የፍቅር ሰራዊቱ በመገስገስ ላይ ነው – ጉዞ ዓድዋ 6 | ያሬድ ሹመቴ

የፍቅር ሰራዊቱ በመገስገስ ላይ ነው – ጉዞ ዓድዋ 6 | ያሬድ ሹመቴ

መልካም በዓል!

ከ1ሺህ ኪ.ሜ. በላይ የሚፈጀው የእግር ጉዞ ከአዲስ አበባ ጥር 7 2011 ዓ.ም. ቀን ከተጀመረ በኋላ እንዲህ ሆነ፦

*ከሐረር (የድሬ ልጆች) ከዘመቱ 4 እግረኛ ተጓዦች ጋር የተቀላቀሉት 44 የአዲስ አበባ ዘማቾች መንገዱን 48 ሆነው ስለፍቅርና የኢትዮጵያ አንድነት እየዘመሩ በመትመም ላይ ናቸው።

*ኤርሚያስ የተባለ ጀግና ተጓዥ በባዶ እግሩ ያለ ጫማ ከመነሻ እስከ አሁን በመጓዝ ላይ ነው። (ብርታቱን ይስጥህ)

*ይድነቃቸው የተባለ ተጓዥ በደረሰበት የእግር ህመም ጉዞውን መቀጠል ተስኖታል። ከዚህ ቀደም የመኪና አደጋ የደረሰበት በመሆኑ መንገዱ ህመሙን ቀስቅሶበታል።

*የመጀመሪያውን ቀን ጉዞ ጨርሶ ሌሊቱን ህመሙ ስለፀናበት በማግስቱ ጉዞውን ለማቋረጥ ወሰነ። 30 ኪ.ሜ. ገደማ እንደተጓዘ የዘመቻ ጓዶቹን ተሰናብቶ ወደ አዲስ አበባ በእግሩ መመለስ ጀመረ።

*በጉዞ ዓድዋ ባህል መሰረት ቢያንስ የእለቱን ጉዞ መጨረስ አለበትና፤ የ1 ሰዓት መንገድ ከተጓዘ በኋላ እንዲመለስ ተነገረው። የቀሩት ተጓዦችም እሱን ለመጠበቅ ባሉበት እንዲቆሙ ሆነ።

*የካሜራ ባለሙያው ዳዊት ቤራ ይድነቃቸውን ለመደገፍ ተመለሰ። ይድነቅ ጓዶቹ ጋር እስኪቀላቀል ድረስ ጀግናዎቹ የጉዞ ዓድዋ ልጆች የአንድ ሽማግሌ ቤት የጭቃ ምርግ ስራ ሲያግዙ የአዛውንቱንም ቤት ግንባታ ለ3 ሰዓታት ያህል ሲረዱ ዋሉ።

*ይድነቃቸው ከሶስት ሰዓታት በኋላ ተመልሶ ተቀላቀላቸው። ምሽትም ሲሆን በሰንዳፋ ማደሪያ ሰፈር ላይ ስንብት ተደረገለት። ይድነቅ ጫማውን እና ለጉዞ ያስፈልጉኛል ብሎ ያዘጋጃቸውን ስንቅና ትጥቁን በሙሉ ለተጓዦች በማስታወሻነት አበርክቶ ወደ አዲስ አበባ በክብር ተሸኘ። “ጉዞው እስኪጠናቀቅ እግሬ ቀረ እንጂ ልቤ አብሯችሁ ይጓዛል” ሲል እንባ ተናንቆት ተሰናብቷል።

*የሰንዳፋ ከተማ አስተዳደር ለተጓዦች ማረፊያ ምሳ ራትና ቁርስ በመጋበዝ ከፍተኛ ድጋፍ አድርጓል።

*የአሌልቱ ከተማ ወጣቶች እና የአካባቢው ማህበረሰብ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን ደማቅ አቀባበል አድርገዋል። ራት ከተበላም በኋላ ተጓዦች በአማርኛ፣ በትግርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሶማልኛ ጋባዦቻቸውን መርቀዋል። እንግዳ ተቀባዮቹ የአሌልቱ ነዋሪዎችም በአማርኛ በኦሮምኛና ጉራግኛ ባህላዊ ምርቃት አድርገው፤ ቋንቋ መመራረቂያ እንጂ መራራቂያ መሆን እንደማይገባው አሳይተዋል።

*ለጥምቀት በተጎዘጎዘ ለምለም ሳር፤ በተጠረገ አውራ ጎዳና የኢትዮጵያ ህብረት ዜማዎች እየተዘመሩ፣ ፍቅርና መተሳሰብ እየተመሰከረ ጉዞው ቀጥሏል።

*ሐሙስ ገበያ ላይ የአንድ ምስኪን ገበሬ ለአጨዳ የደረሰ ማሳ 47ቱም ዘማቾች በደቦ አጭደው ከምረዋል። እንኳን እግራቸው ሊዝል ክንዳቸው ጀግኗል።

*የዓድዋ ድል ነፀብራቅ በታየበት በዘንድሮው ጉዞ ዓድዋ 6 ላይ ትልቅ መልዕክት ገና ከጅማሬው ተላልፏል። “የምናቋርጣቸው የሀገራችንን መንደሮች እንጂ ድንበሮች አይደሉም”

#ፍቅር_ለኢትዮጵያ!!
#ኢትዮጵያዊነት_ይለምልም!!
~ደብረ ብርሐን ጥር 14 ~ደሴ ጥር 23 እንገናኝ
~የኢትዮጵያዊያን የፍቅር ድምጽ ይቀጥላል!!

LEAVE A REPLY