አበበች ጎበናን የመሳሰሉትን በጎ አድራጊዎች ሳስብ ትዝ የሚለኝ ይህ አባባል ነው።

ወዘተረፈ..

ባገራችን ከጥንት እስከዛሬ የጀግንነት ትርጓሜ ከጦርነት አልወጣም። ምናልባት የጀግነትን ትርጉም ስንቀይር ያለንበት ሁኔታ ይቀየር ይሆን?

LEAVE A REPLY