በረከተ መርገምት | መሳይ መኮንን

በረከተ መርገምት | መሳይ መኮንን

ሰው ሁኖ ከሞት ወንጀለኛ ሆኖ ከፍርድ ማምለጥ አይቻልም። በእርግጥ ዋናው መያዙ ነው። ለፍርድ መቅረቡ የፍትህ ፈላጊ ዜጋ ሁሉ ጥያቄ ነበር። እውን የዶ/ር አብይ አስተዳደር ዋናዎቹ አሳዎች ላይ ወኔ አጣ ብለው ሲጠይቁ ለነበሩ ዛሬ በተወሰነ ደረጃ ምላሽ ያገኙበት እርምጃ ነው የተወሰደው። የበረከት ስምዖን እጆች የብረት ካቴና ጠልቆባቸዋል። በፍትህ ሳጥን ውስጥ ቆሞ ፍርድ ሲሰጠው ልናይ ነው። ትልቅ ነገር ነው።

የፕ/ር መስፍንን አባባል ዛሬም ልድገመው። ”መለስ በራሱ ክፉ ነው። መለስን የበለጠ ክፉ ያደረገው ግን በረከት ስምዖን ነው” የክፋት አለቃ፡ የተንኮል ፊት አውራሪ፡ የጭካኔ ደቀመዝሙር፡ የቅጥፈት አምባሳደር፡ የመጥፎ ነገሮች ሁሉ ተምሳሌት በረከት ስምዖን በመጨረሻም የሚገባውን አገኘ። ወንጀለኛ ነህና ወደ እስር ቤት ትገባለህ የተባለው ይፈጸም ዘንድ እነሆ ጊዜው ደረሰ። ፊተኞች ኋለኞች ሆኑ። በሰፈሩት ቁና ተሰፈሩ። ባዋረዱት ህዝብ ፊት የፍትህን አርጩሜ ቀመሱ።

የበረከት መታሰር ለህወሀት ተጨማሪ ውርደት ነው። ቅጥሬን አላስነካም ብሎ መቀሌ የመሸገው ህወሀት መጨረሻው አጉል እንደሚሆን ተጨማሪ ምልክት ያየበት ቀን ነው ዛሬ። በረከት ለህወሀቶች ትልቅ ሀብት ነበር። ከህወሀት በላይ ህወሀት ሆኖ የኖረ፡ ምንጣፋቸውን እየጎተተ፡ ስጋጃቸውን እያጸዳ በፕሮፖጋንዳውና ማደራጀቱ በኩል የጀርባ አጥንታቸው በመሆን ያገለገለ ታማኝ ባሪያቸው ነበር። አቶ ስብሃት ነጋ እንደበረከት ስምዖን የሚጠሉት ሰው አልነበረም ነው የሚባለው። ነገር ግን ከህወሀት አጠገብ እንዲጠፉ ከማይፈልጓቸው ሰዎች አንድ ሰው ምረጡ ቢባሉ በረከት ስምዖንን እንደሚሉ ውስጥ አዋቂዎች ይመሰክራሉ። እንደበረከት ህወሀትን በቀውጢ ሰዓት ያገለገለ ጥሩ ባሪያ አለመኖሩ ለአቶ ስብሃት ቢጠሉትም እንዲርቃቸው የማይፈልጉት ሰው ሆኖባቸዋል።

በረከት ሌላው ቢቀር ለቅሶ በማደራጀት፡ ሀገርን ከዳር እስከዳር ማቅ አልብሶ ለህወሀት የፓለቲካ ትርፍ አፈር ከድሜ የሚግጥ ምርጥ አገልጋይ እንደሆነ በህወሀት ድርሳን ላይ በደማቁ የተጻፈለት ታሪኩ ነው። መለስ ዜናዊ ነፍሱ ከስጋው እስክትላቀቅ ከልቡ የሚያምነው ሰው በረከት ስምዖንን እንደነበረም ይነገራል። መቃብር አብሮ መውረድ አይቻልም ሆኖበት እንጂ ከመለስ ጋር አፈሯን አብሮ መቀመስ ቢቻል ኖሮ በረከት ስምዖን ይህን ጊዜ ስላሴ ጓሮ ይሆን ነበር። አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ”መለስ በመሞቱ ወላጅ አልባ ከሆኑት ሰዎች አንዱ በረከት ስምዖን ነው” ያለበት ጽሁፍ ትዝ አለኝ።

