ኢህአዴግ ኪሎው ስንት ነው? | ዓለማየሁ ገላጋይ

ኢህአዴግ ኪሎው ስንት ነው? | ዓለማየሁ ገላጋይ

ቹቹ ጅሉ መንደርተኛችን ነው። በጅልነት አካባቢውን እያዝናና (እሱ ባያውቀውም ቅሉ) ኑሮውን ያለሀሳብ ይመራል። የዕለት ጉርሱን፣ የዓመት ልብሱን የሚያገኝባቸው ብዙ ተፈጥሯዊ አስቂኝ ድርጊቶች አሉት። አንድ ጊዜ እናቱ ወደገበያ ለመሄድ ከቤት ሲወጡ ጠርተው ‹‹አንተ ከርፋፋ፣ ይሄን የተሰጣ ቅመም ጠብቅ፣ ዝናብ ይምታውና አንተን አያድርገኝ›› ይሉታል። ይሁንና ሰማይ እያጉረመረመ ማንባት የጀመረው እናቱ ብዙም ሳይርቁ ነበር። በቹቹ ስላልተማመኑ ወደቤት ሲመለሱ ቹቹ በደረቱ ተኝቶ ዝናብ ሲመታው ያያሉ።
‹‹ምን እያደረክ ነው?›› ጠየቁ
‹‹ቅመሙን ዝናብ እንዳይመታው ከልዬልሽ ነዋ›› አለ አሉ።
ከዚህ ፅሁፍ ጋር ግንኙነት ወዳለው ወደሌላኛው የቹቹ ጅሉ ተፈጥሯዊ ትወና እናምራ። አንዲት ጐረቤት የስምንት ወር ልጇን ለቹቹ እያስታቀፈች ‹‹ጋግሬ እስክጨርስ ከያዝካት ትኩስ እንጀራ በበርበሬ እሰጥሃለሁ›› ትለዋለች። ቹቹ ይስማማል። ሴትየዋ ገና አንድ እንጀራ እንዳሰፋች ልጇ አምርራ ስታለቅስ ትሰማለች። እየተንደረደረች ወደ ቹቹ በመሄድ ‹‹ምን አደረካት?›› ስትለው
‹‹ፀጉሬን ያዘችኛ ታዲያ›› አላት
‹‹እና…?…››
‹‹እኔም ፀጉሯን ያዝኳታ›› ተመጣጣኝ ምላሽ መሆኑ ነው።
አንዳንድ ጊዜ (ብዙ ጊዜ ላለማለት) ይሄ መንግሥት እንደቹቹ ጅሉ የጨቅላ ደመነፍሳዊ ድርጊት ለሚባሉ ጉዳዮች ሳይቀር በእኩያነት ምላሽ ሲሰጥ ይገኛል። ጠላት አይመርጥም። ኢሕአዴግን ነክቶ ይንቀኛል ማለት ቹቹ ጅሉ ያገናዝባል እንደማለት ነው። ለፀብ ‹‹መልቲ ሲስተም›› ነው። ያገኘውን ይጐርሳል። ትንሽ ከትልቅ ሳይለይ፣ በእኩያነት-ፍርሃት ኃይሉን ሳይመጥን ያሳርፋል። ትንሹን አለመናቅ ብቻ ሳይሆን፣ ትልቁንም ያለመፍራት አለማገናዘብ አለው። ዝቅ ሲል ከአንተና ከእኔ ጋር ይጣላል፤ ከፍ ሲል ከእራሷ አሜሪካ እና አሜሪካ ከፈራችው አሸባሪ ጋር ይገጥማል። ይሄን ስናይ ኢህአዴግ ኪሎው ስንት ነው? ብለን መጠየቃችን ግድ ነው። እውነት፣ እውነት ይሄ መንግሥት ኪሎው ስንት ነው?
ነገር በፈለከው ዕለቱን የፀብ ቱታ ለብሶ በርሃ ላይ ለቦክስ ሲያሟሙቅ ታገኘዋለህ። የተጋጣሚውን ማንነት የሚያጣራው ከቡጢ በኋላ ነው። ትንሽ ታግሎ ሲጥል በትንሽነት እንደሚመዘገብ ልብ አይለውም። ከግለሰብ ጋር ባደረገው ፍልሚያ ያገኘውን ከገመና የሚቆጠር ድል በአደባባይ (በቴሌቪዥን) እያሳየ ይፎክራል።
ለመሆኑ ኢህአዴግ ኪሎው ስንት ነው?
ይሄ መንግሥት የሰውነቱን መደርጀት፣ የዕድሜውን መግፋት ነገር ከፈለገው ግለሰብ አንፃር እንዳያይ ተጭበርብሯል። ከአንተ ጋር ሲጣላ ጀትና ታንክ ያለው፣ ሒሊኮፕተር የሚገጣጥም፣ አዳፍኔ የሚያመርት ግዙፍ መንግሥት መሆኑን ረስቶ ነው። ባለው ኃይል ይከመርብሃል። ከተጨፈለቅክ በኋላ መረጃ ያሰባስብበሃል። የዚህ መንግሥት ድርጊት ብዙ ጊዜ ያናድዳል፣ አንዳንዴ ያሳዝናል፣ ሌላ ጊዜ ያስቃል። የሚያናድደውንና የሚያሳዝነውን ታውቀዋለህ፣ የሚያስቀውን እኔ ልንገርህ።
