“ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!” ይላሉ፣ ከዛስ? | ስዩም ተሾመ

“ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!” ይላሉ፣ ከዛስ? | ስዩም ተሾመ

ዛሬ በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት ግለሰብ ንግግራቸውን ያሳረጉት ቅኔያዊ በሆነ ምሳሌያዊ አነጋገር ነበር። ነገሩ እንዲህ ነው፤ በአንድ አርሶ አደር ቤት ውስጥ የገባችን አይጥ በዱላ ለመምታት ባልና ሚስት ዱላቸውን ሰድረው ሳለ አይጧ እሮጣ ከእንጀራ ምጣዱ ስር ትገባለች። ይህን ግዜ ባልዬው አይጧን በዱላ ሊመታ ሲል ሚስት እጁን ለቀም አድርጋ አስቆመችውና “ተው ውዴ … ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!” አለችው ይባላል።

በእርግጥ አባባሉን የተናገረው በትግሪኛ ቋንቋ ነው። ምክንያቱ ደግሞ አባባሉ በትግራይ አከባቢ የሚዘወተር ስለሆነ ይሁን ወይም ለማስተላለፍ የፈለገው ቅኔ ይኑር አላውቅም። እኔ ግን በአይኔ-ህሊናዬ የተሳለው የሆነ ቲያትር ነው። የቲያትሩ ተዋናዮች፤ አይጧ እንደ “ጌታቸው አሰፋ”፣ ቤቱ እንደ “ትግራይ ክልል”፣ የእንጀራ ምጣዱ እንደ “ኢትዮጵያ”፣ አርሶ-አደሩ እንደ ዶ/ር አብይ አህመድ፤ እንዲሁም እንደ የአርሶ-አደሩን ሚስት ገፀ-ባህሪ የሚጫወተው ደግሞ የቲያትሩ ደራሲ የሆኑት የፅሁፉ አቅራቢ ናቸው።

አርሶ አደሩ አይጧን በዱላ ለመምታት ሲሞክር የእንጀራ ምጣዱን ሊሰብር ይችላል። አይጧን ለመምታት ተብሎ ምጣዱ ከሚሰበር አይጧ ሳትመታ ቢቀር ይሻላል። በዚህ መሰረት ዶ/ር አብይ እንደ አይጥ መቀሌ የመሸገውን ጌታቸው አሰፋን ለመምታት/ለማሰር የሚወስደው የኃይል እርምጃ ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ይችላል። ስለዚህ ለኢትዮጵያ ሲባል አቶ ጌታቸውን ማለፍ ይሻላል የሚል መልዕክት አለው።

በእርግጥ መልዕክቱ በቀናነት ለሀገር ሰላምና ለህዝብ ደህንነት ከማሰብ የመነጨ ነው። ነገር ግን ዋናው ጥያቄ “ዛሬ ለምጣዱ ሲባል የተውናት አይጥ ነገ ላይ ምን ትሰራለች?” የሚለው ነው። አይጧ ከትላንት ስህተቷ ተምራ በአርሶ-አደሩ ቤት ውስጥ ያሉትን ዕቃዎች ማተራመስ፣ መቅደድ፣ ማፍሰስ፣ መብላት፣ ማጥፋት፣… ወዘተ ትተዋለች? አትተውም። ይህቺ አይጥ ዛሬ ቢተዋት እሷ አትተውም። በድጋሜ ነገ ቢያባርሯር ወደ ምጣዱ ስር ትሮጣለች።

ነገም “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!” ብለው ቢተዋት ከነገ ወዲያ የቤቱን ዕቃዎች ማተራመስ፣ መቅደድ፣ ማፍሰስ፣ መብላትና ማጥፋት አትተውም። ነገር ግን እሷን በዱላ ለመምታት ሲሞክሩ ምጣዱን አሊያም ድስቱን ይሰብራሉ።

በእርግጥ አይጧን ከተዋት ነገም ምጣድና ድስት ይኖራቸዋል፤ እንጀራና ወጥ ግን አይኖራቸውም። ምክንያቱም አይጧ እስካለች ድረስ እንጀራውን ትበላለች፣ ወጡን ትበክላለች። አይጧ የጥፋት አመሏን ትታ ከአርሶ-አደሩ እና ባለቤቱ ጋር በሰላም መኖር ትችላለች? አትችልም። ታዲያ ምን ይሻላል? “ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ!” ማለት መፍትሄ ይሆናል? አይሆንም። ስለዚህ አይጧን በዱላ ለመምታት ከመሞከር ይልቅ በወጥመድ መያዝ የተሻለ ይመስለኛል።

LEAVE A REPLY