ከለውጡ በኋላ በነበሩት ሁለት ወራት በረከት የጥፋት በትሩን ይዞ፡ የዕልቂት አቁማዳውን ሸክፎ ሰሜን ጎንደርን ሲያካልል እንደነበር እናስታውሳለን። ደብረማርቆስ ላይ በረከት ተገኘ የተባለበት ሆቴል ጥቃት ከደረስበት በኋላ በድንጋጤ መደበቅን የመረጠው በረከት ስምዖን ለውጡን ለማወክ፡ ከተቻለም በሁከትና ትርምስ የአራት ኪሎ ቤተመንግስትን ዳግም በህወሀቶች እጅ ለማስገባት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም። ከትክል ድንጋይ እስከ ሰቆጣ፡ ከመቀሌ አዲስ አበባ እየተመላለሰ የጥፋት ድግስ ሲያሰናዳ እንደነበርም መረጃዎች ወጥተዋል። ባለፉት ስምንት ወራት ጎንደርን ሲያስጨንቃት በነበረው የቅማንትና የአማራው ማህበረሰብ ደም ያፋሰሰ ግጭት ቀማሚ፡ አርክቴክት በረከት ስለመሆኑ ከጥርጣሬ ያለፈ ሀቅ ነው። ጎንደር አሁን ገና እፎይ አለች። ባህርዳር ላይ ዛሬ የወጣው መፈክር ”ኢትዮጵያ እፎይ አለች” የሚል ነበር። እውነት ነው።

በእርግጥ የህዝቡ ቁጣና ምሬት ለበረከት ጥሩ ምልክት ስላልነበረ በመጨረሻም ከጌቶች ቅጥር መደበቅን መርጧል። ያለፉትን አምስት ወራት ከመቀሌ ጓዙን ጠቅልሎ የገባው በረከት፡ በለውጡ ሃይል ላይ የጭቃ ጅራፉን እያጮኽ፡ በእነአሜሪካን ላይ ጣቱን እየቀሰረ፡ ቆይቷል። እቀመጥ እተኛበት አጣሁ ሲል በአደባባይ የደረሰበትን በደል የገለጸው የህወሀቱ ጎብልስ በመጨረሻም የሚቀመጥበትና የሚያርፍበት ተሰጥቶት ልምናውና ምኞቱ ከዳር ደርሶለታል። በነገራችን ላይ ጎብልስ ለዓላማው እስከቀራኒዮ ተጉዟል። በጠላት እጅ አልወድቅም ብሎ 6ልጆቹን በመርዝ ገድሎ፡ ሚስቱን ሽጉጥ አጠጥቶ እሱም ጠጥቶ ሞቷል። የጎብልስ የባህሪ ወራሽ የሆነው በረከት እንደጎብልስ ራሱን ማጥፋት አልፈለገም። ፈሪ ነው።

የበረከት መታሰር ብዙ ትርጉም አለው። ዝም ብሎ መታሰር አይደለም። ከእስርም በላይ ነው። ለህወሀት ደግሞ ሌላ ዙር ሞት ነው። ቀጣዩ ማን እንደሆነ ምልክት ያሳየ እስር ነው። የአህያ ባል ከጅብ አያስጥል ነገር ነው የሆነው። ህወሀት አብዲ ዒሌን ማትረፍ አልቻለም። በረከትንም ሊያስጥል አቅም አጥቷል። ስለራሱም እርግጠኛ አይደለም።

የዶ/ር አብይ መንግስት የኦነግን ግንባር በድል ካጠናቀቀ በኋላ ወደ ሁለተኛው ግንባር ፊቱን ለማዞር መዘጋጀቱን የሚያመለክት ነው የበረከት የዛሬው እስር። በሳል አካሄድ ነው። ሁለት ግንባሮችን በአንድ ጊዜ መግጠም ውጤት አይኖረውም። ለሽንፈትም የሚዳርግ ነው። የኦነግ የ6ወራት እርግጫ በሽንፈት ተጠናቋል። የመከላከያ ሰራዊቱ የኦነግ ሰራዊት ላይ ያሳረፈው ብርቱ በትር ግንባሩን እጅ እንዲሰጥ አድርጎታል። ሽንፈትን ‘እርቅ’ በምትል ማንጠልጠያ መገልጹ አይከፋም። እውነታው ግን ሌላ ነው። ኦነግ ተንፍሷል። ወደ ሁለተኛው ግንባር የዞረው የዶ/ር አብይ መንግስት የህወሀትን ጉዳይ በአቶ በረከት አሟሽቷል። እንደሚቀጥል ተስፋ ይደረጋል።

