ዐበይት አጫጭር ዜናዎች | ከዋዜማ ራዲዮ

ዐበይት አጫጭር ዜናዎች | ከዋዜማ ራዲዮ

1. ፖሊስ ከቀድሞው የሱማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ኡመር ሞሐመድ ጋር የተከሰሱ 41 ግለሰቦችን ይዞ እንዲያቀርብ ፍርድ ቤት ድጋሚ አዟል፡፡ ዐቃቤ ሕግ ግን ተጠርጣሪዎቹ በአድራሻቸው እንዳልተገኙ ገልጧል፡፡ ፍርድ ቤቱ በበኩሉ በአዳራሻቸው ካልተገኙ በአካባቢያቸው አለመኖራቸውን የሚገልጽ ማስረጃ ይቅረብልኝ ብሏል፡፡ የመጨረሻ ያለውን 14 ቀንም ፈቅዷል፡፡ የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሃን ጣሂር ግን ችሎቱ ገለልተኛ አይደለም ሲሉ ወቅሰዋል፡፡ ከ10 ቀናት በፊት ችሎቱ ለ2 ተከሳሾች አስተርጓሚ እንዲቀርብላቸው አዝዞ የነበረ ቢሆንም ፖሊስ ግን አስተርጓሚ ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡ ቀጣዩ ችሎት ለመጋቢት 20 ተቀጥሯል፡፡

2. የዲያስፖራው ማኅብረሰብ አባላት ሀገር ቤት ላሉ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው የጤና እና አደጋ መድኅን መግዛት የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቶላቸዋል፡፡ የመድኅን ሽፋኑን የሚሰጠው ጸሃይ ኢንሹራንስ ኩባንያ ሲሆን ለአግልግሎቱም ከብሄራዊ ባንክ ፍቃድ ማግኘቱን ሥራ አስኪያጁ ካሣ ልሳነ ወርቅ ዛሬ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን ሪፖርተር አስነብቧል፡፡ የመድኅን ሽፋኑ “Accident and Health Medical Cover Insurance for the Families of Ethiopian Diaspora” በሚል ይታወቃል፡፡ በመላው ዐለም ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መድኅኑን ከድረ ገጽ መግዛት ይችላሉ፡፡ በተገዛው መድኅን ልክ ኩባንያው የተጠቃሚዎችን የሕክምና ወጭ ይሸፍናል፤ የድንገተኛ አደጋ ካሳ ይከፍላል፡፡

3. ኢሕአዴግ ወደ ውህድ አሃዳዊ ፓርቲ ሲቀየር አብረው መዋሃድ የሚፈልጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካሉ በሬ ክፍት ነው- ብሏል ኢሕአዴግ፡፡ ለውህደቱ ዋናው መስፈርት የኢሕአዴግን መሠረታዊ ባሕሪያት መቀበል ብቻ መሆኑን የግንባሩ ሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ ሳዳት ነሻ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ይመሰረታል የተባለለት አሃዳዊ ፓርቲ የኢሕአዴግ መሠረታዊ ባሕሪያት የሆኑትን የብሔርና የቋንቋ ማንነቶችንና የፌዴራል ሥርዓቱ መርሆዎችን እንዳለ ሳይቀየሩ የሚወርስ ይሆናል፡፡

4. ሰባት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች የጋራ ግንባር ለማቋቋም ተስማምተዋል፡፡ ፓርቲዎቹ የመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ አንድነት ፓርቲ (ኢብአፓ)፣ የአፋር ሕዝቦች ነጻነት ፓርቲ፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዴህ)፣ የአፋር ሕዝቦች ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እና የኦሮሞ ሕዝቦች ፍትሃዊ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ናቸው፡፡ የጋራ ግንባሩን ደንብና መመሪያ እንዲያዘጋጅ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመናል- ብለዋል አመራሮቹ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፡፡ አዲሱ ግንባር በ2 ወራት በምርጫ ቦርድ ተመዝግቦ ወደ ሥራ ይገባል፡፡ ፓርቲዎቹ በቀጣዩ ምርጫ በግንባሩ ብቻ ዕጩዎችን የማቅረብ ሃሳብ እንዳላቸው DW ዘግቧል፡፡

5. ገቢዎች ሚንስቴር 14 ቢሊዮን ብር የሚገመት ግብር የሰወሩና ያጭበረበሩ 105 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ ብሏል፡፡ 64ቱን ለፍርድ ቤት አቅርቧል፡፡ በወንጀል የተጠረጠሩ 57 ድርጅቶች ጉዳይም ወደ ፍርድ ቤት ተልኳል፡፡ በሕዝብ ንብረት ምዝበራና ግብር ማጭበርበር 135 ድርጅቶች ተለይተዋል፡፡ በግብር ማጭበርበር ወንጀል ዋና ተዋናይ የሆኑት አከፋፋዮችና አስመጭዎች ሲሆኑ ቸርቻሪዎችም አሉበት፡፡ የተጭበረበረው ግብር ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የገቢዎች ሚንስትሯ አዳነች አቤቤ በሰጡት መግለጫ መናገራቸውን ፋና ብሮድካስት ዘግቧል፡፡

6. በተፋጠነ ግንባታ ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያን ከሱማሌላንዷ በርበራ ወደብ ጋር የሚያገናኘው አውራ ጎዳና ነገ እንደሚመረቅ የሱማሌላንዱ ሆርን ዲፕሎማት ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡ ለነገው ምረቃ ስነ ሥርዓት ሁለቱ መንግሥታት ዝግጅት በማድረግ ተጠምደዋል፡፡

7. የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ትናንት ስብሰባውን አጠናቋል፡፡ ንቅናቄው ባወጣው መግለጫ ዞኖች እያቀረቧቸው ያሉ አዳዲስ የክልልነት ጥያቄዎች መላውን የክልሉን ሕዝብ ተጠቃሚ በሚያደርግ፣ በተረጋጋ እና መፍትሄ በሚያመጣ ሁኔታ በድርጅቱ እንዲመራ መግባባት ተደርሷል ብሏል፡፡

8. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ወረዳ ያለ ክልሉ መንግሥት ዕውቅና 190 የሚሊሺያ አባላት ወታደራዊ ሥልጠና ወስደዋል- ብሏል የክልሉ ሚሊሺያ ቢሮ፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ክልሉ ሚሊሺያውን እንደገና እያደራጀ እንደሆነ በክልሉ ጸጥታ ቢሮ የሚሊሺያ ዘርፍ ሃላፊው ደርጉ ዚያድ ለኢቢሲ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ በዚሁ ሳቢያ 140 የሚሊሺያ አባላት ተሰናብተዋል፤ በክልሉ ሰኔ 17 በተፈጠረው ግጭት የተጠረጠሩ 9 አባላት ደሞ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ሚሊሺያዎቹ ወታደራዊ ሥልጣንውን የት እና ለምን ዐላማ እንደወሰዱት ግን ዘገባው አላብራራም፡፡

LEAVE A REPLY