ደራሲ አውግቸው ተረፈ (ትክክለኛ ሥሙ ህሩይ ሚናስ) ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› ጋዜጣ ላይ ይሰራ ነበር። በመካከሉ ድንገት የአእምሮ ህመም ስለደረሰበት ከቢሮ ይቀራል። አንዳንዴ ጋዜጣው የሚዘጋጅበት ግቢ ቢመጣም አይገባም። ፊት ለፊት ቆሞ ኢህአዴግን ይሳደባል። ‹‹ሌባ›› ይላል። የሥራ ባልደረቦቹ አባብለው ከአካባቢው ገለል ያደርጉታል፣ በሚቀጥለው ቀን እንደሚመጣ ቢያውቁም።
እነዚህ አውግቸውን የሚያባብሉና ፍራንክ የሚሰጡ የሥራ ባልደረቦች በከፍተኛ ሁኔታ ተገመገሙ አሉ፡-
‹‹ከፀረ ሕዝብ ጋር የተለየ ግንኙነት አላችሁ›› ተባሉ።
‹‹ከማን ጋር?›› ‹‹ከአውግቸው ተረፈ ጋር››
‹‹እንዴ፣ እሱ’ኮ ያመዋል እንጂ…››
‹‹ቢያመውም የፀረ ሕዝብ አስተሳሰብ ሰርፆበታል፤ እሱን ማነጋገርና መደገፍ ፀረ-ሕዝብነትን መርዳት ነው።››
ቹቹ ጅሉን መሆን አይደል? አትጠራጠር! ኢህአዴግ ኪሎ የለውም። ለፀብ የተጋበዘበት ቦታ ሁሉ በደስታ ይገኛል። ካላመንክ ጋብዘውና እየው፤ ከፈራህ ታሪኩን መርምረው። ከደረሰብህ ይኮረኩምሃል፤ ካልደረሰብህ ባሻገር ይሰድብሃል። መግለጫ የባሻገር ስድብ አይደል?
የወረቀት መድፍን የቃላት አረር አጉርሶ ‹‹ደም የሚያስቀምጥ›› የስድብ መዓት ካወረደባቸው አካላት መካከል አሜሪካንን፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልንና ሲፒጄን መጥቀስ ይቻላል የዚያን ሰሞን ሰማያቸውን ‹‹በአዲስ-ዘመን›› ጋዜጣ ጋረደባቸው። ያውም በአራት በአራት ገፅ። ይሄ መንግሥት ‹‹አቅሙን አያውቅ›› የሚሆንብን ከአሜሪካ ጋር ሲሰፋፈጥ ብቻ አይደለም። ከተለያዩ አለማቀፍ ድርጅቶች ጋር ሲሰዳደብም ነው። እነዚህ ድርጅቶች ጥርስ የሌላቸው አንበሳ እንደሆኑ ቢያውቅም ከልፊያ ከሚቆጠረው የፀብ ግብዣ አይቀርም። ጥርስ ከሌለው አንበሳ ጋር የሚያስቅ መነካከስ ይገጥማል። ጥርስ ከሌለ መነካከስ መኮራኮር አይደል? እንዴት አያስቅ?
አትጠራጠር! ኢህአዴግ ኪሎ የለውም። ውሎም አይመርጥም።
አርቲስት፣ ሳይንቲስት፣ ነጋዴ፣ መደዴ፣ ድምጻዊ፣ ባህታዊ፣ ጋዜጠኛ፣ ምታተኛ… ሆንክ ግድ የለውም። ፀብ ጋብዘው፣ ፀብ አይጠየፍም። አገር ሆንክ አህጉር፣ ግለሰብ ሆንክ ስብስብ ‹‹በመልቲ ሲስተም›› ፀበኛ እኩያህ ብቻ ሳይሆን አብሮ አደግህ መስሎ ያስተናግድሃል። ኪሎህን ከኪሎው ሳያማጥን ይከመርብሃል። ፀብ ከተባለ እንደ ህንድ አማልክት ብዙ እጅ አብቅሎ የብዙዎችን ክሳድ ይጨመድዳል።