የበረከት እስር ለአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ፖለቲካዊ ድል ነው። አዴፓ/ብአዴን ውስጥ የተሰገሰገው የበረከት ሰንሰለት እየበጣጠሱ ለቆዩት አቶ ገዱ በዛሬው ዕለት የበረከት ቅሬትን ከአዴፓ/ብአዴን ውስጥ አጽድተው ለመጨረሳቸው ማረጋገጫ የሰጡበት እርምጃ ነው። አዴፓ/ብአዴን በረከትን ያሰናበተ ጊዜ ከህወሀት ባርነት መላቀቅ ችሎ ነበር። ሆኖም በአቶ በረከት አማካኝነት ከታች መዋቅር ጀምሮ ጸረ ገዱ አንዳርጋቸው እንቅስቃሴ እንዲደረግ ህወሀቶች እንቅልፍ አጥተው አድረዋል። ገዱ አንዳርጋቸውን በመፈንቀል ዳግም የምስለኔ አገዛዙን ለማስቀጠል ፍላጎት የነበረው ህወሀት ዛሬ እርሙን አውጥቷል። ከበረከት እኩል ባይሆንም እንደእነከበደ ጫኔ ያሉ የህወህት አደግዳጊዎችም በዝምታ ሊታዩ አይገባም። ጊዜው የጥሎ ማለፍ ነው።

የበረከት መያዝ ከጥረት ኩባንያ ሙስና ጋር መያያዙን ብዙም አልወደድኩትም። ዋናው የሰውዬው ከርቸሌ መውረድ ነው በሚል ተቀበልኩት እንጂ በረከት በሰው ልጅ ላይ በፈጸመው የሰብዓዊ ወንጀል ነበር ፍትህ ፊት ቆሞ ማየት የሚያስፈልገው። በእርግጥ ይህ ጅምር ሊሆን ይችላል። በቀጣይ በሌሎች ወንጀሎች ፋይል እንደሚከፈትበት እጠብቃለሁ። በረከት ገንዘብ አጠፋ ተብሎ መከሰሱ ለእሱ ከሽልማት የሚቆጠር ነው። በረከት ትውልድ ነው ያጠፋው። በረከት ሀገር ነው ያወደመው። በረከት የአማራ ክልል ወንጀለኛ ብቻ አይደለም። ከሞያሌ እስከመቀሌ፡ ከጂጂጋ እስከ ቄሌም ወለጋ በጥብቅ የሚፈለግ ወንጀለኛ ነው። ባህርዳር ላይ ሳይሆን አዲስ አበባ ላይ ፍርዱ መታየት ያለበት ሰው ነው።

ለማንኛውም ዛሬ በረከትን ወደ ከርቸሌ ሸኝተናል። አሜሪካ ናት ያሳሰረችኝ የሚለውን ለቅሶ እዚያው ፍርድ ቤት እንሰማዋለን። የመቀሌ ቅጥር መነቅነቁ አይቀርም። የፌደራሉ መንግስት ማንኛውንም ህጋዊ መስመር ተከትሎ የትግራይ ክልል ለህግ ተገዢ እንዲሆን ማድረግ ቀጣዩ ስራ ነው። የወንጀለኞች ጎሬ የሆነውን የትግራይ ክልል ከህወሀት እጅ ፈልቅቆ በመውሰድ አጠቃላይ የቀውሱን ዘመን መቋጨት ግድ ይላል። በህግ መስመር ካልሆነ ደግም ከበጀት ማቋረጥ አንስቶ በፌደራል መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች ይጠበቃሉ። የትግራይን ህዝብ በማይጎዳ መልኩ የህወሀትን ትዕቢት የሚያስተነፍሱ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ሊታሰቡ ይገባል። ህወሀት ሲርበው እጅ እንዲሰጥ የሚያደርግ ስትራቴጂ ያስፈልጋል።

LEAVE A REPLY