እስኪ ዛሬ እንኳን ሰው ይውጣን? | በፈቃዱ ዘ. ኃይሉ

እስኪ ዛሬ እንኳን ሰው ይውጣን? | በፈቃዱ ዘ. ኃይሉ

‘ርዕዮት ሚዲያ’ “ተርጉሜዋለሁ/አስተርጉሜዋለሁ” ባለው የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ ንግግር ውስጥ፣ በቀረበላቸው ጥያቄ ላይ ተመሥርተው መልስ ሲሰጡ “ከተሜነት አስፈላጊ መሆኑን ተረድተን፣ ለዚሁ ቁጥር አንድ የሆነው የዴሞግራፊ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት እየሠራንበት ነው። ለምሳሌ ከሶማሌ ክልል የተፈናቀሉትን 500 ሺሕ ኦሮሞዎች ለምነንም ቢሆን ወደ ቀያቸው መመለስ እንችል ነበር። ነገር ግን በከተሞች፣ በፊንፊኔ ዙሪያ እያሰፈርናቸው ነው። 6 ሺሕ ሰዎችንም አዲስ አበባ አስፍረናል” ብለዋል ተብሏል (ትርጉሙን ቃል በቃል አይደለም ያስቀመጥኩት፤ እንዲያም ሆኖ ትርጉሙ ትክክል አይደለም የሚሉ ኦሮምኛ ተናጋሪዎችም አሉ።) የእርምት ትርጉሙን እስክናገኝ ይህንን ብለዋል በሚለው እንውሰደው እና ስሜታችንን እና ወገንተኝነታችንን የኋላ ኪሳችን አስቀምጠን ፖለቲካ እናውራ፤ እስኪ ዛሬ’ንኳ ሰው ይውጣን።

ኦዴፓ በኦሮሞ ሰዎች የተመሠረተ ፓርቲ ቢሆንም የኦሮሞ ሕዝብ አይደለም። ሌላው ቀርቶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጠ እንኳን አይደለም። ስለዚህ እንደ አንድ ሕዝብ መቁጠራችንን ትተን፣ ቅቡል ወኪል (legitimate agent) ለመሆን ብዙ እንደሚቀረው ፖለቲካዊ ፓርቲ እንየው እና እርምጃውን (እውነት ከሆነ) በምክንያት እናወድሰው ወይም እንውቀሰው። የዴሞግራፊ ለውጥ ለማምጣት ማሰቡ የት ያደርሰዋል? ሙከራው በሌላው ሕዝብ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ምንድን ነው? ከፖለቲካ፣ ከሕግ፣ ከሰብኣዊ መብቶች፣ ከመልካም አስተዳደር አንፃር ትክክለኛ ነው ወይስ ስህተት? የዴሞግራፊ ለውጥ በዓለም ታሪክ ውስጥ ኗሪ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው። (እንደምሳሌ የአዲስ አበባን ዘውግ-ተኮር (ethnic-based) የመቶ ዓመት የዴሞግራፊ ለውጥ ከአዲስ ማለዳ ጋዜጣ ቁጥር አንድ እትም ተውሼ አስቀምጫለሁ።

የዘውግ አረዳድም እንደ ዴሞግራፊ ቋሚ ስላልሆነ ያኔ እንደተለያዩ ዘውጎች ይታዩ የነበሩት ሸዋ፣ ጎጃሜ፣ አማራ የሚሉት አሁን የተለየ አረዳድ ነው ያላቸው፤ ሌሎችም የተነወሩ ሥሞች ለዚህ ዘመን ተዋስኦ እንዲስማሙ ተቀይረዋል…) በዚህ መሠረት እና ከአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የዴሞግራፊ ለውጥ እንደ ተፈጥሯዊ ማኅበራዊ ዕድገት የሚታየው በምን ዓይነት ሁኔታ ሲከናወን ነው? እነ ለማ መገርሳ የዴሞግራፊ ለውጥ ለማድረግ እየሠሩ ከሆነ ግባቸው ምንድን ነው? የምርጫ ዘውጌ-ዤሪማንደሪንግ መፍጠር ይሆን ይሆን? ከተሞችን ኦሮሞኣዊነት ማላበስ ይሆን ይሆን? ቢሆንስ ችግሩ ምንድን ነው? ወይስ የችግሩ አስኳል ምንድን ነው? ነው ወይስ ችግር አይደለም?

LEAVE A REPLY