በእርግጥም ኢህአዴግ ሠፈሩ እንጂ እርሱ ኪሎ የለውም። ከአንተ ጋር በእኩያነት ተናንቆ በማግስቱ ከአልሸባብ ጋር ሠፈሩ ድረስ ሄዶ ይገጥማል። ለማጣጣም ይጥራል። ደግሞ ሌላ ጊዜ መንፈስ ይከተላል፣ ሞገድ ያሳድዳል፣ ከቢቢሲ ይነታረካል፣ ከአልጀዚራ ይተራጐማል፣ ከቪኦኤ ይተናነቃል፤ ጣለኝ ልጣልህ፣ እልህ ይገጥማል።
በዚህ የመንግሥት ባህርይ ሁሌም አንናደድም፣ አንዳንዴ እናዝንለታለን። ምክንያቱም ከ‹‹ፔስ ሜከሩ›› ጋር በጠላትነት ይፎካከራል፣ ከቻለ ጠልፎ ይጥላል። ማንፀሪያውን በማጥፋት እራሱን ያደበዝዛል። ትራኩን ቢቆጣጠርም ለብቻ መሮጥ መወዳደር ሳይሆን የእብደት መፈንጨት እንደሆነ አይረዳውም።
ኢህአዴግ ኪሎ የለውም!
ኢምንቱን እንደግዙፍ ይገጥማል። የኢህአዴግ ነገር ‹‹ዶሮን ስለፈሯት በመጫኛ ጣሏት›› ነው። ይሄ የሥነ-ልቡና ቀውስ ነው። የዶሮን አቅም የማያገናዝብ የመጫኛ መጥለፍ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ኢሕአዴግ ብትወድቅበትም ቢወድቅብህም እንደሚጐዳህ የማያውቅ ከሆነ፣ የሥነ-ልቡና ቀውስ ይሉሃል ይሄ ነው! ድርጅት እንደ ድርጅት የሥነ- ልቡና ቀውስ ይኖረዋል? የሚለውን ትተን የቀውሱን ምንጭ እንምዘዝ፡-
ግለሰብ ህብረተሰብ እንደሚሆን ከወያኔ ሓርነት ትግራይ የሰባት ሰዎች ምሥረታ ተረድቷል፡፡ ስለዚህ ግለሰብን እንደህብረተሰብ ይመለከታል። ‹‹ከአፍሪካ አንደኛ ግዙፍ ጦር›› የነበረውን ደርግ ገርስሷል፤ አሁን ከአፍሪካ አንደኛ ግዙፍ ጦር ቢኖረውም ሊገረሰስ እንደሚችል ይጠረጥራል። ‹‹እንዳያልፉት የለም…›› ሲል ዘምሯል፤ በእንዳይዘመርበት ይሰጋል። የውጪን መገናኛ ብዙሃን በደርግ ላይ አስተባብሯል፣ አሁን እንዳይተባበሩበት ይሰጋል… ወዘተ።
ታዲያስ? ‹‹የደርግ Syndrome›› እንበለው? ወይስ…?

1 COMMENT

  1. I ԁоn’t drop a ton of responses, but I glanced thгough a few comments here ኢህአዴግ ኪሎው ስንት ነው?

    | ዓለማየሁ ገላጋይ | Ethiopia Nege. Ӏ actually Ԁo һave 2 questions fߋr you if it’s okaʏ.
    Ⅽould it Ƅe only mе or do a few of theѕe remarks cօme ɑcross as if theʏ are
    written by brain dead individuals? :-Р Αnd, if ʏou arе writing on additional online sites, Ӏ
    woulԀ like tο follow anythіng fresh yοu have to post.

    Couⅼd yоu list оf the completе urls of your
    public sites ⅼike your twitter feed, Facebook ρage оr linkedin profile?

LEAVE A REPLY